በመጪው ሰኔ ወር 32 ሺህ የ10/90፣ 20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለተጠቃሚዎች ይተላለፋሉ 32 thousand condo units will be transferred to owners in June

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2007 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ነባር የቤት ፈላጊዎች ከሰኔ 2005 እስከ የካቲት 2007 ድረስ በሚገኙት 21 ወራቶች ውስጥ ከስድስት ወራት በላይ የባንክ ቁጠባ እዳ ከሌለባቸው በጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣው ተሳታፊ ይሆናሉ ተባለ።

በሰኔ 2005 ዓ.ም ከ900 ሺህ በላይ የቤት ፈላጊ ዳግም ምዝገባ ያካሄደ ሲሆን፥ ከዚህ ውስጥ ከ132 ሺህ በላይ የሚሆነው ነባር ተመዝጋቢ ነው።

በዚህም መሰረት በቤት ፈላጊዎች የተቆጠበው የገንዘብ መጠን ከሰኔ 2005 እስከ የካቲት 2007 ድረስ በሚገኙት 21 ወራቶች ተካፍሎ ከስድስት ወራት በላይ እዳ እንደሌለው ከተረጋገጠ በዕጣው ውስጥ እንደሚካተት አቶ መስፍን መንግስቱ የከተማዋ ቤቶች ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገነቡት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ 41 ሺህ ቤቶች ከመጋቢት 10 እስከ መጋቢት13፣ 2007 ዓ.ም በእጣ ለተጠቃሚዎች ይተላለፋሉም ተብሏል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ ለፋና ብሮድካሲቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ እጣ ከሚወጣባቸው ውስጥ 1 ሺህ ያህሉ ቤቶች በ10/90 የቤት ልማት መርሃ ግብር የሚገኙ ሲሆኑ፥ ከ34 ሺህ በላይ ደግሞ የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ናቸው።

አቶ ድሪባ ኩማ አክለውም በተለያዩ የከተማይቱ ክፍሎች የተጀመሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታቸው እንዲፋጠን እየተደረገ ይገኛልም ነው ያሉት ።

በያዝነው ወር ለተጠቃሚዎች የሚተላለፉት የጋራ መኖሪያ ቤቶች 35 ሺህ በእጣ የሚተላለፉ ሲሆን፥ ቀሪዎቹ 7 ሺህ ቤቶችም ከተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች በልማት ለሚነሱ ነዋሪዎች የሚሰጥ መሆኑንም ገልጸዋል።

የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ በየካ አባዶ፣ ቦሌ ለሚ፣ ቦሌ ቡልቡላ እና ቱሉ ዲምቱን ጨምሮ ባሉ ሰባት መንደሮች ላይ እንደሚገኙም ከንቲባው ተናግረዋል።

የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ የግንባታ ሂደታቸው እንዲፋጠን በማድረግ የውሃ፣ የኤክትሪክ ሀይል አቅርቦትና የመንግድ መሰረተ ልማት እንዲሟላላቸው አሰተዳደሩ በልዩ ትኩረት ሲከታተል መቆየቱን ጠቅሰዋል።

አሁን ከሚተላለፉት የጋራ መኖሪያ ቤቶች በተጨማሪም በተያዘው ዓመት በ40/60 የቤት ልማት መርሃ ግብር 1 ሺህ 200 ቤቶች ለእድለኞች በዕጣ ሲተላለፉ፥ የ15 ሺህ የ40/60 ቤቶች ግንባታም በያዝነው ዓመት ይጀመራል ተብሏል።

በመጪው ሰኔ ወርም 32 ሺህ የ10/90፣ 20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች በእጣ ሙሉ በሙሉ ለተጠቃሚዎች እንደሚተላለፉ አስታውቀዋል።

በሰኔ ወር ለተጠቃሚዎች ከሚተላለፉት 32 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ 1ሺ 200 ቤቶች በ40/60 መርሃ ግብር ሲሆኑ፥ አብዛኛዎቹ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግን በ20/80 መርሃ ግብር ለተመዘገቡት የሚተላለፉ ናቸው ነው የተባለው።

የተጫነው፦ በሳሙኤል ዳኛቸው

Receive Ethiopian News, Movies and Videos by email. Sign up for Email alerts ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን፣ ጠቃሚ ምክሮችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜሎን ያስመዘግቡ።