እረ ይሄ የተረገመ ምርጫ ምንነው ቢቀር ? – ግርማ ካሳ
ምርጫ አገራችን ወደ ጦርነት እንዳትገባ፣ ዜጎች ያሏቸው ልዩነቶችን ሕዝብ ፊት በማቅረብ በሰላም እንዲፈቱ ለማድረግ የታሰበ ነበር። ምርጫ ባይኖር አንዱ ድርጅት ሌላውን በኃይል ለማሸነፍ ይሞክራል። አመጽና ጦርነት ይኖራል። ያ እንዳይኖር ነበር የምርጫ አስፈላጊነት። ሆኖም ኢትዮጵያ ዉስጥ ግን፣ በምርጫ ሰበብ የዜጎች ደም እየፈሰሰ ነው። በሕዝቡ ላይ ስቃይና መከራ እየጨመረ ነው። ምርጫ በመጣ ቁጥር ሕወሃቶች በደም ይሰክራሉ። ሁሉም ነገር ይዘጋል !!! ጠዋትና ማታም ያደነቁሩናል።
በምርጫ ቢያንስ አንጻራዊ መረጋጋት ይኖራል የሚል ተስፋ ነበረኝ። ወደ ምርጫው ተገብቶ እንቅስቃሴዎች እንዲደረጉ ሳበረታታ ነበር። ሆኖም በአገራችን ኢትዮጵያ ዲሞክራሲ የለም። ሕግ የለም። እኩልነት የለም። ነጻነት የለም። ምንድን ነው ያለው ብትሉኝ ያለው ባርነት ነው፣ ያለው ግፍ ነው። ያለው ዘረኝነት ነው። ያለው ጭቆና ነው። በአገራቸው የሰፈነው የዳግማዊ ግራዚያኒ አገዛዝ ነው። ሕወሃቶች በልመና በተገኘ ገንዘብ ( ያው ብዙዉን ድርሻ ወደ ኪሳቸው እያዞሩ) መንገድ፣ ድልድይ ሰርተዋል። በግራዚያኒ ጊዜም ጣሊያኖች መንገዶችና ድልድዮች ሰርተዋል። ያኔም ልማት ነበር። ሆኖም ኢትዮጵያዊያን በፋሺትስ ኢጣሊያ ጊዜ እንደ ሰው ይቆጠሩ አልነበረም። እንደ እንስሳ ነበር የሚቆጠሩት።
አሁንስ በምን ተለየ ? አንድ የሕወሃት ባለስልጣን አይቶ ካልወደዳችሁ እሥር ቤት ሊወረወራችሁ ይችላል። ሽብርተኛ ብሎ። የምትኖሩበትን ቤት ወይም የምታእርሱበትን መሬት አንድ ሕወሃት ለግሉ ይሁን ለቢዝነስ ከፈለገው፣ ለልማት ያስፈልጋል ብሎ ካስ በሚል ፍርፋሬ ተወርዉሮላችሁ፣ ከቤታችሁ ፣ ከመሬታችሁ ትፈናቀላላችሁ። ትንሽ አገዛዙን የሚቃወም ነገር ካደረጋችሁ ከሥራ ትባረራላችሁ። በፍርህትና በሰቀቀን ነው የምትኖሩት። ኢትዮጵያ ዉስጥ ማንም ባለ ሃብት ይሁን ደህን ኑሪ የሚኖረ፣ በአገሩ በገመድ ላይ እንደሚራመድ ተጠንቅቆና ፈርቶ ነው የሚኖረው። ምንም አይነት የህግ ዋስትና የለም። ደፍራችሁ የመብት ጥያቄ ካነሳችሁ እንደ አህያ ተደበደባላችሁ። ሰበብ ተፈልጎ ሽብርተኞች ተብላችሁ ወደ ወህኒ ትጣላላችሁ።
ያኔ እነ በላይ ዘለቀ እምቢ ባርነት ብለው፣ ከፋሺስት ኢጣሊያን ጋር ተጋደሉ። አሁን ያለነው ኢትዮያውያን ግን ባርነት እሺ ብለን ተቀብለን መኖር የመረጥን ይመስላል። ለ23 አመታት በዚህ ስርዓት ሥር የምንገዛው ባርነትን ስለመረጥን ነው። ግን ለምን ? ነጻ መዉጣት እንፈልጋለን። ግን የድርሻችንን ለመወጣት ለምን እንፈራለን ? በረሃብና በጠኔ ልጆቻችን እየለቁ፣ በሌላ በኩል ግን ጥቂቶች በዊስኩ ሲራጩ እያየን እስከ መቼ ያስችለናል ? እኛ እየተራብን፣ ጤፉ፣ ፍራፍሬ፣ ስጋው ወደ አረብ አገርና ዳያስፖራ ሲልኩ እያየን ለምን እንታገሳለን ? በረሃብ መሞታችን ካልቀረ ለነጻነታችን ለምን አንሞትም ? ለምንስ ይሄንን ነቀርሳና ዘረኛ አገዛዝ በቃህ አንለዉም ?
እንግዲህ ምርጫ ምርጫ እያልን ጊዜ ባናጠፋ ጥሩ ነው። አገዛዙ አቸነፍኩ ብሎ፣ ደሞክራሲን አለ ለማስባልና ተለራ የፕሮፖጋንዳ ፍጆታ፣ 10፣ 20% የሚሆኑ መቀመጫዎችን ተቃዋሚዎች ይለቃና የግፍ አገዛዙን ይቀጥላል። ከወዲሁ ሊያሸንፉ የሚችሉ ድርጅቶች አግዷል። ስለዚህም ለምን ምርጫ እያልን እየደከምን ሌሎችን እናደክማለን ? ምርጫ ሕጋዊ ትግል ነው። ሕጋዊነት ሕግ ባለበት ቦታ ነው። ኢትዮጵያ ዉስጥ ምን ሕግ አለና ነው ሕጋዊ ትግል የሚደረገው ? ከወዲሁ እጅ አይሰጥም በሚል አገር ቤት ያሉ ደርጅቶች ገፍተው ሄደዋል። ብዙ የሚያኮራ ተግባራትን ፈጽመዋል። ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ታግለው ዳር የደረሱ መሰለኝ።ከዚህ በኋላ የሚያደረጉት ነገር አለ ብዬ አላስብም።
ከዚህ በኋላ ኳሷ እያንዳንዳችን ደጃፍ ላይ ናት። መፍትሄው አንድ ብቻ እርሱም። እርሷም እያንዳንዳችን እጅ ዉስጥ ነው ያለችው። ሁላችንም በየቅያችን፣ በየመነደራችን እንነቃነቅ። ፈረንጆች one at a time ይላሉ። አራቲ ኪሎ ያሉትን ለጊዜው እንተዉን ሁላችንም በየቀቤሌያችን እንጀመር። እንዴት ጥቂት ጭራቅና አጋንንት የሰፈረባቸው ገዢዎች እንደዚህ ሲያምስኑ ዝም እንላለን ?
ይቻላል ፤ አንፍራቸው፣ አንደናገጥ፣ ተስፋ አንቁረጥ። ጥንቃቄና ብስለት ባለው መልኩ ሰላማዊ በሆነ የእምቢተኝነት ዘመቻ ለውጥ ማምጣት እንችላለን። ይሄ ሕጋዊ የሚለውን ትግል ወደዚያ እርሱት !!!! ሕጋዊነት ሕግ ባለበት ቦታ ነው። ኢትዮጵያ ዉስጥ ምን ሕግ አለና ነው ሕጋዊ ትግል የሚደረገው ?
