አቶ ታደሰ ሲሳይ ስልጣነ ክህነታቸውን ቢገፈፉም አሁንም “ካህን ነኝ” ማለታቸውን አልተዉም
የአሌክሳንደሪያ፣ ቨርጂኒያ ሐመረኖህ ኪዳነ ምሕረት የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ አስተዳዳሪ “ቀሲስ” ታደሰ ሲሳይ በመባል የሚታወቁት ግለሰብ ክህነታቸውን ተገፈው በተራ ስም አቶ ታደሰ ሲሳይ ተብለው እንደሚጠሩ ውሳኔ ከተላለፈባቸው ዛሬ አንድ ዓመት ሞላው። ሙሉውን የተወገዙበትን መግለጫ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ። ቀሲስ ታደሰ ሲሳይ ሥልጣነ ክህነታቸውን ተገፈፉ ይህ ወሳኔ የተላለፈበት ምክንያት አቶ ታደሰ ሲሳይ የነበራቸውን ህጋዊ ትዳር አፍርሰው ከህገ ቤተክርስቲያን ውጭ የክህነት አገልግሎት ለበርካታ ዓመታት ሲያከናውኑ የነበረ በመሆኑና ከጥፋታቸው እንዲመለሱና ንስሐ እንዲገቡ የቀረበላቸውን ጥሪ አሻፈረኝ በማለታቸው ነው። አቶ ታደሰ ሲሳይ 1ኛ ጢሞቲዎስ ምዕራፍ 3 ቁጥር 1 እስከ 5 ላይ በማያሻማ ሁኔታ የተደነገገውን መለኮታዊ ሕግ ጥሰዋል። “…..ማንም ኤጲስ ቆጶስነትን ቢፈልግ መልካምን ሥራ ይመኛል የሚለው ቃል የታመነ ነው። እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል፤ የማይነቀፍ፥ የአንዲት ሚስት ባል፥ ልከኛ፥ ራሱን የሚገዛ፥ እንደሚገባው የሚሰራ፥ እንግዳ ተቀባይ፥ ለማስተማር የሚበቃ፥ የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ ነገር ግን ገር የሆነ፥ የማይከራከር፥ ገንዘብን የማይወድ፥ ልጆቹን በጭምትነት ሁሉ እየገዛ የራሱን ቤት በመልካም የሚያስተዳድር፤ ሰው ግን የራሱን ቤት እንዲያስተዳድር ባያውቅ፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ይጠብቃታል?…..”
ግለሰቡ አንዲት ባለትዳር ሴትን ከባሏ ለይተው በማማገጥና በውሽማነት በመያዝ እጅግ አስከፊና አሳዝኝ ከአንድ ካህን የማይጠበቅ ድርጊት መፈጸማቸውን የሴትየዋ የቀድሞ ባለቤት የነበሩት ሰው ባቀረቡት ማስረጃ ተረጋግጧል። ከዚህም በተጨማሪ አቶ ታደሰ ሲሳይ ከሌሎች ሴቶችም ጋር ዝሙት እንደሚፈጽሙ ነቀፋዎችና ትችቶች በተለያየ ጊዜ ሲቅርቡባቸው ቆይተዋል።ሆኖም ሰውየው በተደጋጋሚ ተመክረው ሊመለሱና ንስሃ ሊገቡ ባለመፈለጋቸው ምክንያት ለውግዘት እንደተዳረጉ ይታወሳል። በአቶ ታደሰ ሲሳይ ላይ ውግዘቱን ያስተላለፉት ካህናት የካንሳስ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ የሆኑት ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ፣የዋሽንግተን ዲሲ ርዕሰ አድባራት ደብረሰላም ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ የሆኑት ሊቀማዕምራን ቀሲስ ዶ/ር አማረ ካሳዬና የቨርጂኒያ የአቡነ አረጋዊ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ የሆኑት ቆሞስ አባ ኃይለ ሚካኤል ተከለኃይማኖት ናቸው። የውግዘቱ ሥነ ሥርዓት የተካሄደው በሕዝብ ፊት ሲሆን ይህንኑ ጉዳይ እንዲከታተል ከዚህ በፊት የተቋቋመው ኮሚቴ አባላትና ከተለየዩ አድባራት የመጡ ምዕመናንም ተገኝተው የነበረ መሆኑአይዘነጋም።
አቶ ታደሰ ሲሳይ ባለፈው ዓመት የካቲት 30 ቀን 2006 ዓ.ም. (ማርች 9, 2014) ስልጣነ ክህነታቸው የተሰረዘና ወደ ተራ ምዕመንነት የወረዱ መሆናቸው ቢገለጽላቸውም በማን አለብኝነትና በዕብሪት አሁንም ቤተክርስቲያንን ማርከሳቸውን ቀጥለውበታል። አቶ ታደሰ ሲሳይ እንደግል ንብረታቸው ያሻቸውን በሚሰሩባት በቨርጂኒያ ሐመረኖህ ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ውስጥ ከምዕመናን የሚሰበሰውን ገንዘብ በመርጨት ከአሜሪካ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ በዘረጉት መረብ በመጠቀም ክህነታቸው ተሰርዞ እያለና ይባሱን በዝሙት ተጨማልቀው የምንኩስና ማዕረግ ይዣለሁ በማለት ማጭበርበራቸውን ቀጥለውበት ምዕመናን “ያሁኑ ይባስ” አሰኝተዋል። አቶ ታደሰ ሲሳይ ካፈርኩኝ አይመልሰኝ በማለት ማወናበዳቸውን ለመሸፈንና እውነቱን አዛብቶ ለማቅረብ ለሬዲዮ መርሃግብር ማካሄጃ በርካታ የቤተክርስቲያን ገንዘብ እንዲባክን አድርገዋል። ከዚህ ጋር በአባሪ የተያያዘው መረጃ እንደሚያመለክተው “ኒው ወርልድ” ሬዲዮ ለሚባል ዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ የሚሰራጭ ሬዲዮ የስድስት ወር ክፍያ $4,200 የከፈሉበትንና ሌሎችንም ተዛማጅ መረጃዎችን ይመልከቱ። ታደሰ ሲሳይ አባሪዎች አገራችን ውስጥ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ቤተክርስቲያናት ለመቀደሻና ለማቁረቢያ የሚሆን እጣንና ዘቢብ በጠፋበትና በርካታ አብያተክርስቲያናት በእርጅና ምክንያት እየፈረሱ ባለበት ጊዜ አቶ ታደሰ ሲሳይ ተቃውሞ የሚያነሱ ምዕመናንን ለመክሰስና ከቤተክርስቲያን ለማራቅ በርካታ ገብዘብ ለጠበቃ፣ ለሬዲዮ ማደናገሪያ፣ እንዲሁም ለዘበኞች (ሴኩሪቲ) እያረጩት ይገኛል።
ይህንን ለትውልድ ሲያስጠይቅ የሚኖር በቤተክርስቲያን ላይ የተሰራ ወንጀልን በመሸፈን ኢትዮጵያ ድረስ የግንኙነት አውታር በመዘርጋት አቶ ታደሰ ሲሳይ በሐሰት የምንኩስና ማዕረግ እንዲያገኙ ያደረጉት በቅጥፈታቸውና በአወናባጅነታቸው የሚታወቁት አባ መላኩ (አቡነ ፋኑኤል) ናቸው። በአባ መላኩ አቀናባሪነት በአቡነ ማትያስ የሚመራው የኢትዮጵያው ሲኖዶስ ቢያንስ ሚስቱን በአቶ ታደሰ የተነጠቀውንና ልጆቹ የተበተኑበትን ምዕመን እምባ በማበስ አቶ ታደሰን አውግዞ ከስልጣነ ክህነታቸው ማስወገድ ሲገባው ቀድሞ በሌሎች ሶስት ካህናት በምዕመናን ፊት የተወሰነውን ውግዘት እንኳ ለማጽናት ወኔው ከድቶታል። የአቡነ ማትያስ ሲኖዶስ በዚህም ምክንያት በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 20 ቁጥር 28-30 የተጻፈው እየመሰከረባቸው እንደሆነ ለመገንዘብ አያዳግትም። “……..በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ።…”
በመጨረሻም፣ አቶ ታደሰ ሲሳይ አለቦታዎ ከቤተክርስቲያን መቅደስ ውስጥ መግባትዎንና አውደ ምሕረት ላይ መቆምዎን ትተው እንደ ተራ ምዕመን ነጠላዎትን አጣፍተው እንዲያስቀድሱና ተሰጥዎውን እንዲመልሱ እንዲሁም እንደማንኛውም ምዕመን እርስዎንም እውነተኛ ካህናትን “ይፍቱኝ” የሚያሰኝ ህሊና ይስጥዎት እንላለን። እርስዎ በተለይ ከአንድ ዓመት ወዲስ ስልጣነ ክህነትዎ ከተገፈፈብዎትና ከተወገዙ ወዲህ ለራስዎ ነፍስ እንጅ ለሌሎች ሊያስተሰርዩ ስለማይችሉ አለቦታዎ ከተቀመጡበት ቦታ ይወገዱ። በተለይም በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ አካባቢ የምትገኙ በተለያየ ቤተክርስቲያን ውስጥ የምታገለግሉ ካህናት ይህንን አብይ ጉዳይ ጠንቅቃችሁ እያወቃችሁ አባ መላኩን ላለማስቀየም ወይም ኢትዮጵያ ከመመላለስ ያግደናል ብላችሁ እውነተኛውን ነገር ከመመስከር የተለጎማችሁ አሁንም አልመሸባችሁምና የውግዘትና የተቃውሞ ድምጻችሁን በአቶ ታደሰ ላይ አሰሙ። የግብጽ ክርስቶያን ወንድሞቻችን እውነቱን መስክረው ሲሰየፉና መስዋዕትነትን ሲቀበሉ እያየን፣ እናንተ ግን በጣም ትንሹን ነገር ተደላድላችሁ ከተቀመጣችሁበት ወንበር ላይ ማከናወን ተስኗችኋል። ማፈሪያዎች ሆናችኋል። ክርስትና ስም ብቻ አይደለም ስራም ይጠይቃል። ክርስትና እውነቱን ተናግሮ የሚመጣውን መቀበል ነውና አስመስሎ መኖሩና ማምታታቱ ይብቃችሁ። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልቦና ይስጣችሁ። ሁላችንንም ልቦና ይስጠን። ሁላችንንም ሃጢያታችንን ይቅር ይበለን። አሜን።