ሚሊየንስ ድምጽ – ምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤቶች፣ የፖሊስ ተቋማት … ገለልተኛ እንዳልሆኑ ሪፖተር ዘገበ

“ሕዝብ በመንግሥት ላይ አመኔታ ኖሮት የየዕለት ሕይወቱን መምራት ይኖርበታል፡፡ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ የተመሠረተ የሕዝብ ፍላጎት ዘለቄታዊ የሆነ እርካታ እንዲፈጠርለት ሲፈለግ ደግሞ፣ ዋና ዋና የሚባሉ ጉዳዮች መፈተሽ አለባቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ አንገብጋቢ ተብለው ሊጠቀሱና መፍትሔ ሊፈለግላቸው የሚገቡ ዋና ዋና ጉዳዮች በአራት ይጠቃለላሉ፡፡” ሲል ሪፖርተር “ሕዝብ የመንግሥትን አመኔታ የሚፈልግባቸው አራት ነጥቦች” ባቀረበው ዘገባ ይዘረዝራቸዋል።

ከአራቱ ጉዳዮች አንዱ የዲሞክራሲ ግንብታ ፈታናውች ብሎ ሪፖርተር ያቀረባቸው ናቸው። «ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤቶች፣ የፀጥታ አስከባሪዎችና የመሳሰሉት አካላት ገለልተኝነታቸውን አስመስክረው ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ ሁኔታዎችን (መንግስት) ማመቻቸት አለበት» ሲል ሪፖርተር በግልጽ ያስቀምጣል። በተቃዋሚዎች ዘንድ ሕግን አክብረው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ያተተው ሪፖርተር በዲሞክራሲ ግንብታ ዙሪያ ትልቅ ችግር የፈጠረው ግን ተቋማት ገለልተኛ አልመሆናቸው መሆኑን አስረድቷል።

የሪፖርት ትንተና እንደሚከተለው ቀርቧል፡
«የመንግሥት ሥልጣን የሚገኘው ከሕዝብ በሚገኝ ፈቃድ ነው፡፡ ይህ ዴሞክራሲ በሰፈነባቸው አገሮች ውስጥ ተግባራዊ የሚሆን የሕዝብ ነፃ ፍላጎት ነው፡፡ አገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት የምትችለው ነፃ ኅብረተሰብ ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረታዊ ከሚባሉ ጉዳዮች መካከል ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ነፃነት፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ፣ ሰላማዊ የሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውድድርና የሕግ የበላይነት መኖር ናቸው፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚደረገው ትግል ፈተናዎች ተጋርጠውበታል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የሥልጣን ምንጭ ሕዝብ መሆኑን መዘንጋት ነው፡፡

የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚያግዙ በርካታ አንቀጾችን በውስጡ ይዟል፡፡ ዜጎች ያለምንም መሸማቀቅ የሚፈልጉትን የፖለቲካ አማራጭ እንዲመርጡ ዕድሎችን አመቻችቷል፡፡ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ከተፈለገ መንግሥት ሕገ መንግሥቱን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት አለበት፡፡ በምርጫው ተወዳዳሪ የሆኑ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎችም ኃላፊነት ይኖርባቸዋል፡፡ በመንግሥት ላይ የሚኖረው ጫና ግን ከፍ ይላል፡፡ በመጀመሪያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤቶች፣ የፀጥታ አስከባሪዎችና የመሳሰሉት አካላት ገለልተኝነታቸውን አስመስክረው ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ ሁኔታዎችን ማመቻቸት አለበት፡፡ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምኅዳሩ ሰፍቷቸው በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲወዳደሩ በተግባር ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ሁሉም ወገን የሕግ የበላይነትን አክብሮ ከተንቀሳቀሰ ሕዝቡ በነፃነት በመምረጥ የሥልጣን ባለቤት መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ የመንግሥትንም መተማመኛ ይፈልጋል፡፡ ሕዝቡ በመንግሥት ላይ አመኔታ እንዲኖረው ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ይፈቱ፡፡ ሕዝብ አሁንም ተግባር! ተግባር! ይላል፡፡ »10168133_780614882023448_8694735050311338874_n