ዓለም በጦርነት እየተናወጠች ነው፣ ከዚህ ጦርነት አትራፊው ማነው? War profiteering – List of countries and companies engaged in business of war
በሳምሶን ደሳለኝ
ዓለም በጦርነት እየተናወጠች ነው። ዓለምን እየናጠ ካለው ጦርነት አትራፊውስ ማነው? እንዴት ከጦርነት ይተረፋል? ከጦርነት ምን መልካም ነገር ሊገኝ ይችላል? ጦርነት እንዴት አዋጪ ስራ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል? እነዚህን መሰል ጥያቄዎች እያነሳ እየተጨነቀ የሚጠይቅ ሰው ወይም በሕግ ሰውነት ያለው አካል የሞራል ልዕልናው ከፍ ያለ ተደርጎ ይወሰዳል። በአንፃሩ ግን በዓለም ዓቀፉ ኮርፖሬት ኢፔሪያሊዝም መረብ ውስጥ የወደቀ ግለሰብ፣ ተቋም፣ ሀገር፣ ፖለቲከኛ፣ ሃይማኖተኛ፣ ባለሙያ እንዲሁም ሌሎች አካሎች፤ ከላይ ከጦርነት ጋር ተያያዥ ሆነው የቀረቡ መጠይቆችን ለመመለስ ብዙም የሚቸገሩ አይደለም። ምክንያቱም ጦርነትን የሚመለከቱት ከሞራል መነሻ ሳይሆን ከአትራፊነቱ በመሆኑ ነው።
ይህም ሲባል፣ የዓለም ዓቀፉ ኮርፖሬት ኢፔሪያሊዝም ስለጦርነት ያለውን አረዳድን ታዋቂው ጆርጅ ኦርዌል ሲያስቀምጠው “War against a foreign country only happens when the moneyed classes think they are going to profit from it.” ጦርነት በውጭ ሀገራት ላይ የሚካሄደው የዓለም ዓቀፉ ኮርፖሬት ኢፔሪያሊዝም ከጦርነቱ ትርፍ እንደሚያገኙ ሲገምቱ ነው። ይህ ማለት ዓለም አቀፍ ባለጸጎች በጦርነት ትርፍ ማግኘታቸውን ሳያረጋግጡ ወደ ጦርነት ውስጥ አይገቡም። ወይም ትርፍ ዓልባ ጦርነት ሲካሄድም ቅድሚያ ሰጥተው አይመለከቱትም።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በአስረጅነት የስቶኮልም ዓለም ዓቀፍ የሰላም ምርመር ተቋም (Stockholm International Peace Research Institute (SIPRI)) በጦር መሰሪያ ሽያጭ ካዝናቸውን ያደለቡ የዓለም ዓቀፉ ኮርፖሬት ኢምፔሪያሊዝም ተቋማት ላይ ያደረገውን ጥናት ይፋ አድርጎል። እነዚህ ኩባንያዎች በዓለም ላይ የሚፈበርኩት ጦርነት ምን ያህል አዋጪ ስራቸው እንደሆነ በዝርዝር አስቀምጠዋል። ኩባንያዎቹ በሚያገኙትም ከፍተኛ ትርፍ በተለያዩ ሀገሮች በሚደረጉ ሀገር አቀፍ ምርጫዎች ላይ እንዴት ተፅዕኖ እንደሚያሳድሩ በመረጃ አስደግፈው አሳይተዋል። ለተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫ ዘመቻ የሚሆን ከፍተኛ መጠን ያለው ዶላሮች በመመደብ ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም እንደሚሰሩም ጥናቱ ያሳያል። ከዚህም በላይ ርቀው ሄደው የመራጩን ሕዝብ ድምጽ ላይ በመገናኛ ብዙሃን ተፅዕኖ በማሳደር ለሚፈልጉት የፖለቲካ ፓርቲ መራጩን ሕዝብ ድምፅን እንዲሰጥ ከፍተኛ ጫና ያሳድራሉ። ቤት ለቤት እየዞሩ ቅስቀሳ ለሚያደርጉ ግለሰቦችም ከፍተኛ ክፍያ ይፈጽማሉ።
ለምሳሌ በፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ እና በሪፕብሊካኑ እጩ በነበሩት ሚቲ ሮምኒ መካከል እንዲሁም ለኮንግረስ እና ለሴኔት በተደረገው የእ.ኤ.አ. 2013 ምርጫ 6 ቢሊዮን ዶላር በሀገረ አሜሪካ ወጪ ሆኗል። የምርጫ መሰረተ ልማት ከከተማ እስከ ገጠር ከተሞች ድረስ መዋቅራዊ በሆነ መልኩ የዘረጋችው አሜሪካ ለአንድ ዘመን ምርጫ 6 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ማድረጓን ተከትሎ፣ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ሳይሆን የህዝብ ድምጽን በይፋ መግዛት ነው የሚመስለው። በዘመናዊ ኤሌክትሮኒክስ ድምፅ መስጫ የተካሄደ የድምጽ አሰጣጥ ስነስርዓት ለምን ይህን ያህል ወጪ ጠየቀ? ወጪውንስ የሚሸፍኑት እነማናቸው? ይህን ያህል ወጪስ ማውጣት ለምን አስፈለጋቸው? የዴሞክራትና የሪፐብሊካን አባላት ብቻቸውን ይህን ያህል ወጪስ ማውጣት ይችላሉ? የአሜሪካ መንግስትስ ይህን ወጪ ሸፍኖት ይሆን? ለምርጫ የወጣው ወጪስ በሕጋዊ መንገድ ወደ ምርጫው የገባ ነው? የዓለም ዓቀፉ ኮርፖሬት ኢምፔሪያሊዝም ተቋማት በአሜሪካ ምርጫ ላይ ያላቸው ሚናስ ምን ነበረ? የምርጫውን ወጪስ እነሱ ሸፍነውት ይሆን? ወይንስ ሌሎች?
የስቶኮልም ዓለም ዓቀፍ የሰላም ምርምር ተቋም (Stockholm International Peace Research Institute (SIPRI)) በጥናቱ ከመቶ በላይ በጦርነት መካከል በመሳሪያ ሽያጭ ካዝናቸውን ያደለቡና ከተለያዩ ዓለም ዓቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ጋር ያላቸውን ግንኙነት በጥልቀት አጥንቶ አቅርቧል። ለማሳያ ሊሆኑ የሚችሉ አስር የዓለም ዓቀፉ ኮርፖሬት ኢምፔሪያሊዝም ተቋማትን በዚህ ጽሁፍ ለማሳየት ተሞክሯል።
በዓለም ዓቀፍ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ከፍተኛ የሆነ የገበያ ድርሻ ያላቸው የአሜሪካ ኩባንያዎች ናቸው። በዓለም ከታወቁት አስር የጦር መሳሪያ አምራችና ሻጭ ኩባንያዎች መካከል ስድስቱ የአሜሪካ ኩባንያዎች ናቸው። ከመቶዎቹ የጦር መሳሪያ አምራቾች መካከል 39 አሜሪካ ተቀማጭ የሆኑ ናቸው። ከእነዚህ መቶ የጦር መሳሪያ አምራቾች ሃምሳ ስምንት በመቶ የሽያጭ ድርሻ የምትወስደው አሜሪካ ነች። የምዕራብ አውሮፓ ሀገሮች በበኩላቸው 28 በመቶ የሚሆነው የገበያ ድርሻ ይወስዳሉ።
10. ታለስ ግሩፕ “Thales Group (Paris)”
ይህ የፈረንሳይ የጦር መሳሪያ አምራች ድርጅት እ.ኤ.አ. ከ2013 እስከ 2014 አጠቃላይ ሽያጩ 10 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ከዚህ ውስጥ የተጣራ ሽያጩ 800 ሚሊዮን ዶላር ነበር።
9. Finmeccanica S.p.A. (Italy)
ይህ የኢጣሊያ የጦር መሳሪያ አምራች ድርጅት እ.ኤ.አ. ከ2013 እስከ 2014 አጠቃላይ ሽያጩ 10 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ከዚህ ውስጥ የተጣራ ሽያጩ 100 ሚሊዮን ዶላር ነበር። ሌላው ተቋሙ በአሜሪካን የምርጫ ዘመቻ ላይ ከፍተኛ ዶላር በማፍሰስም የሚጠቀስ መሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ።
8. United Technologies (U.S.)
ይህ የአሜሪካ የጦር መሳሪያ አምራች ድርጅት እ.ኤ.አ. ከ2013 እስከ 2014 አጠቃላይ ሽያጩ 11.9 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ከዚህ ውስጥ የተጣራ ሽያጩ 5 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ነበር። ይህ ኩባንያ እ.ኤ.አ. ከ1990 ጀምሮ በአሜሪካ ሀገር አቀፍ ምርጫ ላይ ከፍተኛ ዶላር ከሚያፈሱ አንዱ ነው። በ2014 ፖለቲከኞችን ለማግባባት (LOBBYING) እስከ 15 ሚሊዮን ዶላር ድረስ ወጪ አድርጓል። ሃያ አራት የሚጠጉ የአሜሪካ የኮንግረስ አባላት በዚህ ተቋም ውስጥ የአክሲዮን ድርሻ አላቸው።
7. Airbus Group (France/Netherlands)
ይህ የአውሮፓ ሀገሮች የጦር መሳሪያ አምራች ድርጅት እ.ኤ.አ. ከ2013 እስከ 2014 አጠቃላይ ሽያጩ 15 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ከዚህ ውስጥ የተጣራ ሽያጩ 2 ቢሊዮን ዶላር ነበር።
6. General Dynamics (U.S.)
ይህ የአሜሪካ የጦር መሳሪያ አምራች ድርጅት እ.ኤ.አ. ከ2013 እስከ 2014 አጠቃላይ ሽያጩ 18 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ከዚህ ውስጥ የተጣራ ሽያጩ 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ነበር። ይህም ኩባንያ ከ1990 ጀምሮ ከፍተኛ በሀገር አቀፍ ምርጫ ከፍተኛ ዶላሮች ከሚያፈሱት አንዱ ሲሆን በሀገር አሜሪካም የመከላከያ ስራዎች ኮንትራት ከሚወስዱ ተጠቃሽ ኩባንያ ነው። ተዋጊ ጀቶች፣ የጦር መርከቦች፣ ሰርጓጅ መርከቦችን ታንኮች እና ሌሎች ጦር መሳሪያዎችን ያመርታል። ሕግ አውጪዎችን በማግባባትም ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ ነው።
5. Northrop Grumman (U.S.)
ይህ የአሜሪካ የጦር መሳሪያ አምራች ድርጅት እ.ኤ.አ. ከ2013 እስከ 2014 አጠቃላይ ሽያጩ 20 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ከዚህ ውስጥ የተጣራ ሽያጩ ትርፉ 2 ቢሊዮን ዶላር ነበር። በዓለማችን አራተኛው የመከላከያ ኮንትራክተር ሲሆን በኤሮስፔስ ሲስተም በኤሌክትሮኒክስ ሲስተም የመርከብ ግንባታ እና ሌሎች ተዛማጅ ስራዎችን የሚሰራ ግዙፍ ኩባንያ ነው። በ2008 ምርጫ 2 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ዴሞክራት ፓርቲን ወክለው ለፌዴራል ምርጫ ዕጩ ለነበሩ ድጋፍ አድርጓል።
4. Raytheon (U.S.)
ይህ የአሜሪካ የጦር መሳሪያ አምራች ድርጅት እ.ኤ.አ. ከ2013 እስከ 2014 አጠቃላይ ሽያጩ 29 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ከዚህ ውስጥ የተጣራ የሽያጩ ትርፉ 2 ቢሊዮን ዶላር ነበር። ኩባንያው ሚሳኤሎችን በተለይ በምሪቲ የሚሰሩ ሚሳኤሎችን በማምረት ስፔሻላይዝድ ያደረገ ነው። በ2008 ምርጫ 55 በመቶ ለዴሞክራቶች 45 በመቶ ለሪፕብሊካን ድጋፍ የሰጠ ኩባንያ ለማግባባት ከ6 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ አድርጓል። በዚህ ኩባንያ ውስጥ የአክሲዮን ድርሻ ያላቸው አባላት ይገኙበታል።
3. BAE Systems (U.S./United Kingdom)
ይህ የአሜሪካና የእንግሊዝ የጦር መሳሪያ አምራች ድርጅት እ.ኤ.አ. ከ2013 እስከ 2014 አጠቃላይ ሽያጩ 26 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ከዚህ ውስጥ የተጣራ ሽያጩ 275 ሚሊዮን ዶላር ነበር። በ2004 ምርጫ ከ1 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለማግባቢያ ወጪ አድርጓል።
2. Boeing (U.S.)
ይህ የአሜሪካ የጦር መሳሪያ አምራች ድርጅት እ.ኤ.አ. ከ2013 እስከ 2014 አጠቃላይ ሽያጩ 30 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ከዚህ ውስጥ የተጣራ ሽያጩ 4 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ነበር። ኩባንያው የአሜሪካ ኮንግረስ ለመከላከያ የሚመድበውን ውጪ በጣም እንዲንር ከፍተኛ የማግባባት ስራ ከሚሰሩ አንዱ ሲሆን ከአሜሪካ ኢምፖርት ኤክስፖርት የጋራንቲ ቦንድ ከፍተኛም ተጠቃሚ ነው። በ2004 ምርጫ ዘመቻ ላይ 16 ሚሊዮን ዶላር ድረስ ወጪ ማድረግ የቻለ ኩባንያ መሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ። 17 የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ከኩባንያው የአክሲዮን ድርሻ አላቸው።
1. Lockheed Martin (U.S.)
ይህ የአሜሪካ የጦር መሳሪያ አምራች ድርጅት እ.ኤ.አ. ከ2013 እስከ 2014 አጠቃላይ ሽያጩ 35 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ከዚህ ውስጥ የተጣራ ሽያጩ 3 ቢሊዮን ዶላር ነበር። ይህ ኩባንያ ኤፍ-16 ተዋጊ ጀቶችን እና ከመሬት ከባህር ላይ የሚወነጨፉ ሚሳኤሎችንም ያመርታል። በ2001 በዓለም ታሪክ ከፍተኛ የተባለለትን የመከላከያ ኮንትራት የወሰደ መሆኑም ይነገርለታል። ለምርጫ ዘመቻ የሚመድበውን ገንዘብ ለሁለቱ የአሜሪካ ፓርቲዎች እኩል ሃምሳ ሃምሳ ያካፍላቸዋል። ኩባንያው ከሚያመርተው የጦር መሳሪያዎች የመከላከያ ቁሶች ሰማንያ በመቶ የሚሆነውን አመታዊ ሽያጭ ለናሳ እና ለአሜሪካ መከላከያ ነው የሚፈጽመው። በ2014 በአሜሪካን በተደረገው የምርጫ ዘመቻ ላይ ከ14 ሚሊዮብ ዶላር በላይ ወጪ ማድረጉ መረጃዎች ያሳያሉ።
በአጠቃላይ እነዚህ አስር ኩባንያዎች ብቻቸውን 210 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ አጠቃላይ ሽያጭ ፈጽመዋል። ጦርነት ለእነዚህ ኩባንያዎች ምን አይነት ትርጉም ሊኖረው እንደሚችል መገመት የሮኬት ሳይንስ አይደለም። ጦርነት በዚህ ምድር ላይ ከሌለ የእነዚህ ኩባንያዎች እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል? ጦርነት ቢጠፋ ጦርነት ይፈጥራሉ። ዓለም በማያባራ ነውጥ ውስጥ ትቀጥላለች። አትራፊዎቹ እነሱ፤ ሞቾቹ ሌሎች እንደሆኑ ቀጥለዋል።
Watch Ethiopian movies legally. Upto 5 movies added daily. Here are the top 10 most viewed movies today.
Receive Ethiopian News, Movies and Videos by email. Sign up for Email alerts ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን፣ ጠቃሚ ምክሮችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜሎን ያስመዘግቡ።