የወንድ ሕፃን ልጅ ግርዛት መብት ወይስ የመብት ጥሰት? Is circumcision of male infants a violation of human rights?
ተጻፈ በ ጌታሁን ወርቁየሰብዓዊ መብት ሰዎች ሰው በመሆናቸው በተፈጥሮ የሚያገኙዋቸው መብቶች ናቸው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰብዓዊ መብቶች ከዳበሩበት ዘመን ጀምሮ በብዙ አገሮች ዕውቅና አግኝተዋል፡፡
የዕውቅናው መጠን ግን በአገሮች መካከል የአመለካከትና የአፈጻጸም ልዩነት መኖሩ ሰብዓዊ መብት በተመሳሳይነትና በወጥነት እንዳይከበሩ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ እስካሁን ከታወቁት ልዩነት ታሪካዊው፣ ዋናውና አንዱ ከባህል አንፃር የሰብዓዊ መብትን ምንነትና ወሰን በመረዳት የሚታየው ልዩነት ነው፡፡ አገሮች በአንድ በኩል ሰብዓዊ መብቶች ለሁሉም ሰው በእኩል የተሰጡ በመሆናቸው ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ የኅብረተሰቦች ልዩነት ተፅዕኖ ሊያደርግባቸው እንደማይገባ ይገልጻሉ፡፡ በተለይ ምዕራባውያን በተባበሩት መንግሥታት ደረጃ የወጡት የሰብዓዊ መብት ሰነዶች የሁሉም የሰው ልጆችን መሠረታዊ መብቶች የያዙ በመሆናቸው በሁሉም አገሮች በወጥነት ተፈጻሚ ሊሆኑ እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡ አፍሪካን ጨምሮ በሌሎቹ ክፍለ ዓለማት ያሉ የሰብዓዊ መብት ምሁራን አስተሳሰቡን የሚደግፉ ቢሆንም፣ ሰብዓዊ መብት በባህልና ሃይማኖት አፈጻጸሙ ሊለያይ እንደሚችል የሚገልጹ ምሁራኖችም አሏቸው፡፡ እነዚህ አካሎች ሰብዓዊ መብት ባህልና ሃይማኖትን የዘነጋ፣ የአንዲት አገር ባህል ከሌላው የተሻለ የሚያስመስል መሆን ስለሌለበት አረዳዱና አፈጻጸሙ ባህልንም ያገናዘበ ሊሆን ይገባል ይላሉ፡፡ በዚህ ረገድ የአስተሳሰብ ልዩነቱ መገለጫዎች አሉ፡፡ ውርጃ፣ የሞት ቅጣት፣ በጋብቻ ላይ ጋብቻ፣ በስቃይ ላይ ያለን ሰው እንዲሞት መርዳት፣ ሕፃናትን መቅጣት ወዘተ አሁንም ባህልን ወይም ሃይማኖትን መሠረት ባደረገ መልኩ በአገሮች መካከል የአቋም ልዩነት የሚታይባቸውና ሁሉንም የተባበሩት መንግሥታት አባል አገሮችን በወጥነት ያላስማሙ ናቸው፡፡
በዚህ ጽሑፍ የምንመለከተው የወንድ ሕፃን ልጅ ግርዛትም በዚህ ምድብ የሚወድቅ ነው፡፡ ከሴቶች ግርዛት በተለየ የወንድ ልጅ ግርዛትን በተመለከተ ምሁራን ተመሳሳይ አቋም ሲይዙ አይስተዋልም፡፡ የሴት ልጅ ግርዛት የሴቶችን መሠረታዊ መብቶች የሚጥስ ጎጅ ልማድ እንደሆነ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶችና ኦፊሴላዊ ትርጉሞች በተመሳሳይ መልኩ ተቀብለውታል፡፡ የአገራችን ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 35 የሴት ልጅ ግርዛትን የመሰሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የሴቶችን መብት የሚጥሱ መሆናቸውን ከመግለጽ ባለፈ፣ የወንጀል ሕጉ የሴት ልጅ ግርዛትን የተለያዩ አፈጻጸሞችን የሚቀጡ ድንጋጌዎችን አካትቷል፡፡ የወንድ ልጅ ግርዛትን በተመለከተ ግን ዓለም አቀፍ ስምምነቶችም ሆነ በብዙ አገሮች ብሔራዊ ሕግጋት በግልጽ የሚባል ነገር የለም፡፡ በዚህ የተነሳም ጸሐፊያንና ምሁራን የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችን በመተርጎም የድጋፍ ወይም የተቃውሞ ሐሳባቸውን ያንፀባርቃሉ፡፡ በዚህ ጽሑፍ የወንድ ልጅ ግርዛት በተለይ በሕፃናት ላይ የሚፈጸምበትን ምክንያቶች በመግለጽ፣ በግራ ቀኙ ከመብት አንፃር የሚነሱ ሙግቶችን ለማሳየት ጥረት እናደርጋለን፡፡ በአገራችን ወንድ ሕፃናትን መግረዝ ሃይማኖታዊና ሃይማኖታዊ ያልሆኑ አመክንዮ ያለው ሲሆን፣ በሕጋዊነት በሆስፒታሎችም ሆነ በየቤቱ ስለሚፈጸም በጽሑፉ የሚገለጸው የግራ ቀኝ ሙግት ዓለም አቀፍ መብት ተኮር የአመለካከት ልዩነትን ለማሳየት ካልሆነ ተግባራዊ ረብ ላይኖረው ይችላል፡፡
ታሪክና አመክንዮ
የወንድ ልጅ ግርዛት በታሪክ ከቀደሙት የቀዶ ሕክምና ሥርዓቶች ምድብ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በዓለም ደረጃ በብዛት (1/5ኛው የዓለም ክፍል) የወንድ ልጅ ግርዛት እንዲሚፈጸም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ግርዛቱ በአብዛኛው የሚፈጸመው በሃይማኖት አመክንኖ መነሻነት ሲሆን፣ በተወሰኑት ደግሞ በተለይ በምዕራባውያን ከጤና ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ይፈጸማል፡፡ የተለያዩ የወንድ ልጅ ግርዛት ዓይነቶች መኖራቸው በአንዳንድ መጻሕፍት የተመለከተ ቢሆንም፣ በአብዛኛው የተለመደው የወንድን ልጅ የብልት ሽለፈት በሕፃንነት የማንሳት አነስተኛው ግርዛት (Routine Circumcision) ነው፡፡ በአብዛኛው ግርዛት ሲፈጸም ሐኪሞች ማደንዘዣ የማይጠቀሙ ሲሆን፣ ግርዛቱ በሕፃኑ ላይ ምንም ወይም እጅግ አነስተኛ ችግር እንደሚያስከትል ይነገራል፡፡ በግልጽ የታወቁት ተፈጥሮዓዊ የግርዛት ውጤቶች (ችግሮች) የደም መፍሰስ፣ አልፎ አልፎ ኢንፌክሽንና የሥነ ልቦና ችግሮች ናቸው፡፡
የወንድ ልጅ ግርዛት ሃይማኖታዊ ወይም ሃይማኖታዊ ያልሆነ አመክንዮ ሊኖረው ይችላል፡፡ ሃይማኖታዊ አመክንዮው የሕፃኑ ወላጆች የእምነታቸው አንድ ግዴታ አድርገው የሚፈጽሙት ሲሆን በአይሁዳ፣ በክርስቲያኖችና በሙስሊሞች የተለመደ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለአብርሃም ቃል ኪዳን የገባለት በመገረዝ በመሆኑ አይሁዶችና የብሉይ ኪዳን ተከታዮች የወንድ ልጅ ግርዛትን ይፈጽማሉ፡፡ ግርዛቱ ሕፃኑ በተወለደ በስምንተኛ ቀኑ የሚፈጸም ሲሆን፣ ራሱን የቻለም ሥርዓት አለው፡፡ በክርስቲያኖች ተጠቃሽ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ በሰባተኛው ቀን የመገረዙ ነገር ሲሆን፣ ክርስቶስ የብሉይን ሕግ ለመፈጸም ያከናወነው ስለመሆኑ በክርስቲያኖች ይታመናል፡፡ ክርስቲያኖች መገረዝን የሚፈጽሙት የብሉይ ኪዳን ትዕዛዝን ከማክበር አንፃር ካልሆነ ከሕዝብና አህዛብ ልዩነት ጋር የተያያዘ አይደለም፡፡ በሐዲስ ኪዳን ተጽፎ እንደሚታየው መገረዝ አለመገረዝ ከማመን ካለማመን፣ ከመጠመቅ ካለመጠመቅ፣ ከመጽደቅ ካለመጽደቅ ጋር የሚያያዝ አይደለም፡፡ በሙስሊም ሃይማኖትም የወንድ ልጅ ግርዛት የተለመደ ሲሆን፣ ወንድ ሕፃናት ዕድሜያቸው ከአራት እስከ 13 ዓመት በሚሆንበት ጊዜ ይፈጽሙታል፡፡ ቁርዓን ግልጽ ድንጋጌ በወንድ ልጅ ግርዛት ላይ ባይኖረውም በሱና (በነብዩ ንግግርና ድርጊት) ወንዶች ሊፈጽሙት የሚገባ ሥርዓት መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ከሃይማኖታዊ ምክንያቶች ውጪ የተለያዩ አመክንዮዎች ለወንድ ልጅ ግርዛት ሲነሳ ይታያል፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ የወንድ ልጅ ግርዛት ወንዶች ግለ ወሲብ በመፈጸም ለዓይነ ስውርነትና የአዕምሮ ጤና መጓደል እንዳይጠቁ ግርዛቱ አስፈላጊ እንደነበር ይነገራል፡፡ አደገኛ የአልኮል ፍላጎትን ለመግዛት፣ ለአስምና ለራስ ምታትም ጥቅም እንዳለው የሚነገርበት ጊዜም ነበር፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የተለመዱት አመክንዮች የወንድ ልጅ ግርዛት ለግል ንጽህና፣ በወሲብ ምክንያት የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል፣ ከብልት ካንሰር ለመጠበቅ፣ የኤችአይቪ ተጠቂነትን ለመቀነስ ጠቃሚ መሆኑ ይነገራል፡፡ ሆኖም የወንድ ልጅ ግርዛትን የተመለከቱ የሕክምና ነክ አመክንዮዎች አሁንም ድረስ አከራካሪ እንደሆኑ ቀጥለዋል፡፡ የወንድ ልጅ ግርዛት ጥቅሞችን አንዱ ሲገልጽ ሌላው ሲያስተባብል፤ እንደገና ሌላው ደግሞ ሌላ ምክንያት ሲያቀርብ እስካሁን ሙግቱ ቀጥሏል፡፡ በአገራችን ግን የወንድ ልጅ ግርዛትን በተመለከተ የሕክምና ሙግትም ሆነ የአመክንዮ ልዩነት በአደባባይ ሲንፀባረቅ አይስተዋልም፡፡ ኅብረተሰባችንም በአብዛኛው ከሃይማኖት፣ ከባህል ወይም በጤና ምክንያት ልጆቹን እያስገረዘ ይኖራል፡፡
ግርዛት ከሰብዓዊ መብት አንፃር

ከሰብዓዊ መብት አንፃር በወንድ ልጅ ግርዛት ላይ የሚንፀባረቁ አስተሳሰቦች ሁለት ዓይነት ናቸው፡፡ አንዳንዱ ከጤንነትና ከሃይማኖት ምክንያት አንፃር ግርዛት የሚደግፉ ሲሆኑ፣ ሌሎቹ ደግሞ ከሰብዓዊ መብትና ከአካል ደኅንነት መብት አንፃር ግርዛትን ይቃወማሉ፡፡
ግርዛትን የሚቃወሙ ወገኖች የሕፃናት መብት ኮንቬንሽንን መሠረት በማድረግ ልክ እንደ ሴት ልጅ ግርዛት ሁሉ የወንድ ልጅ ግርዛት ጎጅ ልማዳዊ ድርጊት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ድርጊቱ በሕፃናት ላይ የሚፈጸም ጥቃት ሲሆን፣ ያልታሰበ የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት ያስከትልበታል ይላሉ፡፡ የግርዛት አፈጻጸም ያለ ማደንዘዣ መሆኑ ግርዛት በሕፃኑ ላይ የሚፈጸም ቶርቸርና አሰቃቂ ተግባር ነው ሲሉ ይገልጹታል፡፡ በተጨማሪም ሕፃኑ እንደማንኛውም ሰው የግላዊነት መብት (Right to Privacy) ያለው ቢሆንም ፈቃድ ሊሰጥ በማይችልበት የሚፈጸመው ግርዛት ግላዊነትን እንደሚጥስ አንዳንዶች ይገልጻሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች አቋማቸውን ለማጠናከር የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት መግለጫ አንቀጽ 5 (ከቶርቸር መጠበቅ)፣ አንቀጽ 12 (የግላዊነት መብት)፣ አንቀጽ 3 (የአካል ደኅንነት መብት) ሲጠቅሱ ይስተዋላሉ፡፡ በሌላ በኩል ይህን ሐሳብ የሚደግፉ ወገኖች በሴቶች ላይ የሚፈጸም ግርዛትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት አድርጎ የወንዶችን ግርዛት ጥሰት አለማድረግ መሠረታዊውን የእኩልነት መብት ይጥሳል ሲሉ ይከራከራሉ፡፡
ግርዛትን የሚተገብሩ ወገኖች በበኩላቸው ግርዛት በሕፃናት ላይ የሚፈጸም ጥቃት ነው ተብሎ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች አስፈጻሚ ተቋማት በኦፊሴል ያልተገለጸ በመሆኑ፣ ተቃዋሚዎች የሚያቀርቡት ክርክር ምናባዊ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በሌላ በኩል በሕፃናት መብት ኮንቬንሽን ሕፃናትን በልማዳቸውና ባህላቸው ዐውድ የማሳደግ መብት የወላጆች ስለመሆኑ ተመልክቷል ይላሉ፡፡ ወላጆች ሕፃናትን በራሳቸው ባህል ሲያሳድጉ ለሕፃኑ ጠቃሚ የሆኑ ውሳኔዎችን ከመንግሥት ተፅዕኖ ውጪ የመወሰን መብት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ወላጆች ሕፃናትን የሚያስገርዙት ሕፃኑን ለመጉዳት በማሰብ አለመሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የወላጆቹ ድርጊት ‘ጥቃት’ ነው የሚያስብል ሳይሆን ለሕፃኑ ጥቅም የሚፈጸም፣ በሃይማኖትና በጤና የሚመከር በመሆኑ ነው ሲሉ ክርክራቸውን ያጠናክራሉ፡፡ ግርዛት የማይፈጽሙ አካላት ግርዛት የመፈጸም ባህል ባለባቸው አገሮች ላይ አቋማቸውን መጫን ተገቢ እንዳልሆነ በመግለጽ ክርክሩ የሰብዓዊ መብትና የባህል ግጭት (Universalism vs Culture relativism) አካል አድርገው የሚመለከቱትም አልጠፉም፡፡ ግርዛትን በሃይማኖት አመክንዮ ለሚፈጽሙት ደግሞ ግርዛት የሃይማኖት ነፃነት መገለጫ በመሆኑ መከልከል የሃይማኖትን መብት መግፋት እንደሚሆን የሚገልጹ አሉ፡፡
የወንድ ልጅ ግርዛት መብት ወይስ የመብት ጥሰት የሚለው ጭብጥ አሁን አሁን እያከራከረ የሚገኝ የሰብዓዊ መብት ጥያቄ ሆኗል፡፡ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶችን በመቅረፅና ይዘቱን በመወሰን ሰፊ ድርሻ የነበራቸው ምዕራባውያኑ አሁን አሁን የሕፃን ልጅ ግርዛት በሴትም ይፈጸም በወንድ ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ግርዛትን ለአንዱ ፆታ ከልክሎ ለአንዱ መፍቀድ ተገቢ አይደለም፣ የሕፃኑን ብልት ተፈጥሮ በሰጠችው መልኩ አካለ መጠን ደርሶ ራሱ እስከሚወስን ልንጠብቅለት ይገባል ይላሉ፡፡ ለግርዛት መነሻ የሚሆኑ ምክንያት ሃይማኖትም ቢሆን የሕፃኑን የአካል ደኅንነት፣ ግላዊነትና ከጥቃት ነፃ የመሆን መብትን ባከበረ መልኩ ሊከናወን ይገባል፤ ከግል ንጽህናም አንፃር የሕፃኑን አካል በመቁረጥ ሳይሆን በማፅዳትና ካደገም እንዲያፀዳ በማስተማር ልንጠብቅለት ይገባል ይላሉ፡፡
አገሮች የወንድ ልጅ ግርዛትን በአብዛኛው የሚፈቅዱ ሲሆን፣ አንዳንዶችም ሕፃኑ ፈቃዱን ለመግለጽ በሚችልበት ዕድሜ እንዲፈጸም ያስገድዳሉ፡፡ የግርዛት ነገር አንዳንድ ጊዜም ከፖለቲካና ከሃይማኖት መብት ጥያቄ አንፃር የሚታይበትም ጊዜ አለ፡፡ ለምሳሌ ጀርመን ከሁለት ዓመታት በፊት የወንድ ልጅ ግርዛትን የሚፈቅድ ሕግ ስታወጣ ግንዛቤ ውስጥ የገባው ዋና ነጥብ የአይሁዶችና የሙስሊሞች የሃይማኖት ልማድ እንደነበር ተዘግቧል፡፡ በጊዜው እነዚህን ተፅዕኖ ፈጣሪ ቡድኖች ፍላጎት ለመጠበቅ አቋሙ መያዙ ተዘግቧል፡፡ በዚህም ምዕራባውያኑ ሁለት መስፈርት (Double Standard) ይከተላሉ፣ በአንድ በኩል የሴት ልጅ ግርዛትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው ሲሉ፤ በሌላ በኩል የወንድ ልጅ ግርዛት የሕፃናትን የአካል ደኅንነት፣ የግላዊነትና ከቶርቸር የመጠበቅ መብት የሚጥስ መሆኑን ቢያምኑም ፀረ አይሁድ (Anti-semetic) አቋም ላለማንፀባረቅ ከማውገዝ ይቆጠባሉ በሚል ትችት ይደርስባቸዋል፡፡ ምዕራባውያኑ የሴት ልጅ ግርዛትን ያህል የወንድ ልጅ ግርዛት ላይ የያዙት አቋም ከሰብዓዊ መብት አንፃር የሚይዙት አቋም ቁርጠኝነት ላይ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ከሰብዓዊ መብት ጥያቄው በተሻለ በወንድ ሕፃን ልጅ ግርዛት ላይ የሚነሳውን ተቃውሞ ተቀባይነት ሊያጠናክር የሚችለው የሕክምና ሙያ ዕርዳታው (Intervention) ከሰፋና በእርግጠኝነት ላይ ከተመሠረተ ነው፡፡ የሕክምና ሳይንሱ የወንድ ልጅ ግርዛት ከጤናና ከዘላቂ የሥነ ልቦና ችግር አንፃር ያለውን ችግር አሳማኝ በሆነ መረጃ እስካላረጋገጠው ድረስ የወንድ ልጅ ግርዛት ላይ የሚደረግ ሙግት መደምደሚያ አይገኝለትም፡፡
የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ደግሞ ከዚህ እጅጉን የተለየ ነው፡፡ መገረዝ መብትና አለመገረዝም አሳፋሪ የሚሆንበት ልማድ ይበዛል፡፡ በሃይማኖትም ሆነ በጤና አመክንዮ ኅብረተሰቡ ሕፃን ወንድ ልጁን ያስገርዛል፣ አለመገረዝ አማራጭም አይደለም፡፡ በተግባርም ሕፃናት ተገርዘው ጤነኛ ሲሆኑ ምንም የጤና ችግር (ምናልባትም የሥነ ልቦናም ጭምር) ሳይኖርባቸው ስለሚታዩ መገረዝን የሚቃወም ሐሳብ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ፍትሐ ነገሥት በአንድ ወቅት ሕጉ ለነበረ፣ ብሉይ ኪዳናዊ ልማዶችን አሁንም ለሚተገብር፣ የኅብረተሰቡ ዋና እምነቶች በሚባሉቱ ድጋፍ ያለው የወንድ ልጅ ግርዛት ያለምንም መጠይቅና ተግዳሮት መፈጸሙን መቀጠሉ በአገራችን አያስደንቅም፡፡ ሕገ መንግሥቱም ሲረቀቅ ሆነ የወንጀል ሕጉ ሲቀረፅ ሐሳቡ አለመነሳቱ በዚህ ጽሑፍ ያነሳናቸው የፈቃድ፣ የግላዊነት፣ ወዘተ ሕገ መንግሥታዊ ክርክሮች በአገራችን ምናባዊ ሆነው መቅረታቸው አይቀርም፡፡ የወንጀል ሕጉ የሴት ልጅ ግርዛትን ‹‹ጎጂ ባህላዊ ድርጊቶች›› በሚል ወንጀል አድርጎ ቅጣት ሲደነግግ የወንድ ልጅ ግርዛትን በተመለከተ ዝምታን መምረጡ ሕጋዊነቱን፣ ለክርክርም የተጋለጠ አለመሆኑን ሲያጠይቅ (ሲመሰክር) ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የወንድ ሕፃን ልጅ ግርዛት በምዕራባውያኑ መልስ ያላገኙ የሰብዓዊ መብት ሙግት ሲሆን፣ በአንዳንድ አገሮች አገራችንን ጨምሮ ደግሞ መብት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ወደ ፊት አንድ ቀን የሰብዓዊ መብት ሙግት ባስነሳ ጊዜ ግን የሕግና የሰብዓዊ መብት ምሁራኖቻችን እንደሚሟገቱበት ተስፋ እናደርጋለን፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕግ ጠበቃና አማካሪ ሲሆኑ፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡
Watch Ethiopian movies legally. Upto 5 movies added daily. Here are the top 10 most viewed movies today.
Receive Ethiopian News, Movies and Videos by email. Sign up for Email alerts ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን፣ ጠቃሚ ምክሮችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜሎን ያስመዘግቡ።
