በለንደን ደብረ ጽዮን የደረሰው የወያኔ ጥቃት በዲሲ ደብረ ሰላም እንዳይደገም

በለንደን ደብረ ጽዮን የደረሰው የወያኔ ጥቃት በዲሲ ደብረ ሰላም እንዳይደገም

ከታዛቢዎች

ጠላት ከሩቅ አይመጣም እንደሚባለው አቶ አዲሱ አበበ የደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያንን ከውስጥ ሆኖ መገዝገዝ ከጀመረ ወራቶች ተቆጥረዋል። ግለሰቡ የተለያየ ሰበብና ምክንያት ቢደረድርም ዋናው ዓላማው ቤተክርስቲያኒቷን ለወያኔው ሹመኛ ለአባ መላኩ (ፋኑኤል) መጠቀሚያ አናደርጋትም በማለት በጽናት የቆዩትን የባለ አደራዎች ቦርድ አባላትንና ካህናትን ለማስወገድ ነው። ይህንን ሁኔታ የቤተክርስቲያናችንን ሁኔታ እግር በእግር የምንከተታተል ምዕመናን ከተገነዘብነው ውለን አድረናል። ይህ ግለሰብ በስውር የተሰጠውን ቤተክርስቲያኒቷን ለወያኔ የማስረከብ ጥረት በአደባባይ ለማሳካት ባለመቻሉ ጭምብሉን አውልቆ ጥሎ በግላጭ መንቀሳቀሱን በመቀጠል የቤተክርስቲያኒቷን መተዳደሪያ ደንብ ተከትሎ በአባል ምዕመናን በአብላጫ ድምፅ የተመረጠውን የባለአደራዎች ቦርድ መተናነቁን አጠናክሮ ቀጥሎበታል። ከአሁን በፊት በትለያዩ ጊዜዎች ዕሁድ ከቅዳሴ በኋላ በየመኪናችን ላይ ይቀመጡልን የነበሩ አድራሻና ስም የሌላቸው የቤተክርስቲያናችንን አካሄድ የሚኮንኑ ወረቀቶችን እናስታውሳለን። አቶ አዲሱ ቤተክርስቲያኒቷን በወያኔ በቀጥታ ለሚታዘዙት ለከሃዲውና ለአታላዩ ለአባ መላኩ አሳልፎ ለመስጠት ዱካውን አጥፍቶ በስውር ሲያደርግ የነበረው ደባ ሊሳካለት ስላልቻለ ወደ አደባባይ ከመውጣት ሌላ አማራጭ አልነበረውም።  ይህንንም ለማድረግ በቤተክርስቲያኒቷ ውስጥ ያለውን ከህንጻ የማሰራት እንቅስቃሴዎች ጋር የተከሰቱትን ችግሮች እየተጠቀመባቸው ይገኛል። በመሠረቱ ግለሰቡ ከወያኔ ጋር ለመስራትና ለመጎናበስ ከፈለገ መብቱ ቢሆንም ቤተክርስቲያንን እንደገጸበረከት ለማቅረብ መድፈሩን ግን አበክረን እንቃወማለን።

አቶ አዲሱ በቤተክርስቲያኒቷ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ያለውን አስተያየትም ሆነ ቅሬታ እንዲያቀርብ እድሎች ቢሰጡትም “ውሃን የሚያስጮኽው እውስጡ ያለው ድንጋይ ነው” እንደሚባለው ዓላማው ሐይማኖታዊና ትክክለኛ ስላልነበር የመረጠው እንደ ቁራ መጮህን ነው። ዕድሉን ሊጠቀምበት አልቻለም። እንደውም ነባርና ለረዥም ዓመታት የቤተክርስቲያኒቷ አባል የሆኑ ምዕመናንን አሳስቶና ጠምዝዞ የሱን የጥፋት ዱካ እንዲከተሉ ለማድረግ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም። የቤተክርስቲያኒቷ ግንባታ ዕቅድ በምዕመናን ፊት ከጸደቀ ከወራት በኋላ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚለውና አታሞ የሚመታው አላማው ሌላ ስለሆነ ነው።ይኽውም ቤተክርስቲያኒቷን ለወያኔ ለማስረከብ ነው። ለዚህም እኩይ ዓላማው አልበገር ያሉትን የቤተክርስቲያኒቷን አስተዳዳሪ ከቦታቸው ለማስነሳት ነው። የቤተክርስቲያኒቷ አስተዳዳሪ በወሰዱት ጠንካራና ትክክለኛ ውሳኔዎች በተለይም በዝሙት ምክንያት ታደሰ ሲሳይ የተባሉ ቀድሞ በቅስና አገልግሎት ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ላይ የነበሩ ግለሰብን ከሌሎች ካህናት ጋር ሆነው ማውገዛቸውንና ስልጣነ ክህነታቸውን መግፈፋቸው ወያኔው አባ መላኩንና አቶ አዲሱን እንዳንጨረጨረቸው ይታወቃል። የደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ በተለያዩ አጋጣሚዎች በቅርቡ ስለ አገራችን ኢትዮጵያ የተናገሯቸው ንግግሮችና ቤተክርስቲያናችንን በወያኔ እንዳትነጠቅ አጥር በመሆናቸው ለአቶ አዲሱ የእግር እሳት ሆኖበታል። በመሆኑም አሁን የተፈጠረውን ሁኔታ አራግቦና አፋፍሞ ከቁጥጥር ውጭ የወጣ እረብሻና ሽብር በመፍጠር አስተዳዳሪውን ከስልጣናቸው አውርዶ ከአሁን በፊት የተባረሩትን መልሶ በማምጣት በአባ መላኩ ሥር ቤተክርስቲያኒቷን ለማስገባት የተጠነሰሰ ሴራ ነው። ግርግር ለሌባ ይመቻልና ነው።

ባለፈው ቅዳሜ እራሱ በአቢሲኒያ ሬዲዮ ላይ እንደተናገረው የኢትዮጵያ አባቶች “እንዴት ናቸሁ?” ብለዋል በማለት ከማን ጋር እየሰራ እንደሆነ አሳውቋል።አፍ ሲያመልጥ እራስ ሲመለጥ ማለት ይህ ነው። ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም የኢ/ኢ/ተ/ቤ/ክ እራሷን የቻለችና በአሥተዳደር ገለልተኛ የሆነች ደብር እንደሆነች እየታወቀ የተለያዩ ገዳማት ሲፈርሱና የጻድቃንና የሰማዕታት መካነ መቃብራት እንደ ዋልድባ ገዳም ዓይነቶች ሲደፈሩና በግሬደር ሲጠረጉ ትንፍሽ ያላሉ አባቶች እንዴት ነው አሜሪካን አገር በርቀት ያለ ጉዳይ እንቅልፍ የነሳቸው? በጣም አስቂኝ ፌዝ ነው። አቶ አዲሱ ከአቢሲኒያ ሬዲዮ አዘጋጅና አቅራቢ ጋር በቅድሚያ የተቀነባበረ በሚመስል ሁኔታ የደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን የበላይ ጠባቂ የሆኑትን አንጋፋውን ሊቀ-ሊቃውንት ወርቅነህ ኃይሌንና ሌሎችንም ካህናት በቦርዱ ላይ ለማነሳሳትና ክፍፍል በመፍጠር የአዲሱ የጥፋት ድርጊት ተባባሪ ለማድረግ ያደረጉት ሙከራም ባለፈው ዕሁድ በቤተክርስቲያኒቷ ውስጥ ምልዓቱ ጉባዔው በተሟላ አባላት በተደረገው ስብሰባ ላይ ከሽፏል። አዲሱ ባለፈው ዕሁድ የመጨረሻው ሽንፈት ስለደረሰበት ሊያደርግ የሚችለው ምን እንደሆነ ለመገመገት አስቸጋሪ ቢሆንም እኛ ግን ይቅርታ ጠይቆ ተመልሶ በአባልነቱ እንዲቀጥል እንመክረዋለን። ምዕመናን የዲሲ ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን የለንደን ደብረጽዮን ቤተክርስቲያን ሆና ለከፍተኛ ችግር እንዳይዳረጉ፣መሳለቂያ እንዳይሆኑና በወያኔ ስውርና አደገኛ ወጥመድ ውስጥ እንዳይገቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉና ጉዳዩን አበክረው እንዲከታተሉ አደራ እንላለን። በለንደን ደብረጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ላይ በወያኔ እየደረሰ ያለውን እጅግ የሚያሳዝን ጉዳት የሚያሳይ መረጃ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ። ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን