ለእሁዱ የ35 ሺህ ቤቶች እጣ ብቁ የሆኑ ተመዝጋቢዎች ቁጥርና የቤት ዋጋ ይፋ ሆነ Number of condos and price of homes announced for 35 thousand home owners
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2007 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፊታችን እሁድ ለሚወጡ 35 ሺህ የ20/80 እና 10 /90 የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ ውስጥ ለመካተት ብቁ የሆኑ ነዋሪዎች ቁጥር ይፋ ሆነ።
እሁድ ዕለት እጣ ከሚወጣባቸው 35 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ የ10/90 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ቁጥር 960፣ የ20/80 ስቱዲዮ 6 ሺህ 768፣ ባለ 1 መኝታ 15 ሺህ 638፣ ባለ 2 መኝታ 7 ሺህ 322፣ ባለ 3 መኝታ 4 ሺህ 312 መሆናቸው ታውቋል።
በእሁዱ እጣ ተካፋይ የሚሆኑትን ቆጣቢዎች በተመለከተም፥ በደንበኞች ሂሳብ ቁጥር ውስጥ ያለው ገንዘብ በወር መቆጠብ ካለባቸው የገንዘብ መጠን አንጻር ለ16 ወራት የሚሆን የቆጠቡ መሆን እንዳለባቸው አስተዳደሩ አስታውቆ ያንንም ሲያጣራ ቆይቷል።
በዚህም መሰረት 34 ሺህ ገደማ ለሆኑት የ20/80 መርሃ ግብር ቤቶች በነባርነት ከተመዘገቡ 134 ሺህ 099 ቆጣቢዎች መካከል 81 ሺህ 037 የሚሆኑት በእጣ ውስጥ ለመካተት ብቁ ሆነዋል። እሁድ እጣ ለሚወጣባቸው 960 የ10/90 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ደግሞ 14 ሺህ 192 ሰዎች በእጣው ለመካተት ብቁ መሆናቸውን ነው ይፋ ያደረገው። አስተዳደሩ በመግለጫው የቤቶችን ዋጋ ዝርዝርንም አስታውቋል።
አሁን እጣ የሚወጣባቸው ቤቶች በአጠቃላይ 16 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው ሲሆን፥ መንግስትም ከዚህ ውስጥ 7 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብሩን ድጎማ አድርጓል። መንግስት ይህን ያህል ገንዘብ ድጎማ ማድረጉ የቤቶቹ ዋጋ እንዳይንር ማድረጉን ከንቲባ ድሪባ ኩማ በመግለጫው ላይ አንስተዋል።
በዚህም መሰረት ለ10/90 ቤቶች በካሬ ሜትር 1 ሺህ 910 ብር፣ ለ20/80 ስቱዲዮ 2 ሺህ 483 ብር፣ ለ20/80 ባለ አንድ መኝታ ቤት 3 ሺህ 438 ብር፣ ለ20/80 ባለ ሁለት መኝታ ቤት 4 ሺህ 394 ብር እና ለ20/80 ባለ ሶስት መኝታ ቤት 4 ሺህ 776 ብር መሆኑ ተገልጿል።
የ10/90 ቤቶች በአማካይ 36 ነጥብ 82 ካሬ ሜትር ስፋት ሲኖራቸው፥ የ20/80 ስቱዲዮ 29 ነጥብ 60 ካሬ ሜትር፣ ባለ አንድ መኝታ 48 ነጥብ 34 ካሬ ሜትር፣ ባለ ሁለት መኝታ 72 ነጥብ 28 ካሬ ሜትር እና ባለ ሶስት መኝታ 97 ነጥብ 13 ካሬ ሜትር ስፋት በአማካይ እንደሚኖራቸውም በመግለጫው ተመልክቷል። የቤቶቹ ዋጋ ካለፉት በ8ኛ አና 9ኛ ዙር ለባለዕድለኞች ከተላለፉበት ዋጋ ከ15 እስከ 20 በመቶ ጭማሪ ተደርጓል።
በእጣው አወጣጡ ሴቶች 30 በመቶ እና የመንግስት ሰራተኞች 20 በመቶ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ይሆናል። ስለዚህም ባለዕድለኛ የመንግስት ሰራተኞች ከሚሰሩበት ተቋም የማረጋገጫ ደብዳቤ ይዘው መቅረብ ይኖርባቸዋል፤ ቤቶቹን ለመረከብም በ10/90 የቤት ፕሮግራም ዕድለኞች የሆኑ የ10 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ መክፈል ሲጠበቅባቸው፥ የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤት ባለዕድለኞች ደግሞ የ20 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ መክፈል ይኖርባቸዋል።
ከዚህም ባለፈ ባለዕድለኞች ቤቶቹን ለመረከብ የሚጠበቅባቸውን መስፈርቶች አሟልተው በ2 ወራት ጊዜ ውስጥ ውል እንዲፈርሙ ይገደዳሉ።
ከእሁዱ ዕጣ የሚተርፉ ቆጣቢዎችም በቀጣይ ሰኔ ወር በእጣ እንደሚተላለፉ በሚጠበቁት ከ32 ሺህ በላይ ቤቶች እጣ ውስጥ ይካተታሉ።
ለስድስት ወራት በተከታታይ ሳይቆጥቡ እጣ ውስጥ መግባት ያልቻሉ ተመዝጋቢዎችም የሚጠበቅባቸውን ቆጥበው ከተገኙ በቀጣይ ዙሮች ዕጣ ውስጥ እንዲካተቱ ይደረጋል። 35 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ በየካ አባዶ፣ ቦሌ ቡልቡላ፣ ቱሉ ዲምቱ፣ ባሻ ወልዴ፣ ልደታ መልሶ ማልማት እና ገነት መናፈሻ መንደሮች ላይ የሚገኙ መሆናቸውን የከተማ አስተዳደሩ ጠቅሷል። እሁድ ዕጣ የደረሳቸውን ባለዕድለኞች ስም ዝርዝር ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመተባበር በድረገጹ www.fanabc.com ላይ ይዞ እንደሚወጣ ከወዲሁ ይገልጻል።
በባሃሩ ይድነቃቸው
Watch Ethiopian movies legally. Upto 5 movies added daily. Here are the top 10 most viewed movies today.
Receive Ethiopian News, Movies and Videos by email. Sign up for Email alerts ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን፣ ጠቃሚ ምክሮችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜሎን ያስመዘግቡ።
