ከስሜታዊነት የጸዱ በሳል ወጣቶች ለለውጡ በብዛት ማፍራት ይጠበቅብናል:: - ምንሊክ ሳልሳዊ
ተቀምጦ ከማላዘን – የወሬ ትውልድ ከመቀፍቀፍ – የስሜት ናዳ ዶፍ ከማዝነብ – ብሎም በባዶ ሜዳ ስንፍናን ከማዛጋት ይሰውረን:: ኢትዮጵያችን አፈና የተንሰራፋባት.. ጭቆና የነገሰባት አገር … ነፃነት በእጅጉ የተሸረሸረባት አገር ከሆነች አመታቶች ተቆጠሩ::ወያኔ ህዝቦች የምንመኘውን ያላሟላ የዜጎችን ነፃነት ማክበር ሸክም ሆኖ የሚያስብ ቢያንስ ቢያንስ በታጋሽነትና በመቻቻል መንፈስ ትችቶችን ለማስተናገድ በቂ ችሎታ እና ዝግጁነት የሌለው አምባገነንነት ከተቃዋሚ ፓርቲዎችና ከተቀናቃኝ ፖለቲከኞች የሚሰነዘሩ ወቀሳዎችን እና የዜጎችን አቤቱታና የምሁራንን ትችት ለመስማት ተግስት የሌለው በጣም አሳሳቢ ነው። ወያኔ ከዚህና ከዚያ አንድ ሁለት ትችት ብቅ ብቅ ሲሉ ይበረግጋል። አሸባሪ ብለው ለመፈረጅ የሚቸኩሉም ባለስልጣናት እና ካድሬዎች ጥቂት አይደሉም።በሃሳብ የተለዩትን ሁሉ መወንጀልም ቀላል እየሆነ ነው።የዚህ ሰላባ የሆኑት በአብዛኛው ወጣቶች ናቸው::
ለሃገራዊ እና ህዝባዊ አጀንዳ አንዳችም ልዩና መሰረታዊ ዓላማ ከጀርባው ሳይኖር ወዳጅነትን መፍጠር መባረክ ነው፡፡ ለሀገር ለወገን የሚበጅ እፁብ ነገር ነው፡፡ ስብዕና፣ ዕውቀት፣ ምጥቀተ-ህሊና፣ የጋራ-ቤትን ማፍቀር፤ መሰረታዊ መነሻዎችና ማደጊያዎች ናቸው፡፡ በተለይ ወጣቱ ከመሰረት ከንጣፉ እኒህን ጉዳዮች ማወቅና መገንዘብ መቻሉ ደርዝ ያለው ነገር ነው፡፡ መተሳሰብ፤ መወያየት፣ ማንበብና መናበብ፣ በሥርዓት መኖር፤ የጋራ ምጥቀተ-ህሊና ያስፈልገዋል;የሀገራዊነት መሰረቱ ይሄው ነውና::ይህ ሃገራዊ መሰረት በወጣቱ ውስጥ እንዳይኖር ወያኔ በመሰሪ ተግባሩ እየሸረሸረው ነው::ወጣቱ ለትምህርት ዝግጁ እንዳይሆን ለመንቃት እንዳይተጋ ስለሃገሩ ያገባኛል እንዳይል ራሱን ምንጊዜም ለመለወጥ እንዳይታታር አርቆ ማስተዋል ጐዳና ላይ እንዳይወጣ በስፋት በወያነ እየተሰራ ነው፡፡ በእርግጥ አገር ተረካቢ ትውልድ እንዳይፈጠር ወያኔ በአንድ ለአምስት ስም ከቤተሰብ ጀምሮ በመማሪያ ተቋማት እና በህብረተሰቡ ውስጥ ዕጁን አስገብቶ ወጣቱ ለአካለሥራ መብቃት ጋር እንዳይበቃ እና ከዘመኑ ስልጣኔ ጋር እንዳይተሳሰር እኩይ ስራዎችን በመስራት ደፋ ወና እያለ ማህበራዊ ዝቅጠት በመፍጠር ይህንን ጥሰው ያለፉትን በማሰር ተግባራት ላይ ተሰማርቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት ለተያዘው ትግል ዋና ተሳታፊ እና ትልቅ ስራ ሊሰራ የሚችለው ወጣቱ ነው::ወጣቶች ስሜታዊ እና ያለፉትን አቀንቃኞች የሚከተሉ እንዳይሆኑ በነጻነት ሃሳባቸውን እንዲገልጹ እንዲበስሉ ማበረታታት ግድ ይለናል::በስፋት እና በግንባር ቀደምትነት ወጣቱን ያላሳተፈ ተግባራዊ ስራ እሰራለሁ አሊያም ወጣቱን ተጠቅሜ ወደ ስልጣን እመጣለው የሚለው ሃሳብ ጊዜ ያለፈበት እንደሆነ በማወቅ ወጣቱ በአገር ጉዳይ ላይ ግቡን የሚመታ እና የሚሳተፍበት ሃገሩን የሚመራበት መንገድ ውስጥ ማስገባት ችላ ሊባል የሚገባው ጉዳይ አይደለም::የዕውር የድንብር አለመሄድ ትልቁ ጥበብ ነው፡፡ ወጣቱ ህይወትን የሚቃኝበት ኮምፓስ ያሻዋል፡፡ ሌሎችን የሚማርክበት ማግኔት ያለው እንዲሆንም እንጠብቃለን፡፡ በዚህ የመረጃ ዘመን መረጃ – የለሽ ትውልድ እንዳይፈጠር ሁሉም ዜጋ አስተዋፅዖ ሊያደርግ ይገባል፡፡እያንዳንዳችን በሰፋት ከቀድሞ በበለጠ የወጣቱን ዐይን ልንከፍትለት ይገባል::እንዲያው በደፈናው ትውልድን መራገም ማብቃት ይኖርበታል፡፡ተቀምጠን ከምናላዝን ተንቀሳቅሰን ለነገ ለውጥ እናምጣ ነው ጉዳዩ::