አይኖች ሁሉ ወደ መገንጠል ያማትራሉ!

ሰሞኑን የማህበራዊ ሚዲያዎቻችን ልብ ብሎ ያየ ሰው መቼም አንድ ነገር መታዘቡ አይቀርም። የለየለት የብሄር እሰጣገባን የታዘበ ሰው የኢትዮጵያ ምጽዓት የደረሰ ይመስላል። በየካቲት 11 የህዋሀት ክብረ በዓል ላይ ትግራዊያን በደስታ ስካር ሲዋኙ፤ በፌሽታ ሲያከብሩ እና ድህረ መረቦቻቸውን ሁሉ በክልሉ ባንዲራ ሲያንቆጣቁጡ ከአንድነት ሃይሎች እና ከሚኖሶታ መንደር ደግሞ የጣዕረ ሞት ድምጽ ይሰማ ነበር። ታምራት ነገራ ለአልጀዚራ ‘በህዋሀት 40ኛ አመት ክብረ በዓል ላይ ቤቴን ዘግቼ ሳለቅስ አደርኩ’ እንዳለው ቀላል የማይባሉ ሰዎች ምሬታቸውን በተለያየ መንገድ ሲግልጹ ሰንብተዋል። እዚያ ማዶ ውስኪ ሲረጭ ከአትላንቲክ ማዶ ደግሞ በእንባ መታጠብ።
ከዚያ የቀጠለው የአድዋ በዓልም መልካም ነገር ይዞ አልመጣም። ለአንድነት ሃይሎች ፈንጠዚያን፤ ቀላል ለማይባሉ ኦሮሞዎች ደግሞ ከሆድ የማይወጣ ህመምን ያስታወሱበት ቀን ነበር። እነ ዳንኤል ብርሃኔ እና ጃዋር ሞሃመድ ጭራቁ ሚኒልክን ሲያብጠለጥሉ የአንድነት ሀይሎች ደግሞ እምየ ሚኒልክን ሲያወድሱ እና ሲያመልኩ እንዲሁ በሃሳብ ጦርነት ስንለበለብ ሰነበትን።
የሚኖሶታ ፖለቲከኞች በምናባቸው በፈጠሩት ሪፓብሊክ አማካኝነት በጀርመን ሃገር በሙኒክ ከተማ “Historical and Contemporary Relations between Europe and the Oromo.” በሚል አርዕስት የአንድ ብሄር እና አንድ አህጉር ታሪካዊ እና ወቅታዊ ግንኙነቶችን በተመለከተ ሊወያዩ ቀነ ቀጠሮ ይዘዋል።
ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ በማለታችን ያተረፍነው የብዙሃን ጥላቻ፤የህዝባችንን ስደት እና ሞት ነው ያሉ ቀላል የማይባሉ የአንድነት ብሎገሮች ደግሞ ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ታፔላን ወርውረን የአማራን መገንጠል ከልባችን ደግፈናል ፤ለተግባራዊነቱም የህይወት መስዋዕትነት ሳይቀር ለመክፈል ተዘጋጅተናል ሲሉ በአደባባይ አውጀዋል። ይህች እንቅስቃሴ በወያኔ በኩል ትንሽ ድንጋጤን ስታመጣ ቀላል ለማይባሉ ኦሮሞዎች ደግሞ ድሮም ሲፈልጓት የነበረች በመሆኗ ፈንጠዝያን አስከትላለች።
ከሃሳባዊ ጦርነቱ ባለፈ ደግሞ የአፋር ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ፤ የጋምቤላ ህዝቦች ነጻ አውጭ ግንባር። ትህዴን፤ ኦብነግ፤ኦነግ፤አርበኞች ግንቦት ሰባት እና የ አማራ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት በጦር ግንባር ለወከሉት ህዝብ እየተፋለሙ ይገኛሉ ።
አዎ ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን ቀኑ እየጨለመ መሆኑን መካድ አይቻልም። እንደ ቀልድ የተዘራው የዘር ፖለቲካ አፍርቶ እና ጎምርቶ እንደ ምስጥ ቀስ በቀስ እየበላን ኢትዮጵያ የምትባለውን ግንድ ቀንጥሶ ለመጣል የቀረው ትንሽ ጊዜ ብቻ ነው። የከፋፈለህ ግዛው ፖሊሲን ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት የተማረው ወያኔም የህዝቡን ሮሮ ላለመስማት ከማለ ይህው 24 አመታት ተቆጠሩ። ስለ አንድነት ስንቶች ታሰሩ፤ተሰደዱ፤ሞቱ። የአንድ የብሄር የበላይነት ይቁም እና የተባበረች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እንገንባ ያሉ በድሮ ስርዓት ናፋቂነት ተፈርጀው የሞት ጽዋቸውን ጨለጡ። ይህ መገፋት ደግሞ ውሎ አድሮ ጽንፈኝነት ወለደ። ኢትዮጵያ የሚባለው ትልቁ እና ቅዱሱ ማሰሪያ ገመድም ሊበጠስ ጫፍ ደረሰ። እነሆ በመሪር ለቅሶ የማንፈልጋትን አፍሪካዊት ዩጎዝላቪያን ለማየት ልንበቃ ነው።
አምላኴ ሆይ እባክህ ሞቴን ከዚያ በፊት አድረገው።
By Ay Anchi Ethiopia
The post አይኖች ሁሉ ወደ መገንጠል ያማትራሉ! appeared first on ሳተናው (Satenaw) – Latest & Current Ethiopian News, Breaking News,.