በመቀሌ አንዱ ወረዳ የመድረክ ተወዳዳሪ – አረጋሽ አዳነ (በላይ ገሰስ)

10428515_793641810720755_389702726005876893_nአረጋሽ በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ – ህወሓት – ሲታገሉ ከቆዩት ነባር ታጋይ ሴቶች አንዷ ናት:: በትጥቅ ትግሉ ሂደት በነበራት ንቁ ተሳትፎ፣ ጀግንነትና የአመራር ብቃት መሰረት በየደረጃው ከተራ ተዋጊነት እስከ ማእከላይ ኮሚቴ የመሪነት ደረጃ የደረሰች ብቸኛ ሴት ነበረች:: በወቅቱ ከነበሩት ጠቅላላ ታጋይ ሴቶች ውስጥ ከዩኒቨርስቲ በደግሪ የተመረቀች ብቸኛ ሴት ነበረች:: በመሆኑም የትምህርት ብስለትዋን፣ የፓለቲካ ብቃትዋን፣ ጀግንነትዋንና ድፍረትዋን ሁሉም ተደማምረው በህዝቡና በሰፊው ታጋይ ዘንድ ትልቅ ከበሬታና አሜኔታ በማትረፍ ታጋይና አታጋይ በመሆን ረጅም መንገድ ተጉዛ አዲስ አበባ ድረስ ዘልቃለች::

ህወሓት/ኢሕአዴግ መንግስታዊ ስልጣን ከያዘ በሗላም የድርጅቱን የማእከላዊ ኮሚቴ አባልና የትግራይ ክልላዊ መንግስት ዋና ፀሐፊ በመሆን የተለያዩ የሞያ ዘርፎችን በመምራት ስታገለግል ቆይታለች:: አረጋሽ በትጥቅ ትግሉ ዘመንም ሆነ በሗላ በአመራር ላይ በነበረችበት ጊዜ ህዝባዊና ድርጅታዊ ስብሰባዎችን በመምራትና በማሳካት ልዩ ተሰጥዖ ነበራት:: በተለይም በሴቶች የነፃነትና የመብት ጥያቄዎች ላይ በነበራት ፅኑ እምነትና አቋም ምክንያት በተለያዩ መድረኮችና ስብሰባዎች ተገኝታ በመከራከርና በማስረዳት እስከ መጨረሻ በአቋሟ ፀንታ ቀጥላለች:: አረጋሽ በሴቶች ጉዳይ ብቻ አይደለም በሌሎች ፓለቲካዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያም የራሷን አመለካከት ይዛ በግልፅ ስትከራከርና ስትሟጎት ቆይታለች::

ለምሳሌ በሀገራችን ሉዓላዊነት ጉዳይ ዙሪያ ይነሱ በነበሩት ልዩነቶች ምክንያት በተለይም አፍቃሬ ሻዕቢያ በሆኑት ጥቂት የህወሓትመሪዎች ዘንድ በሞጎደኛነት ዓይን እንዲትታይ አድርጓታል:: በመጨረሻም በፈረንጆች አቆጣጠር በ2001 ዓ.ም. በህወሓት ውስጥ በተፈጠረው መከፋፈል ምክንያት ከህወሓት ተለይተው ከወጡ 12 የማእከላይ ኮሚቴ አባላት አንዷ በመሆን የትግል ጎራዋን ለየች::

ከጥቂት ጊዜ በሗላም ከህወሓት የተለዩ የፓለቲካ አመራሮች ዕጣ ፋንታቸውን ምን ሊሆን ይችላል ተብሎ በጉጉት ሲጠበቁ፣ በማሀሉ አብዛኞቹ ከህወሓት ወዲያ ሌላ ትግል አይቻልም ብለው ራሳቸውን ከትግሉ ጎራ አገለሉ:: አቶ ስየ አብርሃ እስር ቤት ገባ:: የቀሩት አረጋሽ አዳነ፣ ገብሩ አስራትና አውዓሎም ወሉ ግን ያልተቋጨ ሀገራዊ አጀንዳና ህዝባዊ አደራ አለን በማለት ቀደም ብለው የተወሰኑ የትግራይ ምሁራን ወስጥ ለውስጥ ጀምረውት የነበረው የፓለቲካ እንቅስቃሴ ጋር በማበር እኖሆ ዓረና ትግራይ ፓርቲን በማቋቋም መራራ ትግላቸውን ተያያዙት:: አረጋሽም የአዲሱ ድርጅት የዓረና ትግራይ ፓርቲ ማእከላይ ኮሚቴ አባል ሆነች::

አረጋሽ የነ መለስ ዜናዊ የቤተ መንግስት ቡድን የስም ማጥፋትና የውሸት ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ሳይበግራት በልበ ሙሉነት እንቅስቃሴዋን ቀጠለች:: በርሱዋ ላይ የሚደረገው ጫናም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ሄደ:: በመጀመሪያ መፈንቅለ መንግስት በሗላ ደግሞ መፈንቅለ ፓርቲ ለማድረግ አሲራለች በማለት በተለያየ መልኩ የስነ ልቦናና የማግለል ጥቃት ለማድረስ ትልቅ ዘመቻ ተካሄደባት:: ከፕሮፓጋንዳ አልፈው በግል ህይወትዋና ስብእናዋ ላይ መግባት ጀመሩ:: በዚህ መሰረት በማንኛውም መልኩ በመንግስት ስራ አካባቢ እንዳትቀጠር ተደረገ:: በሗላም በሞያዋ በአንድ የግል ድርጅት ተቀጥራ ለመስራት ስትጀምር ሌላ ሰበብ በመፍጠር በተቀጠረችበት መስሪያ ቤት ላይ የተለያየ ተፅዕኖ በማድረግ ከስራው እንድትለቅ አደረጉ:: ይህንን ሁሉ ተፅዕኖ የሚደረግባት ዋናው ምክንያትም ለሁለት ነገር ነበር:: በአንድ በኩል ለሆድዋ ስትል ይቅርታ ጠይቃ እጅዋን እንድትሰጥ ጫና ለማድረግ ነው:: ይህ ካልሆነ ደግሞ ችግር ላይ ወድቃ ሌሎች የህወሓት ታጋዮች እንዳያፈነግጡ እንደ መቀጣጫ ወይም “እኔን አይተህ ተቀጣ” የሚል መልእክት ለማስተላለፍ እንዲጠቀሙባት ነበር ሃሳባቸው:: ነገር ግን አልሆነላቸውም:: የአላማ ፅናትዋ ከብረት የጠነከረ ሆኖ አገኙት::

አረጋሽ ይህንን ሁሉ መከራ ተቋቁማ በሶስተኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ ዓረና ትግራይን ወክላ ለፌዴራል ፓርላማ ዕጩ ተመራጭ በመሆን በዓድዋ ከተማ ከመለስ ዜናዊ ጋር ለምርጫ ውድድር ቀረበች:: የምረጡኝ ዘመቻ ተፋፋመ:: የህወሓት ካድሬዎችና ደጋፊዎቻቸው የተለየ ሃሳብና ፓሊሲ ይዞ መለስን በግልፅ መወዳደር ያልለመዱት የፓለቲካ ባህል ስለሆነ የአረጋሽ አዳነን በዓድዋ መወዳደር እንደ መብት ሳይሆን እንደ ድፍረት ቆጠሩት:: ብቻውን ሮጦ ብቻውን ማሸነፍ የለመደው መለስ ዜናዊም የአረጋሽ ተሳትፎ እንደ ቀላል ነገር አላየውም:: በሁለቱ መካከል ጎልቶ የወጣ ባይሆንም ገና ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ እምብዛም አይዋደዱም:: አረጋሽ በተለያየ ጊዜ የድርጅቱ ስብሰባ ስትመራ አልፎ አልፎ በአንዳንድ ነገሮች ይጋጩ እንደነበር ይታወሳል:: በክፍፍሉ ጊዜም መለስን ይንቃሉ ተብለው ቂም ከተያዘባቸው ውስጥ ከስየ አብርሃ ቀጥሎ አረጋሽ አዳነ ነበረች:: ይህ ሁሉ ታሪካዊ ሁኔታዎች ተደማምረው ሲታዩ የዓድዋው የምርጫ ውድድር ቀላል አልነበረም::

የምረጡኝ ቅስቀሳ እየተጋጋለ ሲሄድ በአካባቢው የሚገኙ ካድሬዎችና ደጋፊዎች ተሰባስበው የተለያዩ አጥቂና ስብሰባ በታኝ ቡድኖችን በማድረጀት አረጋሽን እንደ ባዕድ በመቁጠር የማጥላላትና የማስፈራራት ዘመቻ ከፈቱ:: መለስን ዘንበባ አንጥፈው ሲቀበሉት እሱዋን ግን በገዛ ትውልድ መንደርዋ በነፃ ተንቀሳቅሳ ምረጡኝ ብላ ለመናገር አዳጋች ሆነባት:: ስብሰባ ስትጠራ ሌላ ተመሳሳይ ስብሰባ ይጠራሉ:: ነዋሪውን ህዝብ ወደ ጠላት ስብሰባ እንዳትሄድ እያሉ ያስፈራራሉ:: በስብሰባው ቦታም በታኝ ቡድን አሰርጎው በማስገባት ተሰብሳቢውን እንዲበተን ያደርጋሉ:: ከአዳራሹ ውጭም ከተለያየ አቅጣጫ ድንጋይ እየወረወሩ አረጋሽን ያጠቁ ነበር:: ይህ ሁሉ ሲደረግ ፓሊስና ሌሎች የፀጥታ ሀይሎች ቆሞው ያያሉ:: የሕግ ከለላ እንዲሰጣት ብትጠይቅም መልስ የለም:: በዚሁ ሁኔታ የተካሄደውን ምርጫ መለስ አሸንፏል ተብሎ ተበሰረ:: በአንፃሩ ካድሬውም አጥቂውም ፓሊሱም መሪውም በመቀናጀት በአንዲት ታጋይ እህታችን በአረጋሽ ላይ በመረባረብ ቂማቸውን ተወጡባት:: ዓድዋ የመለስ ዜናዊና የስብሓት ነጋ የግል ጓሮ መሆንዋንም አስመሰከረች::

አረጋሽ ዘንድሮም በፈረንጆች አቆጣጠር በፊታችን ግንቦት 24, 2015 ዓ.ም. በሀገራችን በሚካሄደው 5ኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ ላይ በመቀሌ ከተማ በዕጩነት ለመወዳደር ተመዝግባለች:: በመሆኑም ይህቺ ዕድሜ ልክዋን ሁሉ ለትግል የሰጠች፣ ከራስዋ ህይወት በላይ ሀገርዋንና ህዝብዋን የምትወድ፣ በፍቅረ ንዋይና በጥቅም የማትንበረከክ፣ ቆራጥና አስተዋይ የፓለቲካ መሪ ለተደላደለ ንሮ፣ ለሀብትና ለጡረታ እንኳን አልታደለችም:: ከአላማዋና ነፃነትዋ ሌላ የምትመኘው ሀብት የላትም:: ስለሆነም የዘንድሮውን ምርጫ የተሳካ እንዲሆንላት በጎ ምኞት ብቻ ሳይሆን ምርጫውን ምክንያት በማድረግና ስፓንሰር በመሆን በሞራልም ሆነ በተለያየ መልኩ በመተባበር አይዘሽ እኛም ከጎንሽ አለን ልንላት ይገባል:: ለዚህች ጀግና ሴት ማበረታታትና መደገፍ ማለት ደግሞ ሌሎቹም ወደ ትግሉ መድረክ እንዲወጡ የሚገፋፋ ስለሆነም ጭምር ነው :: በምርጫ ጊዜ መተባበር ማለት ደግሞ በሞራልና በንዋይ ብቻ አይደለም:: ከያለንበት ቦታ ስልክ በመደወል ለጓደኞቻችንና ቤተሰቦቻችን እገሌን ምርጡ ብለን መናገርም እንችላለን::

ለመተባበር የምትፈልጉ ካላችሁ በኢሜይል ([email protected]) ስልክ ቁጥር (240 701 1445) በመደወል አስፈላጊውን መረጃ ማግኘት ትችላላችሁ:: እኔም ለወይዘሪት አረጋሽ አዳነ እንኳን ለማርች 8 በሰላም አደረሰሽ እያልኩኝ መልካም የምርጫ ዕድል እንዲሆንላትም ከልብ እመኛለሁ::

The post በመቀሌ አንዱ ወረዳ የመድረክ ተወዳዳሪ – አረጋሽ አዳነ (በላይ ገሰስ) appeared first on ሳተናው (Satenaw) -Latest Ethiopian News & Breaking News.