ሀበሻ በየመን፣ በቁም ብቻ ሳይሆን እሬሳውም ይሰቃያል

ከግሩም ተክለሃይማኖት

አንድ ክርስቲያን ሞቶ መቅበሪያ ቦታና የድጋፍ ወረቅት አጥተን ራሳው ፍሪጅ ውስጥ ቀረ

የውስጥ ቁስል የሚሆን በርካታ ስቃይ ማየት በተለመደበት የስደት ህይወት ውስጥ የሞተ ወገንን መቅበር አለመቻል እንዴት ስሜትን እንክት እንደሚያደርግ የደረሰበት ካልሆነ ማን ይረዳዋል?ማንም::በእምነት ልዩነት ምክንያት መቀበሪያ ማጣት አንድ ችግር ሆኖ ሳለ ለዜጎቹ ግድ የሌለው ኤምባሲና የጭፍሮቹ መዳከሪያ ኮሙኒቲ ለመተባበር አለመፈለጋቸው ኢትዮጵያዊነት ዋጋ ያጣበት ጊዜ ያሰኛል::ሀበሻ በየመን ለጉድ ይኖራል::የየመን መንግስት ሀበሻን አልጎዳም::በየቦታው ታስረው ያሉትም ቢሆን ድንበር ጥሰው ገብተው ብሎም ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሊሻገሩ ሲሉ የያዛቸው ከመሆናቸው ባሻገር ኤምባሲው መጓጓዣቸውን ቶሎ ቢያጠናቅቅ ኖሮ ማቆየት እንደማይፈልጉ ሁሌም የሚገልጹት ነገር ነው::እንደህገ-ወጡ መብዛት እንዲያውም ምንም ችግር የለም ማለት ይቻላል::መኖሪያ ፍቃድ ካለው ይልቅ ህገወጡ ይበዛል::የመናዊያንም ቢሆኑ ለሀበሻ ጥሩ ናቸው::በተለይ ከከተማ ውጭ ያሉ የመናዊያን በባህር ለሚገባው ተራብን ለሚለው ሁሉ አብልተው መንገድ መርተው ነው::ያን ማለት ግን ሀበሻን ሙሉ ለሙሉ አይበድሉም ማለት አይደለም ከሌላው አረብ ሀገራት የተሻለ ነው ለማለት ነው::

የመናዊያን የሚኖሩት በህጋቸው:በባህላቸው:በእምነታቸው እንጂ በእኛ ባህልና ህግ አይደለም::ክርስቲያን ለብቻው መቃብር የለውም::እነሱም አብሯቸው እንዲቀበር አይፈልጉም::ሰለዚህ ለቀብር ሲባል ስም ቀይሮ የሙስሊም ስም አድርጎ መቀበር የተለመደ ነው::አለበለዚያ ሬሳ የትም መቅረቱ ነው::

ወንደሰን ካሳሁን የተባለ አንድ ኢትዮጵያዊ በጠና ታመመ አሉኝ::ባውቀውም ባላውቀውም ሄጄ ማየት የህሊና ግዴታዬ ነበርና ሄድኩ::እለተ ረቡዕ 29/12/10 ምሽት ላይ አል ተውራ የተባለው ሆስፒታል ሄጄ ሳየው ጣር ላይ ነበር::በዛ..ሰዓት ሚስቱና እና የአንድ ልጁ እናት ታለቅሳለች::ሄኖክ የተባል ልጅ ጠራሁና እኔና እሱ ልናድር ወሰንኩ::ታዲያ ሰው ሁሉ አንዱ ታመመ ሲባል ሽሽት ነው::በሽታ ሁሉ …ነው የተባል ይመስል የጥርጣሬው እስኬል ቂብ የሚለው የዘመኗን ነው::በቃ! መጠራጠር ነው::እሸት በሌለበት መጠርጠር..መቼ ይሆን የምንተማመነው?እርስ በእርስ ከመባላት..ከመጠራጠር..ከመቀናናት ወጠተን በፍቅር የምንኖረው?
የብርዱን ነገር ተዉትና ልጁ አዳሩን ቢያድርም የንጋት ጀንበር ሳይደምቅ ሀሙስ ጠዋት ነብሱ ከስጋው ተለያየ::ወዲያው ፍሪጅ ይግባ አሉ/በእነሱ አጠራር ተላጃ ነው የሚሉት/:: ማውጫ ወረቀቱን ተሯሩጨ ብጨርስም እምነቱ ክርስቲያን ስለሆነ መቅበሪያ ቦታ የት ነው? ወይ ከኤምባሲ ወይም ከUNHCR ወረቀት አጽፍ ተባልኩና እሬሳው ፍሪጅ ገባ::
UNHCR ህሙስ እና አርብ ስለማይስሩ ኮሚኒቲ ተብየው ጋር ሄድን::የሉም::በየቤታቸው ለመደውል ቁጥር ፈላልገን ሞከርን::አንደኛው የለም ሞባይሉን ተቶ ወጥቶ ነው ተባል::ሁለተኛው ሽንት ቤት ነው ቆይታችሁ ደውሉ ተባለ::ቆየተን..ቆይተን ደወልን አሁንም ሽንት ቤት ነው ተባለ::የእሱ እንትን በጸሎት ነው እንዴ የሚመጣው ከ40 ደቂቃ በኋላም ሽንት ቤት የሚሆነው? ለህዝቡ ችግር ትኩረት ካለመስጠት የተነሳ እያላገጡ እስከመቼ?እኔ እንኳን አላረገውም ኤምባሲ ሌሎች ቢሄዱም ኮሚኒቲ ሂዱ ተብለው ተመለሱ::ዲሞክራሲን በወሬ የሚቦተልክ መንግስት ያዋቀረው ኤምባሲ ከማውራት ያለፈ ምን ይፈይዳል ተብሎ ይጠበቃል?ለአንድም ኢትዮጵያዊ ቁም ነገር ያልሰራው ኤምባሲ ወሬ ቃራሚ እና አቀባዮችን በየመንደሩ ወሽቆ የሀበሻውን ህይወት በመፈራራት እና የሰቀቀን እንዲሆን አደርጎታል::ከ70-80 ሺህ ኢትዮጵያዊያን በስደት የሚኖሩባት የመን ውስጥ ኤምባሲው ለክርስቲያን መቃብር የሚሆን ቦታ አለመጠየቁ ምንነቱን…ተልእኮውን የረሳ መሆኑን ያሳያል::በጣም ጥቂት የኢትዮጵያዊያንን 10% ዜጎች ያሉት የቻይና መንግስት የመቃብር ቦታ አለው ::የግብጽ ክርስቲያኖችም እንዲሁ የ እኛ ኤምባሲ ግን….

ኢትዮጵያዊያን መቼም አልታደልንም በUNHCR በኩልም ቢሆን ተስፋ አስቆራጭ ነገሮች ናቸው ያሉት::ሬሳ ሆስፒታል አልሰጥም ብለው ያዙብን ይህ ልጅ የስደተኝነት ማረጋገጫ ማንዴት አለው ምንድን ነው የምትረዱን? አልን:: ምንም መርዳት እንደማይችሉ ነገሩን::ከነዓካቴው ባጀት አለቀቁልንም ተባለ:: unhcr ሲቸገሩ ካልረዳ ሲሞቱ ካልቀበረ የጄኔቫ ኮንቬንሽን ሁሉ ተሰርዟል ማለት ነው?ወረቀት ስጥቶ ሌላ ችግራችንን ጆሮ ዳባ ልበስ ማለት ውጤቱ ምንደን ነው? ያልተገነጠልነውን ኦሮሞ ነህ ኢትዮጵያዊ እያሉ መለያየት ነው እርዳታቸው?
የሚያሳዝነው የኢትዮጵያዊው አስከሬን አሁንም ሆስፒታል ውስጥ ሲሆን የ የበለጠ ችግር
የሆነው ደግሞ የመቀብሪያው ቦታ ነገር ነው::ከሰነዓ ተነስተን አደን የምትባለው የየመን ሁለተኛዋ ከተማ ድረስ መሄድ ግድ ሊሆን ነው::
ይህ ሁሉ ተቆርቋሪ ማጣት ዜግነትን መገፈፍ ነው::የመን ካለው ኢትዮጵያ ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼው ኮ/ል መሀመድ እና አንድ ተጭማሪ ስራተኛ ጠፍተው ሄደዋል::ብዙ ነገር ሲቀባጠሩ ተስተውለዋል::ያለውን ችግር ምነው እንደማያውቅ አለፉት?ራሳቸውን ለህዝብ ተቆርቋሪ አርገው ከሚቆልሉ ምነው ይህን እንኳን አመቻችተው ቢሆን?
አሁን ያሉትም ቆንስል ቢሆኑ ካለፉት በምን ተለዩ?ሁሌ ተወቃሽ ከመሆን አሁን እንኳን ለህዝብ ጆሯቸውን ቢሰጡ::ወሬ ከመቃረም ስረቶ ማለፍ ቆምኩለት የሚሉትን ህዝብ መቀበሪያውን እንኳን ማመቻቸት ተገቢ ነው::በማውራትና በዲስኩር ታሪክ የሰራ የለም::