የኢትዮጵያ ምድር ሁሉ የኦሮሞ ምድር ነው (የአድዋ መንፈስ) – አማኑኤል ዘሰላም

1510887_345173532354659_8719836103482886979_nየሕወሃት መንግስት በመቶ ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ አዉጥቶ፣ ለሳምንታት ስለ ለካቲት 11 የሕወሃት 40ኛ አመት ሲለፍፍ ነበር። የተለያዩ የአፍሪካ መሪዎች በመቀሌ እንዲገኙ የተደረገ ሲሆን፣ ሽር ጉዱም መላው የኢትዮጵያ ህዝበ እስኪታዘብ ድረስ ጣራ ላይ ደርሶ ነበር። የምርጫ ቦርዱ ሃላፊ አቶ መርጋን ጨምር አሉ የተባሉ የመንግስት ባለስልጣን በመቀሌ ዉር ዉር ሲሉ ታዝበናል።

የሚያስገረመው ግን በነጋታው የካቲት 12 ቀን ፣ በግራዚያኒ የወደቁ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቻችንን ለማስታወስ ግን በስድስት ኪሎ አበባ ለማስቀመጥ የሞከረ አንድም ባለስልጣን አለመነሮ ነው።

ሁለት ሳምንት አልፎ ታላቁ የአድዋ ድል የሚከበረበት ጊዜ ደረሰ። በሕወሃት ዘንድ ለለካቲት 11 የተሰጠው ትኩረት አንድ መቶኛ እንኳን ለአድዋ ድል አልተሰጠም። ሆኖም ኢትዮጵያዊያን ፣ በራሳቸው ፣ በየማእዘናቱ ይሄን ታልቅ የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የጥቁር ህዝብ ድል በመዘከርና በማስታወስ አሳልፈዉታል።

አንዳንድ አክራሪ ዘረኖች፣ የአድዋ ድል የአቢሲኒያዎች (ትግሬዎችና አማራዎች የሚሏቸው) እንደሆነ ይናገራሉ። አጼ ሚኒሊክን የ«ኦሮሞ ጠላት» እንደሆኑ ለማሳየት ይሞከራሉ። ሆኖም ሐቁ ግን የተለየ ነው። የአጼ ሚኒሊክ ጀነራሎችን ወታደሮች በአብዛኛዉ ኦሮሞዎች ነበሩ። ነፍጠኞች የሚባሉት በአብዛኛው ኦሮሞዎች ነበሩ።

ዶር መራር ጉዲና አንድ ወቅት የተናገሩትን ላካፍላችሁ፡

«የድርጅታችሁ አቋም በአድዋ ላይ ምንድን ነው ?» ብሎ አንድ ግለሰብ ሙኒክ ላይ በተደረገ ስብሰባ ዶር መራራ ጉዲናን ይጠይቃል። ዶር መራራ እንዲህ ሲል ይመልሳሉ፡

«አንዳንድ ፖለቲካ ያልገባቸው የኦሮሞ ልጆች የሚሉትን አትስሙ፤ ከአንድ ወይም ሁለት የማይበልጡ የአማራ ጀነራሎችና፣ ከአንድ ወይም ሁለት የማይበልጡ የትግራይ ጀኔራሎች በስተቀር በጦርነቱ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱት የኦሮሞ ጀኔራሎች ነበር። ለአብነትም የወሎ ጦር የተመራው በወሎ ኦሮሞ፣ የልጅ ኢያሱ አባት ንጉስ ሚካሌ ነበር። የጎንደርን ጦር የመሩት ፣ የጣይቱ ብጡል ወንድም ፣ ወሌ ብጡል ነበሩ። የጎጃምን ጦር የመሩት ፣ ንጉስ ተክለ ሃይማኖት/ ራስ አዳል ወደ ክርስቱና የተለወጡ የጎጃም ኦሮሞ ነበሩ። የሐረርን ጦር የመሩት የአጼ ኃይለስላሴ አባት ፣ ራስ መኮንን የሸዋ ኦሮሞ ነበሩ። ከየጁ ኦሮሞ የመጣችሁ የጣይቱን ሚና ሳታወቁት አትቀርም። “ገበየሁ ሲሞት ተተካ ባልቻ፣ መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ” የሚባለውን ሳትሰሙ አትቀርሙ። ፊታዉራሪ ሃብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴም የንጉሱ አማካሪ ነበር”
ዶር መራራ ይሄን ጠንቅቀው ስለሚያወቁ ነው ኦሮሞ ከኢትዮጵያ ሊገነጠል አይችልም ያሉት። እንዴት ግንድ ከቅርንጫ ይገነጠላል ብለው ብዙ ጊዜ የተናገሩት። እውቁ ጀነራል ጃጋማ ኬሎም ተመሳሳይ ነገር ነው የተናገሩት።

እንግዲህ በአድዋ ጦርነት እንዳየነው፣ ኦሮሞው፣ ትግሬው ሁሉም ዜጋ፣ ለኢትዮጵያ አንድነት ቆሞ፣ ደሙን አፍሶ ያቆይዋት አገር ናት ኢትዮጵያ። ይች ኢትዮጵያ ነው ህወሃት በዘር እየሸነሸነ ያለው።

ከሚለያየን የሚያዛምደን ይበልጣል። አንዳንድ አክራሪ የኦሮሞ ብሄረተኞች፣ ኦሮሞዎች አሁን ያለችዋን ኢትዮጵያ በማቅናት አንጻር የነበራቸው ቁልፍና ዋና ሚና መመልከት አለባቸው። ከነርሱ ስለተለይን እና ኢትዮጵያዊነት ላይ ስላተኮረን፣ “ነፍጠኛ ፣ አምራ “ እያሉ የሚተቹን እኛ የኦሮሞ ደም እንዳለብን መርሳት የለባቸውም። ኦሮሚያ የሚሏትን ኦነግ-ፈጠር ድራማ ማቆም አለባቸው። ኦሮሚያ የሚባል ነገር የለም። ጎጃም፣ ወሎ፣ ጎንደር፣ ሸዋ …እያለ ሁሉ የኦሮሞ ምድር ነው።

ይልቅ ማተኮር ያለብን ይሄ የኢትዮጵያ ግንድ የሆነው ኦሮሞው፣ ቋንቋዉ፣ ባህሉ በአጠቃላይ የዜግነት መብቱ ከማንም ባልበለጠናና ከማንም ባልተናነሰ መልኩ፣ በእኩልነት እንዲከበርለት መታገሉ ላይ ነው።

ሕወሃቶች ወለጋዉን አንተ ኦሮሞ ነህ፤ ጎጃሜዉን አንተ አማራ ነህ ይሉታል። ጎጃሜው አማርኛ ብቻ እንዲማር፣ ወለጋው ኦሮምኛ ብቻ እንዲማር በማድረግ እንዳይገባቡ ፣ እንዳይተማመኑ እያደረገ ነው።፡ግን ትንሽ ወረድ ብንል፣ ጎጃምና ወለጋ አማርኛና አፋን ኦሮሞ ከመናገራቸው ዉጭ አንድ ናቸው። ወለጋ ያሉ ዘራቸው ቢታይ ከጎጃም የመጡ ብዙ አሉበት። ጎጃም ያሉ ቢታይ ከወለጋ የመጡ ብዙ አሉበት። የተደባለቁ ናቸው።፡አንድ ናቸው። ልዩነቱ ቋንቋ ነው። ቋንቋ ደግሞ አፋን ኦሮሞን እና አማርኛ የኢትዮጵያ ፌዴራል ቋንቋ በማድረግ ፣ ጎጃሜዉም፣ ወለጋዉን አማርኛና አፋን ኦሮሞ፣ ሁለቱን ቢማሩ ቢማር አሉ የሚባሉ ልዩነቶቻቸው ያከትማሉ ማለት ነው።

እንግዲህ ይህ ነው የአድዋ መንፈስ ! የአንድነት መንፈስ ! የትብብር መንፈስ !
ሁላችንም ለአገራችን እንነሳ። አገራችን የሁላችንም ናት። ጥቂቶች በዘር ከፋፍለዉን፣ ነጻነታችንን ገፈው በአገራችን እንደባሪያ ሲያደረጉን ዝም ማለት የለብንም። ሰው ያለነጻነቱ ምንድን ነው ? ?

 

The post የኢትዮጵያ ምድር ሁሉ የኦሮሞ ምድር ነው (የአድዋ መንፈስ) – አማኑኤል ዘሰላም appeared first on ሳተናው (Satenaw) – Latest & Current Ethiopian News, Breaking News,.