የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር መጋቢት 20/2007 ዓ.ም ለህዝባዊ ሰልፍ የመረጣቸውን 15 ከተሞች ይፋ አደረገ!

ሰማያዊ ፓርቲ ባህር ዳር ቅርንጫፍ ቢሮው እንደተዘጋበት አስታወቀ:: በጋሞ ጎፋ በቅስቀሳ ላይ የነበሩ የሰማያዊ አባላት ታሰሩ::

የ9ኙ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ትብብር ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍና የምርጫ ቅስቀሳ ለማካሄድ የመረጣቸውን 15 ከተሞች ይፋ አደረገ፡፡ ትብብሩ በተመሳሳይ ሰዓት በ15 ዋና ዋና የሀገሪቱ ከተሞች ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ለማድረግ ቀደም ብሎ አሳውቆ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በዚህ መሰረት የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር መጋቢት 20/2007 ዓ.ም በተመሳሳይ ሰዓት ሰልፉን የሚያካሂድባቸው ከተሞች የሚከተሉት ሆነዋል፡፡ እነዚህም አዳማ፣ ባህር ዳር፣ አርባ ምንጭ፣ ደብረ ታቦር፣ ሐዋሳ፣ ጅማ፣ ደብረ ብርሃን፣ ወልቂጤ፣ አሰበ ተፈሪ (ጭሮ)፣ ወላይታ ሶዶ፣ ደሴ፣ ዱራሜ፣ ደብረ ማርቆስ እና ሆሳዕና ናቸው፡፡ትብብሩ ‹‹መጋቢት 20 በፍጹም አይቀርም›› በሚል ለህዝቡ የድጋፍ ሰልፍ ጥሪ ያደረገ ሲሆን፣ ከተሞቹ የተመረጡትም ፓርቲዎቹ በየአካባቢዎች ባቀረቡት እጩ ብዛት መሰረት እንደሆነ ገልጹዋል፡፡ይህ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ የሚደረገው የድጋፍ ሰልፍ በተመረጡት ከተሞች የሚደረገው ሰልፍ በተከናወነ በሳምንቱ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
===================================
ሰማያዊ ፓርቲ ባህር ዳር ቅርንጫፍ ቢሮው እንደተዘጋበት አስታወቀ

ሰማያዊ ፓርቲ በባህር ዳር ከተማ የከፈተው ቢሮው በአከራይ ላይ በተፈጸመ ከፍተኛ ወከባና ማስፈራሪያ ምክንያት እንደተዘጋበት በስፍራው የፓርቲው አስተባባሪ ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጸ፡፡

በባህር ዳር የፓርቲው አስተባባሪ አቶ አዲሱ ጌታነህ እንደገለጹት ቅርንጫፍ ቢሮው ከትናንት ጀምሮ የፓርቲው ንብረቶች ውስጥ እንዳሉ ተቆልፏል፡፡ አቶ አዲሱ ቢሮውን ያከራዩት ሰው በተደጋጋሚ ከፖሊስ፣ ከኢህአዴግ ካድሬዎችና ከደህንነት ሰዎች ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው እንደሆነ በመግለጽ ቤቱን እንዲለቁላቸው ሲነግሯቸው እንደነበር አስታውሶ፣ ሆኖም ግን ፓርቲው የአንድ አመት ውል ስላለው መልቀቁን እንዳልፈለገ ገልጹዋል፡፡

አከራዩዋ ‹‹ቀሪ ብራችሁን እመልሳለሁ፡፡ የሚደርስብኝን ጫና መቋቋም አልቻልኩምና ውጡልኝ፡፡ ሰዎቹ በዱርየዎች እንደሚያስደበድቡኝ መዛታቸውን ስለሰማሁ ቢሯችሁን ቆልፌዋለሁ›› ማለታቸውን የጠቀሰው አቶ አዲሱ፣ በተለይ በከተማዋ የበላይ ዘለቀ ቀበሌ የጸጥታ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ጌታቸው ግዛቸው አላስፈላጊ ወከባውን በማስተባበር ላይ መሆኑን አስረድቷል፡፡ፓርቲው ጉዳዩን ወደ ህግ እንደሚወስደውም አቶ አዲስ ጨምሮ ገልጹዋል፡፡
================================
በጋሞ ጎፋ በቅስቀሳ ላይ የነበሩ የሰማያዊ አባላት ታሰሩ

በጋሞ ጎፋ ዞን ኮንሶ ወረዳ በምርጫ ቅስቀሳ ላይ የነበሩ ስምንት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት መታሰራቸውን የዞኑ የፓርቲው አስተባባሪ ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡
አባላቱ ከመጋቢት 9/2007 ዓ.ም ጀምሮ በእስር ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ በእስር ላይ የሚገኙት ስምንቱ ሰዎች የሚከተሉት ናቸው፡-
1. ካርታ ካርኪ
2. ኩንሳ ካፒሊ
3. ታሪኩ አንካሶ
4. ካያና ካላታ
5. ገላዬ ካይድራ
6. ካርታ ሀይቶ
7. ኩንሱ ካምባ
8. ሆዳ ሆልጥሽ

ናቸው፡፡11052444_1567287580209106_4888801381358411345_n