የደቡብ አፍሪካውያን ነፃነትና የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪካዊ ድርሻ

በፍቅር ለይኩን

የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ በቅርቡ ፻ኛ ዓመቱን የደቡብ አፍሪካዋ Judicial Capital በሆነችው በብሉምፎንቴን በታላቅ ድምቀት ተከብሯል፣ ይህች ውብ ከተማ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ን ታሪክ ከኢየሩሳሌም ቀጥሎ ሁለተኛ የሆነው የቅድስት ሥላሴ ወቅዱስ ያሬድ ገዳምና የካህናት ማሰልጠኛ ተቋም የተቋቋመባትና የተገደመባት ከተማ መሆኗን ልብ ይሏል፡፡ የደቡብ አፍሪካውያኑ ANC ፓርቲ በአፍሪካ ከተቋቋሙ ፓርቲዎች አንጋፋውና ረጅም ዕድሜ ጭምርም ያሰቆጠረ ነው።

የአፍሪካን የሰው ኃይልና የተፈጥሮ ሀብት ለመዝረፍ አፍሪካን በቅኝ ግዛት የተቀራመቱት አውሮፓውያን በዋነኝነት አፍሪካን ምድር የረገጡበት ምክንያታቸው አፍሪካን በወንጌል ቃል ለማቅናት ነው የሚል ቢሆንም በሂደት ግን የአፍሪካውያን የሰው ኃይልና የተፈጥሮ ሀብትን በመዝረፍ ለአፍሪካውያን ታላቅ ስብራትን ጥሎ ያለፈና ይሄ ነው ተብሎ ሊገመት የማይችል ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ታሪካዊ ቀውስንና ክስረትን ሊያተረፍ የቻለ የአፍሪካውያን መራር ጨለማ ዘመን ታሪክ ሆኖ ሊያልፍ በቅቷል፡፡

አፍሪካውያን ወይም በአጠቃላይ ጥቁር ህዝብ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ሰብዕና የለውም ብሎ የሚያምነው የአውሮፓውያን አፍሪካን በቅኝ ግዛት የመቀራመት ዘመቻ፤ ጥቁር ህዝቦችን ከሰውነት ተራ በማውረድ በገዛ መሬታቸው ባይተዋር የሆኑበትንና የተፈጥሮ ሀብታቸው ተዘርፎ ባህላቸው ተንቆ፣ በዘመናት ያፈሩት ስልጣኔያቸው፣ ታሪካቸውና ቅርሳቸው የእነሱ እንዳልሆነና ጥቁር ህዝብ እንዲህ ዓይነት የረቀቀና የመጠቀ ስልጣኔ ባለቤት አይሆንም በሚል እኩይ አስተሳሰብ ቅርሶቻቸውና ታሪካቸው በአውሮፓ ቤተ-መዘክሮችና ዐውድ ርዕዮች ተግዘው ለእነሱ ከፍተኛ የገቢ ማስገኛ ምንጮች በመሆን አፍሪካውያን በገዛ ታሪካቸውና ቅርሳቸው ባይተዋር ሆነው ታሪክና ቅርስ አልባ የሆኑበትን ዘግናኛ የመከራና የሰቆቃ ዘመን በአፍሪካ ታላቅ ታሪክ ጠባሳን ጥሎ አልፏል፡፡

በዚህ ግፍና መከራ ኅሊናቸው የቆሰሉ አፍሪካውያን ይሄን ግፈኛ ስርዓት ከጫንቃቸው አሽቀንጥሮ ለመጣል ሲሉ ነበር በ፳ኛው መቶ ክ/ዘመን መባቻ የጸረ-ኮሎኒያሊስት እንቅስቃሴ በአፍሪካ መቀጣጠል የጀመረው፣ በተለይም ደግሞ በደቡብ አፍሪካ በነበረው የአፓርታይድ ዘረኛና ከፋፋይ ሥርዓት ክፉኛ የተቆጡና የህዝባቸው ውርደትና ሰቆቃ በእጅጉ እንቅልፍ የነሳቸው አፍሪካውያን ይህን ሥርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ታሪክ ሊያደርጉት ከዛሬ መቶ ኣመት በፊት የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ African National Congress Party (ANC) አቋቋሙ፡፡ የዚህ አንጋፋ ፓርቲ ጽንሰትና ልደትም ምክንያቶቹ የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሚከተሉ ደቡብ አፍሪካውያን የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮችና የነፃነት ፋኖዎች ነበሩ፡፡

ለሰው ልጆች ሁሉ ከፈጣሪ ዘንድ ስለተሰጠ ነፃነትና ክብር በግልጽ የምታሰተምረው ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን፡- ነፃነት የሰው ልጅ ከአምላኩ የተሰጠው ክብሩ መሆኑን ቅዱሳት መጻህፍትንም ዋቢ በማድረግ፣ የሰው ልጅ በታሪኩ ዘመን ለነፃነቱ የከፈለውን ክቡርና ውድ ዋጋ የእግዚአብሔርን ህዝበ ታሪክ በመጥቀስ በዘመኗ ሁሉ ስታስተምር ቆይታለች፤ አሁንም በማስተማር ላይ ነች፣ ወደፊትም እንዲሁ፡፡ ለዘመናት ሀገራችን በነፃነት ኮርታ የመቆየቷ፣ የህዝቦቿም አይበገሬነት ምስጢሩ ይኽው ቤተክርስቲያን ለሰው ልጆች ነፃነትና ክብር ካላት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ከሆነ አስተምህሮ የተነሳ ነው፡፡ ለጥቁር ህዝቦች ሁሉ ትልቅ ድልን ያጎናጸፈው የአድዋው ድል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ትልቅ መንፈሳዊ ተጋድሎ፣ ጸሎትና ትልቅ የሆነ ታሪካዊ አሻራ ያለበት እንደሆነ በተለያዩ የውጭ ሀገርና የሀገራችን የታሪክ ምሁራንና ተመራማሪዎች ዘንድ ብዙ የተነገረለትና የተፃፈለት ነው፡፡

በ፳ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን መሰረት በማድረግ በሰሜን በአሜሪካ፣ በካረቢያንና በጃሜይካ እና በመላው አፍሪካ እንዲሁም በተለይ ደግሞ በደቡብ አፍሪካ በስፋት የተነሱ የነፃነት እንቅስቃሴዎች በዋነኝነት መነሻ ያደረጉት የኢትዮጵያን የረጅም ዘመን ስልጣኔ እና ታሪክ፣ የህዝባችንን አኩሪ የነፃነት ተጋድሎን፣ ክርስትናን በቀደምትነት ሰላማዊ በሆነ መንገድ የተቀበለችና በአፍሪካ በቀዳሚነት የክርስትና ማዕከል መሆኗን፣ ከዚህም የተነሳ በተደጋጋሚ በቅዱሳን መጻህፍትና በተደጋጋሚ መጠቀሷ፣ በጥንት ጸሀፍትና ታሪክ ተመራማሪዎች ዘንድ ብዙ የተነገረላትና የተፃፈላት መሆኑ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የሺ ዘመን አኩሪ ታሪክ የብዙዎችን ቀልብ በመሳቡ በተጨማሪም በ ፲፱ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማብቂያ ላይ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ጀግንነትና ኢትዮጵያውያን አንድነት በዘመናዊ መልኩ ተደራጅቶ የመጣውን የኢጣሊያ ወራሪ ጦር በማንበርከክ በመላው አውሮፓውያን ቀኝ ገዢዎች ዘንድ መደናገጥንና ለመላው ጥቁር ህዝቦች ደግሞ አዲስ የሆነ የነፃነት ፋና የለኮሰውን ኢትዮጵያውያን በአድዋው ጦርነት የተጎናጸፉት ታላቅ ድል በአፍሪካ፣ በአፍሪካ አሜሪካውያን፣ በካረቢያና በጃሜይካ ጥቁር ህዝቦች ዘንድ ትልቅ የነፃነት ጥያቄ ማስነሳቱና ለዚህም የነፃነት ጥያቄ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የነፃነት ትግሉ ዋና ማዕከልና መነሻ በመሆን ትልቅ ድርሻ የወሰዱበት ታላቅ የታሪክ ምዕራፍ ሊከፈት ችሏል፡፡

በደቡብ አፍሪካውያን፣ በአፍሪካ አሜሪካውያን፣ በካረቢያንና በጃሜይካውያን ህዝቦች ዘንድ በእጅጉ ተስፋ ትደረግ የነበረችው ቤተክርስቲያናችን ለሰው ልጆች ነፃነትና በተለይም ደግሞ ለአፍሪካዊ ወንድማማችነት መንፈስ (Pan Africanism) ትልቅ የሆነ ታሪካዊ ድርሻን አበርክታለች፡፡ የዚህን ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን ለነፃነት የከፈለችውን ክቡርና ውድ ዋጋ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት፣ በላቲን አሜሪካ እንዲሁም በአፍሪካ አሜሪካውያን ዘንድ ያሳደረውን ትልቅ መነሳሳትና ወኔ እንዲሁም ታሪካዊ ፋይዳ በጉልህ የሚያስገነዝብ እውነታ በዚህ በደቡብ አፍሪካ ህያው የሆነ የታሪክ ትስስሩን ጠብቆ ቆይቷል፡፡

የዛሬው አንጋፋው የአፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ (African National Congress Party-ANC) መጸነስና መወለድ ምክንያት የሆነችው ሀገራችን ኢትዮጵያና፣ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካውያን የነፃነት ተጋድሎ ታሪክ ውስጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የነበራትን ታሪካዊ ፋይዳና ጉልህ ድርሻ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት ታቦ እምቤኪ እ.ኤ.አ በ2010 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሴኔት በወሰነው መሰረት በሕግ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ በተሰጣቸው ጊዜ በዳረጉት ንግግር ቤተክርስቲያናችን በደቡብ አፍሪካውያን የነፃነት ተጋድሎ ታሪክ ውስጥ የነበራትን ጉልህ ድርሻ እንዲህ ነበር የገለጹት፡-

ዘመናዊው የአፍሪካ የነፃነት ንቅናቄ የመነጨው ወደ ፲፱ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ አካባቢ በደቡብ አፍሪካ ነበር፣ የዚህ ንቅናቄ የቀድሞ መስራቾች የሀገራችን የመጀመሪያዎቹ ዘመናዊ አፍሪካውያ ልሂቃን ናቸው፡፡ የተነሱትም ከአብያተክርስቲያናት ትምህርት ቤቶች ሲሆን፣ የመጀመሪያዎቹ አፍሪካውያን የቤተክርስቲያን አገልጋዮችም ነበሩ፡፡ እነዚህ ዘመናዊ የአፍሪካ ልሂቃን ከአውሮፓውያን ሚስዮኖች እራሳቸውን አላቀው በቤተክርስቲያናቱ ላይ ባለቤትነታቸውን ሲያውጁ፣ እነደመነሻ የተጠቀሙት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በመዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፷፰ ላይ ይገኛል፤ ይህም፡- ‹‹መኳንት ከግብጽ ይመጣሉ፣ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች፡፡›› የሚለው ነው፡፡

እንደ ቅኝ ገዢዎች አፍሪካ የአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት እሽቀድድም ሰለባ ሆና በኖረችበት ወቅት ኢትዮጵያ ነፃነቷን እንደያዘች መቀጠሏ መነሳሳትን ይሰጣቸው ነበር፣ እናም በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተተነበየው ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ስትዘረጋ ቤተክርስቲያናችን በአፍሪካዊ ስነ ምግባር ትሞላለች ብለው ያምኑ ነበር፡፡ ይህች እውነተኛ የአፍሪካ ቤተክርስቲን ደግሞ አፍሪካያን በሙሉ ለነፃነት፣ ለባህላቸው፣ ለልዑላዊነታቸው፣ ለማንነታቸውና ለሰብአዊነታቸው እንዲከበር ላላቸው ህልም እንደማከማቻ ቦታ ሆና ታገለግላለች ብለው ያምኑ ነበር፡፡ ታዲያ በዚህ እውነታ እና ታሪካዊ ሀቅ ላይ ተመስርተው ነበር እነዚህ የጠቀስናቸው ቤተ ክርስቲያናት እራሳቸውን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ብለው የሰየሙት፡፡ በአህጉራችን ላይ የመጀመሪያው ዘመናዊ የብሔራዊ ንቅናቄ የሆነው የደቡብ አፍሪካው አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ (ANC) የተወለደውም ከነዚሁ ከሀገራችን የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ውስጥ ነው. . . የፓርቲያችን የመጀመሪያ ፕሬዝዳንት የነበሩት ቄስ ጆን ዱቤም የዚሁ የደቡብ አፍሪካ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መሪ ነበሩ… ፡፡1

የመቶ ዓመቱ ባለዕድሜ የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ (ANC) የነፃነት እንቅስቃሴ እና የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት የታቦ እምቤኪ ታሪካዊ ንግግር የሚነግረን ሐቅ ቢኖር ለሰው ልጆች ከፈጣሪ ለተቸረው ነፃነትና ክብር ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የነበራትን ጽናትና መንፈሳዊ ተጋድሎዋን ነው፡፡ ይሄ የቤተክርስቲያናችን መንፈሳዊ ተጋድሎና መልካም ስም ተጠብቆ እንዲቆይ እንዲሁም የቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮዋ የሆነውን የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ቅዱስ ወንጌል ለሰዎች ሁሉ በቋንቋቸው ለማዳረስ ዛሬስ በዚህ ዘመን የምንገኝ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ኃላፊነት ምን ድረስ ሊሆን ይገባዋል የሚለውን ጥያቄ የመመለስ የሁሉም የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮችና ልጆች ኃላፊነት ነው፡፡