የዐድዋው ዘማች የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር: አለቃው ቀንደኛው አማሳኝ ኃይሌ ኣብርሃ ባነገሠው ሙስናና ዓምባገነናዊ አስተዳደር ተቸግሯል
- በጨረታ የተሰጠ የ61 ሚ. ሕንፃ በዲዛይን ክለሳ ስም ያለጨረታ ብር 175 ሚ. ተደርጓል
- ሢሦ ለማይሞላ ሥራ የተፈጸመው ከብር 25 ሚ. በላይ ክፍያ እንዲመረመር ተጠይቋል
- ሊቀ ጳጳሱ ያልፈቀዱት የብር 40 ሚልዮን የኪራይ ውል ከንግድ ባንክ ጋራ ተፈጽሟል
- ከባንኩ የተለቀቀው ብር 14 ሚ. ያህል ገንዘብ በሕገ ወጥ ክፍያ እንዳይባክን ተሰግቷል
- ያለውድድር በተሠራ ፕላን ከብር 12 ሚ. በላይ የተገመተ ሕንፃ ያለጨረታ ሊሰጥ ነው
- ለካህናቱ የተደረገው የብር 250 ጭማሪ ሀ/ስብከቱ ያላጸደቀው ‹‹መደለያ›› ነው ተብሏል
* * *
- አለቃው ‹‹ፓትርያርኩ በእጄ ናቸው›› በሚል ማናለብኝነት ከተጠያቂነት ውጭ ኾነዋል
- ችግሩን ለሀገረ ስብከቱ ያጋለጡት የደብሩ ዋና ተቆጣጣሪ ከሥራና ከደመወዝ ታግደዋል
- ነጻ አስተዋፅኦ ያበረከቱ የልማት ኮሚቴው ባለሞያዎች በአለቃው ተመርረው ተበትነዋል
- ሰ/ት/ቤቱ ለኮርስ ከሚያሠራው ሕንፃ ለንግድ ቤት ልቀቁ በሚል ጫና እያደረጉበት ነው
- የፓትርያርኩን ሲኖዶሳዊ ውሳኔ እግድ የተቃወሙ አመራሮችን አንለቃችኹም ብለዋል
* * *
- ‹‹ፓትርያርኩ በእጄ ናቸው፤ ማንም ምንም አያመጣም፤ አላርፍ ካልክ ከገጸ ምድር አጠፋሃለኹ፡፡››
/የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ አስተዳዳሪ መልአከ መንክራት ኃይሌ ኣብርሃ ሕገ ወጥ አካሔዱን በአስተሳሰብና በአሠራር የሚቃወሙ አገልጋዮችንና ምእመናንን በማሸማቀቅ የሚታወቅበት የዛቻና ማስፈራሪያ ቃል/
/ምንጭ፡- አዲስ አድማስ፤ ቅጽ ፲፮ ቁጥር ፯፻፹፱ የካቲት ፳፩ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም./
ዐድዋን ጨምሮ በተለያዩ ጦርነቶች በመዝመትና በነገሥታት መናገሻነቱ የሚታወቀው ታሪካዊው የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን ባለዕዳ በሚያደርግና አገሪቱን በሚጎዳ ከፍተኛ የገንዘብ ብክነትና የመልካም አስተዳደር ችግር ውስጥ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡
ደብሩ በራስ አገዝ ልማት ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የጠቀሱ የደብሩ ሠራተኞችና ምእመናን በሰነድና በቃል ባቀረቧቸው አስረጅዎች፣ ‹‹በልማቱ በማመካኘት የሚታየው የሥራ ሒደት መልሶ ልማቱን ሊያኮላሽና ቤተ ክርስቲያኒቱን ለአደጋ የሚያጋልጥ ነው፤›› ብለዋል፡፡
በተለይም ከ፳፻፮ ዓ.ም. መጀመሪያ አንሥቶ በደብሩ አስተዳደሪ መልአከ መንክራት ኃይሌ ኣብርሃ የሚፈጸሙት የመዋቅር ጥሰትና መመሪያን ያልጠበቁ ግለሰባዊ አሠራሮች በመባባስ ላይ እንዳሉ ነው ያስረዱት፡፡ ለዚኽም ከሕንፃ ግንባታና የኪራይ ውሎች ሕጋዊነት፣ ከኪራይ ገቢ አሰባሰብና ከወጪዎች አግባብነት አኳያ የደብሩ ገንዘብ አላግባብ እንዲባክን ተደርጓል ያሉባቸውን ጉዳዮች በማሳያነት አቅርበዋል፡፡
ደብሩ ‹‹ዳዊት ወንድሙ›› በተባለ የሕንፃ ሥራ ተቋራጭ በማሠራት ላይ የሚገኘው ባለአራት ፎቅ የንግድ ማዕከል ሕንፃ፣ በሰኔ ወር ፳፻፬ ዓ.ም. በውስን ጨረታ ባወጣው ማስታወቂያ መሠረት በሰበካ ጉባኤውና በልማት ኮሚቴው ጥምር የጋራ ስብሰባ ለአሸናፊው ድርጅት የተወሰነና የኮንትራት ውሉም በብር 61‚234‚885.02 ጠቅላላ ወጪ የተፈጸመ እንደነበር ተገልጧል፤ አማካሪ ድርጅቱ የተቀጠረውም በግልጽ አሠራር ተለይቶ ሲኾን በግንባታው ሒደትና በክፍያዎች አፈጻጸም የልማት ኮሚቴው ቴክኒክ ክፍል ሞያዊ ይኹንታና ማረጋገጫ በመስጠት ልማቱን ለማገዝ ጥረት አድርጎ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡
ውሉ እንደ ቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ በማዕከል (በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት) ተፈቅዶ ግንባታው እየተካሔደ ባለበት ኹኔታ፣ የደብሩ አስተዳደር በዲዛይን ክለሳ ሰበብ የግንባታ ዋጋውን ከዕጥፍ በላይ በማናር የሥራ ውሉን መቀየሩ ተመልክቷል፡፡ አልፋ አማካሪ መሐንዲሶች የተሰኘውን የቀድሞውን አማካሪ መሐንዲስ በማሰናበት ‹‹የዲዛይን ክለሳና ተያያዥ ሰነዶች ፍተሻ በማስፈለጉ›› በሚል ዳንኤል አሰፋ ፕራክቲሲንግ አርክቴክቸር የተባለ አማካሪ ያለምንም ግልጽ መመዘኛና ውድድር በጥር ወር መጀመሪያ ላይ ቀጥሯል፡፡ ከደብሩ ዋና ጸሐፊ ጋራ ባለው ግለሰባዊ ትውውቅ የመጣው አማካሪ መሐንዲስ ያለውድድር ለሠራው የፕላን ማሻሻያ ብር 80‚500 የተከፈለ ሲኾን የግንባታ ወጪውም ከብር 175 ሚልዮን በላይ እንዲንር መደረጉ ታውቋል፡፡
የኮንስትራክሽንን ሕጉን በመጣስ ያለጨረታ የተሰጠው ‹‹የፕላን ማሻሻያ›› እና የቃለ ዐዋዲውን ድንጋጌ በመተላለፍ ሀገረ ስብከቱ ባልፈቀደው ‹‹የተከለሰ ዲዛይን›› መቀጠሉ የተገለጸው ግንባታ፣ በአነስተኛ ግምት ከብር 80 ሚልዮን ያላነሰ የወጪ ልዩነት ቢታይበትም እንደማሻሻያ የተጨመሩት የአሳንሰርና የኤሌክትሪክ ዝርጋታዎች የተጠቀሰውን ወጪ ምክንያታዊ ለማድረግ እንደማይበቁ ተገልጧል፡፡ ሕንፃው ከጠቅላላ ሥራው በሢሦ ደረጃ በሚገኝበት በአኹኑ ደረጃው እንዲከፈል የታዘዘው ወጪ ከብር 25‚536‚438.98 በላይ መድረሱ፣ ሥራው በማዕከል ከተፈቀደው ውጭና በተለየ ውል እየተካሔደ መኾኑን እንደሚያረጋግጥ በአስረጅነት ተጠቅሷል፤ የልማት ኮሚቴው ቴክኒክ ክፍል የግንባታ ጥራት ምስክርነት ያልተደመጠበትና የጋራ ውሳኔና ስምምነት ያላረፈበት በመኾኑም ለተቋራጩ ሲፈጸም የቆየው ክፍያ አግባብነት በገለልተኛ አማካሪ መረጋገጥ እንደሚገባው ተጠይቋል፡፡
በዲዛይን ክለሳ ስም ከ175 ሚልዮን በላይ የናረው የግንባታ ወጪ በተጋነነ ዋጋ በሚፈጸሙ የሥራ ውሎች አላግባብ እንዲባክን እየተደረገ ስላለው የደብሩ ገንዘብ ኹነኛ መገለጫና አስቸኳይ እርምት የሚያስፈልገው ነው የሚሉት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ደብሩን በጎበኙበት ጥር ወር አጋማሽ ግንባታው የሚጨርሰው ጠቅላላ ወጪ እንደኾነ ተደርጎ በሪፖርት እስከ መገለጽ መድረሱ በእጅጉ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡ ከሕንፃ ግንባታው በተጨማሪ በዕድሳትም ስም ወጪ የተደረገው እስከ ብር 60‚000 ከፍተኛ ገንዘብ ተገቢው የደረሰኝ ማስረጃ ሳይቀርብ እንዲወራረድ አስገዳጅ ትእዛዝ በአስተዳደሪው እንደሚሰጥ በአቤቱታ አቅራቢዎቹ ተብራርቷል፡፡
የደብሩ ይዞታዎች በኾኑ ኹለት ሕንፃዎች ላይ ቅርንጫፎችን ለመክፈት የደብሩ አስተዳደር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰሜን አዲስ አበባ ዲስትሪክት ጋራ ያደረገው የኪራይ ውል የቃለ ዐዋዲውን ድንጋጌ የጣሰና ‹‹ሀገረ ስብከቱ ምን አገባው›› በሚል የተፈጸመ እንደኾነ ነው የደብሩ ሠራተኞች የሚያስረዱት፡፡ የደብሩ አስተዳደር መስከረም ፰ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ከዲስትሪክቱ ጋራ በፈጸመው የዐሥር ዓመት የኪራይ ውል፣ የአቡነ ጴጥሮስ ቅርንጫፍ እና መሀል ፒያሳ ቅርንጫፍ ለመክፈት ብር 12 ሚልዮንና ብር 28 ሚልዮን በድምሩ ብር 40 ሚልዮን እንዲከለፈው መስማማቱ ታውቋል፡፡
አስተዳደሩ በውሉ መሠረት የኪራይ ክፍያው እንዲለቀቅለት ባንኩን የጠየቀ ከመኾኑም በላይ ስለቅድመ ክፍያው አፈጻጸም በጻፈው ደብዳቤ መሠረት እስከ አኹን ከብር 14 ሚልዮን ያላነሰ በቁጠባ ሒሳቡ ገቢ እንደተደረገለት ነው የተጠቆመው፡፡ በቃለ ዐዋዲው አንቀጽ 12(8) መሠረት፣ በሀገረ ስብከቱ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ሳይፈቅዱና መመሪያ ሳይሰጡበት በተፈጸመው ውል የተገኘው ከፍተኛ ግምት ያለው የኪራይ ገንዘብ፣ መመሪያን ባልጠበቁ ከፍተኛ ክፍያዎች ሊባክን እንደሚችል አቤቱታ አቅራቢዎቹ ስጋት አላቸው፡፡
በዚህ ረገድ ለተቋራጭ መሐንዲሱና ለአማካሪው በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ብር ወጪ እየተደረገ መሰጠቱ የሚመለከታቸውን የሥራ ሓላፊዎች ማስጨነቁን ሠራተኞቹ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ተቋራጭ መሐንዲሱ ብድር ጠይቀዋል›› በሚል አራት ሚልዮን ብር በብድር መሰጠቱ በምሳሌነት ተወስቷል፡፡ ብድሩ ‹‹ለሥራው በጊዜ መፋጠን አስተዋፅኦ ስላለው›› በሚል የተፈቀደ ቢኾንም እንዲከፈል የታዘዘው ገንዘብ የሚመለስበት ዝርዝር ኹኔታ ሳይብራራና የሚመለከታቸው ክፍሎች ሐሳብ ሳይካተትበት እንደኾነ ተገልጧል፡፡
ለልማት መዋል የሚገባው የደብሩ ገንዘብ በብድር መልክ የተሰጠው ባለዕዳው ተቋራጭ፣ ደብሩ ከሚያከራያቸው ቤቶችና ቦታዎች ላይ ለጋራዥና ለመጋዘን ከተከራየበት ጊዜ ጀምሮ ከብር 420‚000 በላይ የኪራይ ውዝፍ ያለበትና ዕዳውን እንዲከፍል በተደጋጋሚ ቢጠይቅም በአስተዳደሩ በኩል የማስፈጸም ዳተኝነት መታየቱ ተዘግቧል፡፡ ይብሱኑ ተቋራጩ ከደብሩ በስተምሥራቅ በብር 12 ሚልዮን ብር ወጪ ይገነባል ለተባለው ሕንፃ ያለውድድር ለሠራው ፕላን ብር 35‚000 ተከፍሎታል፤ ፕላኑ በገለልተኛ ባለሞያ ባልተገመገመበትና የግንባታ ወጪ ዝርዝር ባልቀረበበት ኹኔታም የተባለውን ባለኹለት ፎቅ ሕንፃ እንዲሠራ ያለጨረታ የሥራ ውል ለመስጠት መታሰቡ ስጋታቸውን ከፍ እንዳደረገው ሠራተኞቹ አስረድተዋል፤ ባለዕዳነቱ ከመንግሥት ቫትም ጭምር እንደኾነ ነው አክለው የሚናገሩት፡፡
መዋቅራዊ አሠራርንና የሌሎችን የሥራ ሓላፊነት በማናለብኝነት በመጣስ እየተፈጸመ ነው በተባለው የገንዘብ ብክነትና የመልካም አስተዳደር ችግር ዋነኛ ተጠያቂ የተደረገው የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ መንክራት ኃይሌ ኣብርሃ፣ የቢሮ ሠራተኞችንና ባለሞያዎችን ለየብቻቸው በጽ/ቤት እየጠራ በዛቻ ቃል በማስፈራራትና በማሸማቀቅ በዋናነት ተጠቅሷል፡፡ የኃይሌ ኣብርሃ አስተዳደር በደብሩ ስለሚፈጽመው ከፍተኛ የገንዘብ ብክነትና የአስተዳደር በደል ተደጋጋሚ መግለጫ ቢያቀርቡም ተቀባይነት ያጡት የደብሩ ዋና ተቆጣጣሪ አቤቱታቸውን ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና በሀገረ ስብከቱ ለፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ማቅረባቸውን ተከትሎ ከየካቲት ፰ ቀን ጀምሮ ከሥራቸውና ከደመወዛቸው በግፍ መታገዳቸው ታውቋል፡፡
‹‹ቅዱስ ፓትርያርኩ በእጄ ናቸው፤ ማንም ምንም አያመጣም፤ በሰላም አብሮኝ የማይሠራ ካለ ከገጸ ምድር አጠፋዋለኹ›› የሚሉ ኃይለ ቃሎችን በየስብሰባውና በየመድረኩ በመናገር ሐሳብ በነጻነት እንዳይራመድ ምክንያት በመኾኑ ከመስከረም ወር ወዲኽ ሞያዊ አስተዋፅኦዋቸውን ለደብሩ ልማት ዐሥራት ለማድረግ የተሰባሰቡት የልማት ኮሚቴው ቴክኒክ ቡድን ብዙኃን አባላት በዘለፋው ተመርረው መበተናቸውና የቀሩትም በጥቅም የተሳሰሩቱ መኾናቸው ተገልጧል፡፡ ከጥር ወር ጀምሮ ሀገረ ስብከቱ ሳያጸድቀው በገዛ ፈቃዱ ለካህናቱ ብር 250 ጭማሪ ማድረጉ ‹‹በይሉኝታ መያዣና መደለያ›› ነው ተብሏል፡፡

ማንአለብኝ ባዩ ኃይሌ ኣብርሃ፣ የደብሩ ሰንበት ት/ቤት በአባላቱ አስተዋፅኦና በልመና ለሚያሠራው ሕንፃም ምሕረት የለውም፡፡ በቦታ መጣበብ መርሐ ግብሮቹ እየተስተጓጎሉ የተቸገረ ሰንበት ት/ቤቱ÷ ለኮርስ(ሥልጠና)፣ ለቤተ መጻሕፍትና ለስብከተ ወንጌል አዳራሽ ዐቅዶ በደብሩ ሰሜናዊ ምዕራብ ከሚያሠራው ሕንፃ ወለሉን ለንግድ ቤት ኪራይ ካለቀቃችኹልን በሚል ማስገደጃ ጨርሶ ለመንጠቅ በማሰቡ ከአመራሩና አባላቱ ጋራ ፍጥጫ ውስጥ ገብቷል፡፡ ‹‹ምእመናን ናችኹ፤ አያገባችኹም ልንላቸው ይገባል›› ለሚለው ኃይሌ ኣብርሃ እንደኾን የሰንበት ት/ቤት አገልግሎት ‹‹ደግሶ ከማብላትና ጠላ ከማጠጣት›› የማያልፍ እንደኾነ በራሱ አንደበት በይፋ ነግሮናል!! /መስከረም ፳፯ ቀን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አዳራሽ፣ ጥቅምት ፱ ቀን በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ የተናገረውን ከቪዲዮው ይመልከቱ/
አቤቱታ አቅራቢ ሠራተኞቹና ምእመናኑ በመጨረሻም፣ የሕዝብ ሀብት የኾነችው ቤተ ክርስቲያን ‹‹በልማት እየተመካኘ ተገቢ ባልኾነ የሥራ ሒደት በዕዳ እንዳትዘፈቅ፣ የሠራተኛው የሥራ ዋስትና አደጋ ላይ እንዳይወድቅ›› አሳስበዋል፤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትም ጥንታዊውንና ታሪካዊውን ደብር የሚታደግ ፈጣንና ፍትሐዊ ውሳኔ እንዲሰጥም ተማፅነዋል፡፡
ከመስከረም ወር ፳፻፯ ዓ.ም. ጀምሮ ደብሩን በዓምባገነንነት ማስተዳደር ላይ የሚገኘው መልአከ መንክራት ኃይሌ ኣብርሃ ሠራተኞችና ምእመናን በሰነድና በቃል ማብራሪያ አስደግፈው ስለሚያነሷቸው አቤቱታዎች የበኩሉን ምላሽ እንዲሰጥ በስልክ ለመጠየቅ እንደተሞከረ ተመልክቷል፡፡ ይኹንና ‹‹የምእመናን አቤቱታ እንድትቀበሉና ይህን ጉዳይ እንድትመረምሩ ሥልጣን የሰጣችኹ ማን ነው?›› በማለት የመለሰ ሲኾን፣ በአካል ካልኾነ በቀር በስልክ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመኾኑን ቢገልጽም ቀጠሮ እንዲይዝ ሲጠየቅ ግን ስልኩን በጠያቂዎቹ ጆሮ ላይ መዝጋቱ ነው የተዘገበው፡፡
ቤተ ክርስቲያንን በግብረ ሙስና በማዋረድና አባቶችን በመዝለፍ ቀኖናዊ ምክርና ተግሣጽ እንዲሰጣቸው በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከተወሰነባቸው አማሳኞች ቀንደኛው ኃይሌ ኣብርሃ፣ ፓትርያርኩ አፈጻጸሙ እንዲታገድ በማድረጋቸው የታሪካዊውን ካቴድራል ሀብት ያለተጠያቂነት መመዝበሩን ተያይዞታል፡፡ ከዚኽም አልፎ የአ/አበባ ሀ/ስብከትና የሀ/ስብከቱ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የካቲት ፰ ቀን ከ160 የሰንበት ት/ቤት አመራሮች ጋራ ባካሔዱት ውይይት የፓትርያርኩን እገድ በመቃወማቸው ‹‹እንከሣችኋለን፤ አንለቃችኹም›› እያለ በመዛት ላይ ይገኛል – ከተጠያቂነት ውጭ በዓምባገነንነትና ምዝበራ ጎዳና የቀጠለው ኃይሌ ኣብርሃ!
ከነገ በስቲያ ለ፻፲፱ኛ ጊዜ የሚከበረው የዐድዋ ድል በዓል በብሔራዊ ደረጃ መከበር የጀመረው በመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን እንደኾነ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ ዐድዋን ጨምሮ በማይጨውና በሰገሌ ጦርነት የዘመተው ታቦተ ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጣው ከአምቦ አካባቢ ልዩ ስሙ ዱላ ቆሪቻ ከሚባል ቦታ ነው፡፡ አንድ አርሶ አደር በስፍራው ሲያርስ አይቶ ለዐፄ ምኒልክ አስረክቧል፡፡ ታቦቱ ለተወሰነ ጊዜ በቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ከተቀመጠ በኋላ ሐምሌ ፳፫ ቀን ፲፰፻፸፯ ዓ.ም. ወደ ገነተ ጽጌ መጥቷል፡፡
ዐፄ ምኒልክ ወደ ዐድዋ ሲዘምቱ መጀመሪያ ወደዚኽ ቤተ ክርስቲያን መጥተው ጸሎት አድርሰው በድል ቢመለሱ ዋናውን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ሊያሠሩ ስእለት ተሥለው ነበር፡፡ ከዐድዋ መልስ ዐሥር ዓመታት ቆይተው የካቲት ፳፫ ቀን ፲፱፻ ዓ.ም. ዐፄ ምኒልክ፣ መኳንንቱና ሕዝቡ በተሰበሰበበት በግብፃዊው ጳጳስ በአቡነ ማቴዎስ መሠረቱ ተጣለ፡፡
ሥራውን ለማፋጠን ዐጤ ምኒልክ የጢስ ባቡር ከአውሮፓ አስመጥተው ነበር፡፡ የደብሩ መገንቢያ ድንጋይ የተመላለሰው የሰርኪስ ባቡር በሚባለው ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ በኾነው በዚኽ መኪና ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያኑ አርኪቴክት አርፋኒዲስ የተባለ ግሪካዊ ሲኾን መሐንዲሱ ደግሞ ሙሴ ካስታኛ የተባለ ጣልያናዊ ነበር፡፡ የግንባታው ወጪ በአብዛኛው የተሸፈነው በመንግሥት ወጪ ነው፡፡ ዐፄ ምኒልክ 40‚000 ብር አዋጥተዋል፡፡ ደንጊያው ከኮተቤ፣ ቀበናና አምቦ፤ ጉልላቱ የተሠራበት ብረት ደግሞ ከፈረንሳይ የመጣ ነው፡፡
ፋሽስት ኢጣልያ በአምስት ዓመት ወረራው ወቅት ቤተ ክርስቲያያኑን የሚያፈርስበት ምክንያት ሲፈልግ ቆይቶ፣ ግራዝያኒ ላይ ቦምብ መወርወሩን ሰበብ በማድረግ ‹‹የአርበኞች መደበቂያ ነው›› በማለት ሕንፃውን ጋዝ አፍስሶ ለማቃጠል ቢሞክርም ሕንፃው ከመሠረቱ አልፈረሰም ነበር፡፡ ከውጫዊ ክፍሉ ይልቅ የተጎዳው ውስጣዊ ክፍሉ ነበር፡፡ ግምጃ ቤቱና መጻሕፍቱ ሲቃጠሉ ሥዕላቱም ተቃጥለዋል፡፡ የመቅደሱን ግድግዳም ጥቁር ቀለም ቀብቶት ነበር፡፡ ከፊሉ ካህናት ሲታረዱ ከፊሎቹም ወደ ሞቃዲሾ ተወስደዋል፤ የተቀሩትም ተሰደዋል፡፡ ታቦቱ ግን መምህር ወልደ ዮሐንስ በተባሉ ካህን አማካይነት ራስ አበበ ወልደ አረጋይ ወደ ነበሩበት ሰሜን ሸዋ ጎሽ ባዶ ዐፄ ዋሻ ማርያም በድብቅ ስለወሰዱት አልተገኘም፡፡ የተመለሰው ከድል በኋላ ግንቦት ፳፫ ቀን ፲፱፻፴፬ ዓ.ም. ነው፡፡
ፋሽስት ኢጣልያ ጥቁር ቀለም የቀባው የመቅደሱ ግድግዳ ሙሉ በሙሉ የለቀቀው የዐፄ ኃይለ ሥላሴ ፳፭ኛ የዘውድ ኢዮቤልዩ በዓል ሲከበር በተደረገ ዕድሳት ነው፡፡ የመጀመሪያውን ሥዕል የሣሉት አለቃ ኅሩይ ሲኾኑ የአኹኑን የሣሉት ደግሞ አቶ እም አእላፍና የተከበሩ የዓለም ሎሬዬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ናቸው፡፡
ዛሬ ያለው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤት የካቲት ፳፫ ቀን ፲፱፻፬ ዓ.ም ቢከበርም ሥራውን ያስፈጸሙት የዐፄ ምኒልክ ልጅ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ናቸው፡፡ በዚኹ ታላቅና ታሪካዊ ደብር በ፲፱፻፱ ዓ.ም. ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ወለተ ምኒልክ፣ በ፲፱፻፳፫ ዓ.ም. ግርማዊ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘውድ ጭነውበታል፡፡ ገዳሙ 467 ጋሻ መሬት ነበረው፡፡ ከዚኽ መካከል አብዛኛው በንጉሠ ነገሥት ዐፄ ምኒልክ የተሰጠ ነው፡፡ /ዲ.ን ዳንኤል ክብረት፤ የቤተ ክርስቲያን መረጃዎች፣ ፲፱፻፺፱ ዓ.ም./