የቴሌ ትህትና አልበዛባችሁም?
ሰሞኑን ቴሌን አልታዘባችኋትም ? ‹‹ የምትታለበው ላም›› ቀንዷን እያለሳለሰች ይመስላል፡፡ እያንቆለጳጰሰችን ነው፡፡ ‹‹ወዳጆቼ›› በሚል የእንግሊዘኛ ቃል ታጅባ ብቅ እያለች ነው፡፡
ለእኛ ለደንበኞቿ ያላትን ክብር ለመግለጽ ደፋ ቀና እያለች ነው፡፡
ይህ የሆነው የፍቅረኞች ቀን በተከበረበት ሰሞን ስለነበር ያንን ምክንያት በማድረግ የመጣ ደግነት ሊሆን እንደሚችል ገምተን ነበር፡፡ ነገር ግን አሁንም ቀጥሏል፡፡ በአገልግሎቷ ልታረካን ያልቻለችው ቴሌ በሙድ ገብታ ‹‹ውድ ደንበኞች…›› በሚል ሃረግ ልትደልለን እየሞከረች ነው፡፡
ማንም እንደሚያውቀው (ኦባማ ራሱ እንደሚያውቀው) ኢትዮ ቴሌኮም በሚሠጠው አገልግሎትም ይሁን በሚያስከፍለው ታሪፍ አስደስቶን አያውቅም፡፡ ሁሌም እንዳበሳጨን ነው፡፡
ያለ ዕድሜያቸን ነጭ ፀጉር ያበቀልነው በማን ምክንያት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ቴሌ እንደሶቅራጥስ ሚስት ናት፡፡ ሁሌም ታጨሰናለች፡፡ ከሠሞኑ ግን በአገልግሎቷ ባታረካንም በንግግሯ እየደለለችን ነው፡፡
በርግጥ አንዳንድ ደንበኞቿ ጠርጥረዋታል፡፡ ቴሌን በተረት እየወረፏት ነው፡፡ ‹‹አንድ ሰው ደጋግሞ ካቆላመጠህ ሁለት ነገር ካለህ አንዱን ሊወስድብህ ነውና ተጠንቀቅ›› የሚል ተረት እየተረተሩ ይገኛሉ፡፡
ቴሌ ግን እነሱንም በእኛ በታማኝ ደንበኞቿ ልክ አክብራ ‹‹Dear Customers›› በሚል ቁልምጫ እየነዘነዘቻቸው ነው፡፡ ለምን መሰላችሁ .. ቴሌ ይቅር ባይ ናት፣ ሆደ ሰፊ ናት፣ ይህ የህዝብ አገልጋዮች ባህሪ ነው ››
እናመሰግናለን ‹‹ዲር ቴሌ›!›
Receive Ethiopian News and Videos by email. Sign up for Email alerts ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን፣ ጠቃሚ ምክሮችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜሎን ያስመዘግቡ።
