አስር የድረ-ገጽ አዘጋጆች ቴድሮስ አድሃኖም ውሸታቸውን እንዲያርሙ አሳሰቡ!

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ “ቁጥር አንድ የኢትዮጵያ ፒኖሾ” የሚል ስያሜ አግኝተዋል!!
ጋዜጣዊ መግለጫ
ዋሽንግተን ዲሲ፤ አስር የድረ-ገጽ አዘጋጆች በአንድነት በመሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በመንግስት መገናኛ ብዙሃን እና በፌስቡክ ገጻቸው የተናገሩትን አጸያፊ እና ሃላፊነት የጎደለው ውሸት እንዲያርሙ ጠይቀዋል። ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በመገናኛ ብዙሃን ታዳጊ ወጣት በሪቱ ጃለታ የተናገሩትን የ20 ሚልዮን ዶላር የፈጠራ ታሪክ እስካሁን ባለማረማቸውና ህዝብን ይቅርታ ባለመጠየቃቸው፣ የድረገጽ አዘጋጆቹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን “ቁጥር አንድ የኢትዮጵያ ፒኖሾ” (የፈጠራ ገጸ-ባህርይ) የሚል ስያሜ በአንድ ድምጽ ሰጥተዋቸዋል።

የአቡጊዳ፣ የአዲስ ቮይስ፣ የኢካድ ፎረም፣ የኢትዮፎረም፣ የኢትዮ ፍሪደም፣ የኢትዮ ሜድያ፣ የኢትዮጵያን ሪቪው፣ የቋጠሮ፣ የሳተናው እና የ ዘሃበሻ ድረ-ገጽ አዘጋጆች በጋራ በመሆን ይህንን አቋም የወሰዱት፣ ሚኒስትሩ በህዝብ ፊት በመቅረብ ነዋሪነትዋ በሜልቦርን ስለሆነው 14 አመት ተማሪ ብሪቱ ጃለታ በተናገሩት ፍጹም ሃላፊነት የጎደለው ቅጥፈት የተነሳ ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከሳምንታት በፊት ከታዳጊ ወጣትዋ ጋር በቢሮአቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤

“ነዋሪነቷ ሜልበርን ከተማ አውስትሬልያ የሆነችው የ14 ዓመት ታዳጊ ወጣት በቅርቡ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳድራ 20 ሚልዮን የአውስትሬልያ ዶላር ተሸላሚ ስትሆን፤ ያገኘችውን ገንዘብ በኢትዮጵያ ለልማት ለማዋል ወስናለች። በሪቱ በዚህ ዕድሜ ይህን ያህል ከፍተኛ ገንዘብ ለሃገር በማበርከት ተወዳዳሪ የሚገኝላት አይመስለኝም”

ማለታቸው የሚታወስ ነው። ይህ መግለጫ ከእውነት የራቅ ነው። የተጠቀሰው ባደን ኮሌጅ መግለጫው ሃሰት እንደሆነ ታናግሯል። የሽልማቱን ፈንድ ፈቀደ የተባለው ሮታሪ ተቋም እና የአውስትራሊያ መንግስትም መግለጫው ሃሰት እንደሆነ እና ለጉዳዩ እንግዳ መሆናቸውን ገልጸዋል።

“ሚኒስትሩ በአስቸኳAይ ይህንን ሃላፊነት የጎደለውን መግለጫ እንዲያስተባብሉ እና ያለምንም ማንገራገር ሕዝቡን ይቅርታ እንዲጠይቁ እናሳስባለን።”

ሲሉ አስሩ የድረ-ገጽ አዘጋጆች ጠይቀዋል።

ይህ መግለጫ ፍጹም ሃስት የሆነ ታሪክ እና ፈጠራ መሆኑ በመረጃ የተረጋገጠ በመሆኑ ሚኒስትሩ ጥፋቱን በታዳጊዋ ህጻን ላይ ማመካኘቱን ትተው ራሳቸው ሃላፊነቱን እንዲወስዱም የደረ-ገጽ አዘጋጆቹ አሳስበዋል።beritu-and-family-1