ዛሬም ሞት ነገም ሞት – በሻብያ እጅ -ከአደፍርስ ተሰማ
በምርኮ እጅ ወደላይ ያሉ ወታደሮችን በመስመር የረሽነው ጨካኙ ሻብያ ከተተኮሰባቸው የጥይት እሩምታ የተረፉትን የደርግ ወታደሮች አፋቸውን እንደ ከብት እየከፈተ የወርቅ ጥርስ ያላቸውን በመልቀም ከረጢቱ ውስጥ እንደከተተ በጊዜው የወጡ የዜና ዘገባዎች ይጠቁማሉ። ሻብያ የኢትዪጵያ ቀንደኛ ጠላት ነው። ዛሬ ለወያኔ ሃገረ ገዥነት ከፍተኛ አስተዋጾ ያደረገው ሻብያ ነው። ያንን ውለታውን ለመክፈል ወያኔም ሳይውል ሳያድር ኤርትራ የምትባል ሃገር ተፈጥራለችና እወቁልኝ በማለት የግንጠላ ስራውን ያስፈጸመው ከላይ ከላይ እየተነፈሰ ነበር። የባህር በር፤ ድንበር ማካለል ለወያኔ ግድ አይሰጠውም። እኔ ከሞትኩ ስርዶ አይብቀል ባይ ነውና! አሁን በኢትዮጵያ ከዝቅተኛ የመንግስት ስልጣን ጀምሮ እስከ ከፍተኛ አመራር በየመስራቤቱ የተሰገሰጉት ወያኔዎች ናቸው። ስልጣን ለመያዝ መማር አያሻም። ዘርና ጎሳን ተገን አርጎ ወያኔን መምሰል እንጂ!
አሁንም እንሆ ሌባ ሲሰርቅ አይጣላም ሲካፈል እንጂ እንዲሉ ዱባ በማያበቅል መሬት ላይ ሻብያና ወያኔ ተፋልመው የአእላፍ ደም ካፈሰሱ በህዋላ ተፋጠው ተቀምጠዋል። አንድ የምዕራብ ዜና አቀባይ በጦርነቱ ወቅት ፍልሚያው የእበደት መሆኑን ለማመላከት “ሁለት መላጣ ሰዎች በማበጠሪያ” እንደሚታገሉ አርጎ ማቅረቡም ትዝ ይለኛል። የሃሳብ መላጦች። ጀግንነታቸው የሚለካው ሰውን በማሰር፤ በመሰወር፤ በመግረፍና በመግደል ብቻ!
እናት ሃገር ኢትዮጵያን ከወያኔ ለማዳን በኤርትራ የተሰባሰቡት ተቃዋሚ ሃይሎች የሚደርስባቸውን ግፍ የተረዳነው ዛሬ አይደለም። ቆይተናል። በጊዜው በተለያዪ መጣጥፍ ለማስጠንቀቅ ሞክረን ሃሳባችን ለህትምት አልበቃም። አሁን ከወደ አስመራ የሚመነጩ ወሬዎች እየከፉ ሲሄድ ነገሮችን በግልጽ ማስታውቅ የግድ ሆነና ተፈቀደልን። ወሬውም አሳዛኝ ነው። አስራሰባት የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንን መረሽን እብደት ነው። ለነገሩ ያበድነው እኛ ነን። ሻብያን አምነን መጠለያ መጠየቃችን። እንዴት ይረሳናል መቶ አመት የሚፈጅ የቤት ስራ እንደተሰጠን በአቶ ኢሳይያስ? ባድሜን ተቀማን ማለት ጀምበር አትጠልቅም ማለት ነው አላሉንም? ስንት ጊዜ ጀምበር ገብታ ወጣች ከሳቸው ጥሩምባ በህዋላ! እንዴት ሰው ሻብያን አምኖ ሃገራዊ ስራ ይጀምራል? በጎናቸው ለሰላሳ አመታት አብረዋቸው ለተንከራተቱ (ጂ 12)ና ነፃ አወጣንህ እያሉ ለሚለፉለት ህዝብ ያልሆኑ የኢትዮጵያን ህልውና መቀበልና ወያኔን የሚጻረሩ ሃይሎችን መደገፍ አይችሉም። ለጊዜአዊ ጥቅማቸው ካልሆነ በስተቀር። አሁን በአስመራ ከተማና በአካባቢው በቁልምጫ ሰማቸው የሚጠሩት ቀዪ መንግስቱ (አቶ ኢሳይያስ) አረመኔ ለመሆናቸው አለም የተቀበለው እውነታ ነው።
አቶ ኢሳይያስ ኢትዮጵያን ከልባቸው ከሚጠሉ ሰዎች መካከል ቀንደኛው ናቸው። ከቀኝ ግዛት ጨቆና ነፃ የወጡበትን ቀን ሲያከብሩ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ሲረግጥ ቆመው ማጨብጨባቸው ለሃገሪቱ ያላቸውን ጊዜ የማይለውጠው ጥላቻ ያረጋግጣል። አጋራቸው ደግሞ በሚኒሊክ ቤተመንግስት ራሳቸውን ካስጠጉ አመታት ቆጥረናል። የምንዋጋው ጥምር ሃይል ነው። ወያኔን በአዲስ አበባ ሻብያን በአስመራ። ከማንም ተጽኖ ነጻ የሆነ ተቃዋሚ ድርጅት በሃገሩ ውስጥ የሚንቀሳቀስ ሻብያንና ወያኔ ደብሎ የሚወጋ ነው። ከዚህ ውጭ የምናረገው ግርግር ሁሉ እሳት የሌለው ጭስ ነው። ቢቀርቡት ከብርድ አያስጥልም። ወያኔና ሻብያም ሃገራዊ አንድነት እንዳይኖር በሚስጢር በጋራ መስራታቸው አያጠራጥርም። የኢትዮጵያን ህልውና በዘርና በጎሳ ለውሰው ለምዝበራ እንዲመቻቸው የተለሙት የጋራ ሴራ ሊረግብ ወይም ከነጭራሹ ሊወገድ የሚችለው ሃገር ወዳድ የሆኑ ተቃዋሚ ሃይሎች በምድራቸው በነፃነት መንቀሳቀስና ማሰብ ሲችሉ ብቻ ነው። የሻቢያና የወያኔ ግባዕተ መሬት ቅርብ ነው። ተስፋ አንቁረጥ!!
አደፍርስ ተሰማ