አስገደ ገ/ስላሴን ጨምሮ በትግራይ የሰማያዊ እጩዎች ታገዱ

ነገረ ኢትዮጵያ

10941430_669693659822962_8212491307418410094_nሰማያዊ ፓርቲ በትግራይ ክልል ለክልልና ተወካዮች ምክር ቤቶች ለምርጫ ያቀረባቸው እጩዎች በምርጫ ቦርድ መታገዳቸውን በመቀሌ ከተማ ለክልል ም/ቤት ሰማያዊን ወክለው እጩ ሆነው የቀረቡት አቶ አስገደ ገ/ስላሴ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

ቀደም ሲል በቅጽ ሦስት ሲመዘገቡ ምንም አይነት ችግር እንዳልገጠማቸው ያስረዱት አቶ አስገደ፣ አሁን ላይ ተመዝጋቢዎቹ ወደ ቅጽ አራት በሚዘዋወሩበት ወቅት ‹‹ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ ትዕዛዝ ነው›› በሚል በምርጫ አስፈጻሚዎች እጩዎቹ መታገዳቸው እንደተገለጸላቸው አቶ አስገደ ተናግረዋል፡፡

ስለጉዳዩ የክልሉን ምርጫ ቦርድ ኃላፊ አቶ ወልደጊዮርጊስ በላይን ማነጋገራቸውን የገለጹት አቶ አስገደ፣ ‹‹እኛ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ያለውን ትዕዛዝ ነው የምንፈጽመው፡፡ አግዱ ከተባልን እናግዳለን፤ አታግዱ ከተባልን አናግድም፡፡ አሁን ከምርጫው ሙሉ ለሙሉ ተሰርዛችኋላ ማለት ባልችልም መታገዳችሁ ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የተላለፈ ትዕዛዝ ነው›› የሚል መልስ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡

ለእግዱ መነሻ አድርገው የሚያቀርቡት ከአንድነት ፓርቲ መምጣታችንን ነው ያሉት አቶ አስገደ፣ አንድ ሰው ፓርቲን ወክሎ ምርጫ ለመወዳደር የት ነበርክ ተብሎ የሚጠየቅበት የህግ አግባብ የለም ብለዋል፡፡ አንድ እጩ ኢትዮጵያዊ መሆኑ፣ 23 አመትና ከዚያ በላይ መሆኑ እና ሌሎች መስፈርቶች እንጂ ቀድሞ የነበረበት ፓርቲ እንቅፋት ሊሆንበት አይችልም ሲሉ አስረድተዋል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ህግ ደንብ በሚፈቅደው መሰረት በስራ አስፈጻሚ ሙሉ አባል ተደርገው ፓርቲውን እንደተቀላቀሉ የገለጹት አቶ አስገደ፣ አሁን ምርጫ ቦርድ እያነሳው ያለው ሰበብ ምንም ውሃ የማይቋጥር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹የምርጫ ቦርድ ሰዎች ውዥንብር ለመፍጠር ነው የመጣችሁት ቢሉንም እኛ ግን ባመንበት ፓርቲ ገብተን መታገል መብታችን መሆኑን እናውቃለን፡፡ አሁንም በሰማያዊ ፓርቲ ስር ለእጩነት የቀረብንበት አግባብ ምንም አይነት የህግ ችግር የለበትም፡፡ አላግባብ መብታችንን እየጣሱ ነው›› ብለዋል አቶ አስገደ፡፡

The post አስገደ ገ/ስላሴን ጨምሮ በትግራይ የሰማያዊ እጩዎች ታገዱ appeared first on ሳተናው (Satenaw) – Latest & Current Ethiopian News, Breaking News,.