ቡሄ በሉ…

መስቀልብርሃን ከየመን

ዛሬ ማነው ያገር ክብረ-ባህሉ ሲከበር ቀኑን እያወሳ ልቡ ያልሸፈተ? ማን ነው የዓውዳመቶችን ኹካታና ድምቀት በዓይነ ሕሊናው እይሣለ ሆድ ያልባሠው?

ዛሬ ቡሄ ነው የሠፈር እፃናቱ ተሰባስበው ግጥማዊ ዜማቸውን ያወርዳሉ… የነሓሴን ነጭናጫ ዝናብ ድል እየነሱ የዓመት ግብሩን ለማድረስ ”አሲዮ ቤሌማ” ይላሉ።

እዛ ማዶ ነጭ ሻሽ
እዚህ ማዶ ጥቁር ሻሽ
የእኔማ ጌታ ነጭ ለባሽ።

የወንዜው ነብር የወንዜው ነብር
የኛማ ጌታ ሊሰጡን ነበር።

ወዪ ሾህዬ ናና
በሴፊው ጎዳና።

እያሉ ከላይኛው የዱላ ጫፉ ላይ ኮርኪውች በሚስማር ሰክተው እንደ ፅናፅል እያቃጨሉ …ግማሾቹ ጥሩንባ እየነፉ በሰፈሩ ይዞራሉ። ባሕል ነውና የማይሻር የሚያኮራ ማንነት ነውና… ከከተማም ወጣ ያሉ እንድሆን ጅራፍ እያንጧጡ በአስዮ ዜማ ይጨፍራሉ። የተሸለሙትን ሙልሙል ዳቦ በከረጢት ሲያጉሩ የምስጋናው ግጥም ይፈሳል አመታዊ የግጥም ግብሩ …

በፈረስ አፍንጫ አይገባም ትንኝ
የእኔማ እንትና እግዜር ይስጥልኝ።

የወር ፋፋ የወር ፋፋ
የወለዱት ይፋፋ።

እያሉ።

ዛሬ ሰፈሩ በትኩስ የዳቦ ጠረን ታውዶዋል በኮባ ለምለም ቅጠል እንፋሎት መሀዛ ቡሄን ቡሄን ይሸታል …በኩበት ጪስ ደመናው የነሀሴ ግራጫ ኩታውን ተጎናፅፏል።

ችቦም ይበራል ለክረምት ይብቃ ጥሪ …ዕሣትም እየተዞረ ይጨፈራል ለመስከረም ወር ዋዜማ …

ይሄኔ ያበሻ ምድር በቡሄ ደምቃለች እኛም ሕሊናችን ይሸፍታል ዜማው ውስጣችን ያቃጭላል ጭፈራው በዓይናችን ይዞራል የልጅነት ጊዜ ትዝታቶቻችን ወደውሀላ ፈርጥጦ ይተዘታል …እንግዲህ እዚህ ቡሄ የለ ችቦም አናበራም በዱላም የሰው ምድር አንወጋም የተውሶ ነውና። ሙልሙልም አንማፀንም የባሕል ፍቅሩ የሳሳ ነውና …. ኩበትም አናጨስም ”የተበከለን አየር አትበክሉ ” እንባላለንና … ጅራፍም አንወነጭፍ የገመዱ ልጥም የለምና …ዓመት ዓመት ያድረስን ግን እንላለን ለፈዘዘ ዓመት ጊዜው መፈርጠጡ አይቀርምና ….ልጅነታችንን እያወሳን በትዝታ እንጨፍር ትዝታን ይዘን ነው የተሰደድነውና።

ዛሬ ቡሄ ነው

ሥንኝ ልቋጥር ?

እስቲ ቡሄ ቡሄ በሉባይተዋሮች ሁሉ
ልምጭም ባይገኝ-ባሕል ነው እንዲሉ

ጭሥም አናጨስም
ጅራፍም አንገምድም
ሙልሙል አንጠቀልል -ችቦም አናበራም

እንበል አሲዮ እናዚም ትዝታ በልጅነት መዳፍ፣ በእድሜ ገመድ ተርታ ”ወዪ ሾውዬ ና!” ብለን ስቀን ለጨዋታ ጡሩንባም ባይገኝ ኮርኪም ባንመታ፣ እንበል አሲዮ ቢመሽም በማታ ትዝታው አስክሮን ልባችን እየመታ።

ቡሄ ቡሄ በሉ ሠዎች ሁሉ
ትዝታ ብቻ ነው የስደት አመሉ
ቡሄ መጣ
አወይ ጣጣ
ሙልሙል የለ እርምም ይውጣ

ወዪ ሾህዬ
ናና ተው ትዝታዬ
ወደኔ ና
እኔ እንዳልመጣ አንክሻለሁና

ክበር በጤፍ፣ ክበር በጤፍ፣ ተሎጉሟልና የነጭ እሕል ባፍህ

እስቲ እናንተም ስለ ቡሄ ጨማምሩበት፣ ዕለት ክብሩን እናወድሰው …ምንስ ትዝታዎች አሏቹህ?