###እንደፈለጉ አርገው ይጨርሱት……..!!!!###

###እንደፈለጉ አድርገው ይጨርሱት……..!!!!###

እናንተዬ ሳንወድ በግድ እኮ ሰላምታችንን ቀየሩት!

ድሮ፦ እንዴት ነህ? ሰላም ነህ? ሁሉ ነገር ሰላም? ነበር ሰላምታችን፡፡

አሁን፦ እንዴት ነህ? ሰላም ነህ? ጆሮህን ተሻለህ? ሆነና አረፈው፡፡ እንዴ የድፍን ኢትዮጲያን ጆሮ እኮ አደሙት፡፡ የጉድ ዘመን ቢሆንም አይደል፡፡

በነገራችን ላይ እነ እንበጣጠስ ራሳቸውን እየቀረፁ የሚለቋቸውን ቪዲዮዎች ከማየቴ በፊት ዘረኝነትና መልከ ጥፉነት የሚገናኙ አይመስለኝም ነበር፡፡ ለካስ አበልጃሞች ኖረው!!! ኧረ ቀልዴን ነው አትሳቁ!!! እምላችሁ ግን ከቀረፃ በፊት ቢያንስ ቢያንስ ፊትን መታጠብ ፣ አይነ እዳሪን ማስለቀቅ፣ ቢጠፋ ቢጠፋ ባዝሊን መቀባት “ምን አይነት አመዳም ነዉ” ከመባል ያተርፋላ፡፡ ከፍትፍቱ ፊቱ አይደል የሚባለው፡፡ ነገሩማ ብልሹ ምግባር እፁብ የተባለውን መልክ እንኳን ይጋርደውም የል!! እናላችሁ እነዚህ “እስከዚም ፊቶች” የኔንም ጆሮ አደሙት፡፡ እግዜር ይስጣቸው ነገሩ <ልቦና ማለቴ ነው> ያልሰለጠነ አመለካከትና የሰለጠነ ቴክኖሎጂ ሲገናኙ ምን እንደሚመስል ቁልጭ አርገው አሳዩን፡፡ በእውነቱ ከሆነ የቤታቸውን አጥር አስታከው ካልተገነጠልን ከሚሉ ሰዎች ከዚህ በላይ መጠበቅ የዋህነት ነዉ፡፡

እናማ እነ “እስከዚም ፊቶች” ሰምቶ አደር ጆሮዬን አደሙት፡፡ እኔም የደማውን ጆሮዬን ለማስታመም ብእሬን አነሳሁ፡፡ አንስቼም ከበድ ብላ አጠር ባለች ቃል ተቃውሞዬን ላሰማ አሻሁና ብዙ አሰብኩ፡፡ አውጥቼ አውርጄም “ዘረኛ መሆን እኮ… ” ብዬ ፃፍኩኝ፡፡ በርግጥ በሶስቱ ነጥቦች ውስጥ ያሉትን ቃላት በልቤ የጨረስኳቸው ቢሆንም በፅሁፍ ለማስፈር ግን አይመጥኑም ብዬ በሶስት ነጥቦች ቀየርኳቸው፡፡ ይህች የፃፍኳት ቁንፅል ፅሁፍ ልቤን አስደሰተችው፣ ጆሮዬንም አከመችልኝ፡፡ ከዛም ድል አድራጊነት ነገር አይነት ስሜት እየተሰማኝ ወደ አልጋዬ ሄጄ ተንጋለልኩ፡፡

………ግን ብዙም ሳይቆይ “እስከዚም ፊቶቹ” ጅምሩ ፅሁፌ ላይ “ብርቃችን አይደለም” ብለው ቢጨርሱትስ የሚል ሀሳብ ገባኝና ወዲያው የጆሮ ህመሜ አገረሸ፡፡ ከዛማ በቃ ሀረግ የነበረውን ፅሁፌን አረፍተ ነገር ለማድረግ በድጋሚ ብዕሬን አነሳው፡፡

ሙከራ አንድ

“ዘረኛ መሆን እኮ የስልጣኔ ምልክት አይደለም” ብዬ ፃፍኩ ደጋግሜ ሳነበው የሆነ የምርጫ ቅስቀሳ መፈክር አይነት ነገር መስሎ ስለተሰማኝ ተውኩት፡፡

ሙከራ ሁለት

“ዘረኛ መሆን እኮ የ እከሌ ልጅ አያስብልም” ብዬ ከተብኩ፡፡ ይሄ ደግሞ የሆነ “የቤተሰብዎ ደስታ በእጆ ነው” አይነት የ dkt ማስታወቂያ ይመስላል፡፡ ስለዚህ ሌላ…..

ሙከራ ሶስት

“ዘረኛ መሆን እኮ………………………..” ምን ብዬ እንደምፅፍ ግራ ገባኝ፡፡ “ዘር” የሚለው ቃል ያለበት አረፍተ ነገር መስራት እጅግ በጣም ከባድ እንደሆነ ያወኩት 2ተኛ ክፍል እያለው ነው፡፡ ወ/ሮ አልማዝ ማስረሻ “ዘር ማንዘር” በሚለው ቃል አረፍተነገር ስራ ብለው ጉድ አፈሉ፡፡ ወ/ሮ አልማዝ ማስረሻ የአማርኛ መምህሬ ናቸው፡፡ እኔም ብዙ አስቤ በላብ ከተጠመኩ በኃላ “አበበ ዘርማንዘር አከማቸ” ብዬ ከመጨረሴ የወ/ሮ አልማዝ በጠመኔ የነጡ አለንጋ ጣቶች መንገጭላዬ ላይ ብለው እመሬት ዘረሩኝ፡፡ ወ/ሮ አልማዝ ከጥፊው በተጨማሪ የሳቸው ክፍለ ጊዜ እስኪያልቅ ድረስ ፊቴን ወደ ጥቁር ሰሌዳው አዙሬ እንድንበረከክ አዘዙኝ፡፡ ያኔ ነው ዘር ነክ በሆነ ቃል ላይ የተመሠረተ አረፍተነገር አበላሽቶ መጨረስ እመሬት ሊያዘርር እንደሚችል የተገነዘብኩት፡፡

ታዲያ አሁንም ቢሆን ዘር ነክ የሆነውን አረፍተነገሬን ባለመጨረሴ ሳቢያ ወ/ሮ አልማዝ ማስረሻ አሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው ታሰቡኝና ደነገጥኩ፡፡ ስለዚህም “ዘረኛ መሆን እኮ ጠባብነት ነው” ብዬ ፃፍኩ፡፡ የወ/ሮ አልማዝን ቁጣ ለማብረድ እንጂ የሰራሁት አረፍተነገር “እና ምን ይጠበስ” ለማለት እንደሚጋብዝ ተረድቻለሁ፡፡

ሙከራ አራት

“ዘረኛ መሆን እኮ ……………………..(በረጅሙ አዛግቼ ሰአቴን አየሁ ከለሊቱ 6፡15 ሆኗል) ………….እንዴት እንደምጨርሰው እያሰብኩኝ ነው…………………6፡25 ሆነ………………እስካሁን ሀሳብ አልመጣልኝም……………..6፡40 በድጋሚ አዛጋው …………….አሁንም እብሰለሰላለው……………..6፡50 ሆነ ግን ወፍ የለም…………………7፡03 …. ይችን ይወዳል የሰውየው ልጅ!! የራሳቸው ጉዳይ እንደፈለጉ አድርገው ይጨርሱት፡፡ ወደ አልጋዬ ልመለስ የእንቅልፍም ጡር አለው፡፡

ብቻ እነ “እስከዚም ፊቶች” በህልምህ አይምጡብህ ብላችሁ መርቁኝ፡፡

ኃይላት ነኝ
28 .03 .15