በዝቋላ ገዳም ዙሪያ የተቀሰቀሰው የእሳት ቃጠሎ እየተዛመተ ነው

  • የሄሊኮፕተር እገዛ አልያም የውኃ ቦቴ መኪኖች ድጋፍ እየተጠየቀ ነው

To_Ziquwala_3
በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም፣ ትላንት ጠዋት የተቀሰቀሰው የእሳት ቃጠሎ አሞራ ገደል በሚባለው አቅጣጫ መዛመቱ ተገለጸ፡፡

በሰሜን በኩል ወንበር ማርያም እየተባለ በሚጠራው የገዳሙ መውጫ ትላንት ጠዋት 2፡00 የተቀሰቀሰው ቃጠሎ፣ በአዱላላ ወረዳ ሠራተኞችና በነዋሪው ሕዝብ ርብርብ ማምሻውን መጥፋቱ ከተገለጸ በኋላ ነው አሞራ ገደል በሚባለው የገዳሙ ደቡባዊ ገጽ በዛሬው ዕለት 5፡00 ላይ ዳግመኛ መቀስቀሱ የተሰማው፡፡

ቃጠሎው፣ በአካባቢው ከባድ ነፋስ እየበረታ ከገደሉ ሽቅብና ወደ ጎን ወደ አዱላላ አቅጣጫ የተወሰነ የደኑን ክፍልና እዳሪ መሬት እየበላ በአስጊ ፍጥነት እየተስፋፋ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡ አኹን ባለው አካሔድ ሳይገታ ወደ ምሥራቅ ከዞረና ጠበል ሜዳውን ካገኘ ወደ ደኑ ስለሚገባ በእጅጉ አውዳሚ እንደሚኾን የገዳሙ መነኰስ ተናግረዋል፡፡

ከቦታው ገደላማ መልክአ ምድራዊ ገጽታ አንጻር የሚያፍነው ጢስና የቃጠሎው ፍጥነት የመከላከል ሥራውን አስቸጋሪ እንዳደረገው ያስረዱት የገዳሙ መነኰስ፣ አመቺ የሚኾነው አስቸጋሪውን ዐቀበት በመውጣት ለሰው ኃይሉ ውኃ ማቅረብ በሚችሉ መኪኖች አልያም በአየር ርጭት በመኾኑ ከደብረ ዘይት አየር ኃይል የሄሊኮፕተር አልያም የቦቴ መኪኖች እገዛ በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በኩል እንዲጠየቅ አመልክተዋል፡፡