የአመራሮቹ ጠበቆች በፖሊስ ላይ ‹‹አካልን ነፃ የማውጣት ክስ›› ሊመሰርቱ ነው

የሰማያዊ ፓርቲ አመራር የሆነው አግባው ሰጠኝን ጨምሮ የአንድነትና የመኢአድ አመራሮች ጠበቆች በፖሊስ ላይ አካልን ነፃ የማውጣት ክስ ሊመሰርቱ ነው፡፡ ፖሊስ ዛሬ የካቲት 25/2007 ዓ.ም በተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮቹ ላይ የመጨረሻውን ምርመራ ሊያሰማ ቀጠሮ ይዞ የነበር ቢሆንም በቀጠሮው መሰረት አመራሮቹ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡

በዛሬው ዕለት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮቹ ባልቀረቡበት ፖሊስ ምርመራዬን ጨርሻለሁ ብሎ መዝገቡን እንደዘጋ ለፍርድ ቤት ገልጾአል፡፡ ሆኖም በፖሊስ ምርመራ መሰረት አቃቤ ህግ ክስ መመስረት አሊያም ተጠርጣሪዎቹ መለቀቅ ቢኖርባቸውም ከሁለቱ አንዱም ባልተደረገበት ሁኔታ ተጠርጣሪዎቹ በህገ ወጥ መንገድ እስር ቤት እንዲቆዩ ተደርገዋል በሚል የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ነገ የካቲት 26/2007 ዓ.ም በፖሊስ ላይ አካልን ነፃ የማውጣት ክስ ሊመሰርቱ መሆኑን የሰማያዊ ፓርቲ የህግ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ይድነቃቸው ከበደ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ የህግ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ይድነቃቸው ከበደና የአመራሮቹ ጠበቆች ተጠርጣሪዎቹ ለምን ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ፣ ምርመራው ተጠናቅቋል ከተባለ በኋላ ለምን በነፃ እንዳልተለቀቁ ወይንም አቃቤ ህግ ክስ እንዳልመሰረተ ለማጣራት ማዕከላዊ እስር ቤት ድረስ በማቅናት ለማጣራት ቢሞክሩም ፖሊስ ‹‹በእኔ በኩል አስፈላጊው ምርመራ አድርጌ ጨርሻለሁ፡፡ አይመለከተኝም፡፡ የአቃቤ ህግ ጉዳይ ነው፡፡›› ብሏል፡፡ በተመሳሳይ ‹‹አቃቤ ህጎች ስብሰባ ላይ ናቸው፡፡›› በመባሉ ስለ ጉዳዩ መረጃ ማግኘት እንዳልተቻለ የሰማያዊ ፓርቲ የህግ ጉዳይ ኃላፊ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡