ሦስተኛው የበጎ ሰው ሽልማት ተጀመረ

ለሁለት ተከታታይ ጊዜ የተካሄደው የዓመቱ በጎ ሰው ሽልማት የ2007 የምርጫ ሂደት የካቲት 12 ቀን 2007 ዓም በካፒታል ሆቴል በተዘጋጀ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ተጀመረ፡፡  
ጋዜጠኞች፣ የቀድሞ ተሸላሚዎችና እጩዎች፣ ታዋቂ ሰዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በተከናወነው የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ስለ በጎ ሰው ሽልማት ያለፉት ዓመታት ክንዋኔዎችና ያመጣቸውን በጎ ተጽዕኖዎችን በተመለከተ ገለጻ ተደርጓል፡፡ የሽልማት ኮሚቴው አካላት እንደገለጡት 2007 ዓም የሽልማት ሂደት ካለፉት ዓመታት በተለየ በ10 ዘርፎች የሚከናወን ሲሆን ሂደቱ ተጠናቅቆ ሽልማቱ የሚሰጠው በነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ከጥቆማው በኋላ የእጩዎችን ዝርዝር መግለጫ የማዘጋጀት ሥራ የሚሠራ ሲሆን፣ በመቀጠልም በየሞያው ዕውቀትና ብስለት ባላቸው ሰዎች በተቋቋ ቡድኖች የመጀመሪያ አላፊዎች የመረጣ ሥራ ይከናወናል፡፡ በመቀጠልም ማጣሪያውን ላለፉት የሕይወት ታሪክ ዝግጅት ሥራ ይከናወናል፤ በማስከተልም ቦርዱ የመጨረሻዎቹ ተሸላሚዎች ላይ ውሳኔ ይሰጣል፡፡
ለጠቋሚዎች የተሻለ ዕድል ለመፍጠር የኢሜይል፣ የስልክ፣ የፖስታና የገጸ ድር የመጠቆሚያ መንገዶች የተዘጋጁ ሲሆን፣ የበጎ ሰው ገጸ ድር እዚያው በእዚያው(አውቶማቲክ) የሆነ የእጩ መጠቆሚያ ቅጽ ዝርዝር መረጃዎችን ይዟል፡፡
ለሀገራቸውና ለወገናቸው የሠሩ፣ አኩሪ ገደል የፈጸሙ፣ ለትውልዱ አርአያ የሚሆኑና የሀገራቸውን ክብር ከፍ ያደረጉ ዜጎችን በመጠቆም ሕዝቡ እንዲሳተፍ፤ ጋዜጠኞችና በማኅበራዊ ሚዲያ የላቀ ተሳትፎ ያላችሁ ዜጎች መረጃውን በማዳረስ፣ የኢንተርኔት አገልግሎት ለማያገኙም አትሞ በመስጠት ሁሉም እንዲተባበር ቦርዱ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

 

የዕጩ መጠቆሚያ ዘርፎች
1.      ሰላም፡- በዚህ ዘርፍ ለሀገራዊ ሰላም፣ ለሕዝቦች መግባባት፣ ለግጭቶች መፈታት፣ ማኅበረሰቡ ላቅ ያለ ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲያገኝ በማድረግ የሠሩ ይሸለማሉ
2.     ሳይንስ፡ በሕክምና፣ በቴክኖሎጂ፣በፊዚክስ፣ በኬሚስሪ፣ በምሕንድስና፣ በአርክቴክቸር፣ ወዘተ የሠሩ ይሸለማሉ
3.   ኪነ ጥበብ በልዩ ልዩ የኪነ ጥበብ ዘርፎች በአዲስ መንገድ፣ በልዩ አቀራረብ፣ የሥነ ጽሑፍን ደረጃ ከፍ ያደረጉ፣ በማኅረሰቡ ዘንድ በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድር ሥራ የሠሩ፣ ለኪነ ጥበባችን ዕድገት የተጉ ዜጎች ይሸለማሉ
ሀ. ፊልም
ለ. ሙዚቃ
ሐ. ሥነ ጽሑፍ
መ. ቴአትር
ሠ. ሥዕልና ቅርጻ ቅርጽ
4.     የበጎ አድራጎት ሥራዎች፡- በርዳታና ሰብአዊ አገልግሎት የሠሩ ይሸለማሉ
5.     ግብርና ንግድና የሥራ ፈጠራ፡- በንግድ(ቢዝነስ)፣ በግብርና እና ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሥራዎች በመፍጠር፣ አዳዲስ የሥራ ሐሳቦችን በማመንጨት የሠሩ ይሸለማሉ
6.     ስፖርት፡- በስፖርቱ መስክ አርአያነት ያለውና በጎ ተጽዕኖ የሚያመጣ ሥራ የሠሩ ይሸለማሉ
7.     መንግሥታዊ የሥራ ኃላፊነትን መወጣት፡- በተመደቡበት መንግሥታዊ የኃላፊነት ዘርፍ አርአያ የሚሆን ለውጥ ያመጡና ተገቢውን ሕዝባዊ አገልግሎት የሰጡ
8.     ማኅበራዊ ጥናት፡በማኅበራዊ ጥናት መስክ ተሠማርተው የኅብረተሰቡን ማኅበራዊ ችግሮች የሚፈቱና አዳዲስ ግንዛቤ የሚያመጡ፣ ዕውቀት የሚጨምሩ ላቅ ያሉ ሥራዎችን የሠሩ ይሸለማሉ
9.     ሚዲያና ጋዜጠኝነት፡በሚዲያና በጋዜጠኝነት መስክ ለውጥ አምጭና በጎ ተጽዕኖ አሳዳሪ ሥራ የሠሩ ይሸለማሉ
10.   ቅርስና ባሕል፡-ቅርስና ባሕልን በመጠበቅ፣ በማስተዋወቅ፣ በመሰነድና ዓለም ዐቀፍ ዕውቅና እንዲያገኝ በመሥራት ለውጥ ያመጡ ይሸለማሉ፡፡


የመጠቆሚያ መመዘኛዎች
1.      የሚጠቆመው እጩ በሕይወት ያለ ኢትዮጵያዊ ሰው ወይም ተቋም መሆን አለበት
2.     የምንጠቁማቸው ኢትዮጵያውያን በጎ ለውጥ አምጭ የሆነ ሥራ የሠሩ መሆን አለባቸው፣
3.     የዜጎችን ሕይወት በማሻሻልና ሀገርን በማሳደግ ሊጠቀስ የሚችል ነገር ያከናወኑ መሆን አለባቸው፣
4.     አንድ ሰው በተለምዶ ሊሠራው ከሚገባው ወይም ከሚችለው ሥራ ላቅ ያለ ሰብእና የሚታይበት ተግባር የፈጸሙ መሆን አለባቸው፤
5.     በአሠራር፣ በአስተዳደር፣ በጥናትና ምርምር፣ በኪነ ጥበብና በማኅበራዊ አገልግሎት አዲስ መንገድ ያመላከቱ፣ አዲስ አሠራር የዘረጉ መሆን አለባቸው፣
6.     የሀገርና የሕዝብን ችግር የፈታ ተግባር የከወኑ መሆን አለባቸው
7.     በተሠማሩበት መስክ መሥዋዕትነት ጠያቂ ግዳጅን የተወጡ፣ ራሳቸውን ለሀገርና ለወገን የሰጡ መሆን አለባቸው
8.     ይሁነኝ ብለው የሀገርንና የወገንን ስም የሚያስጠራ፣ ታሪካችንን፣ ባሕላችንን፣ ቅርሳችንን አጉልቶ የሚያወጣ የዜጋ ሥራ የሠሩ መሆን አለባቸው
9.     የማኅበረሰቡን ሞራላዊና ሥነ ምግባራዊ እሴቶችን ለሌሎች መጥፎ ምሳሌ በሚሆን መንገድ ያልጣሱና  ለትውልዱ አርአያ ሊሆኑ የሚችሉ መሆን አለባቸው
10.   በተቻለ መጠን ከዚህ በፊት ሥራቸው ሊነገር፣ ሊዘከርና ሊታወቅ ያልቻለ
11.      ለሀገሪቱ ዕድገትና ሥልጣኔ ለውጥ አምጭ አስተዋጽዖ ያደረጉ
12.    ለሌሎች አርአያ የሚሆኑ ብቁ አመራሮችን የሰጡ፣ በአመራሮቻቸውም አካባቢያቸውን፣ ድርጅታቸውንና መሥሪያ ቤታቸውን የለወጡ፣
13.    አዲስ፣ የራሱ ወጥነት ያለውና ያልተደፈረ የሚመስለውን ሥራ ያከናወኑ፣
14.   የሀገሪቱን ክብርና ደረጃ ያስጠበቁ፣ የሀገሪቱንም መብት ያስከበሩ፣
15.    ሀገራቸውን በዓለም አደባባይ በበጎ ያስጠሩ፣ ስሟን ከፍ ያደረጉ
የመጠቆሚያ አድራሻዎች
              ስልክ፡- 0941615252
              ኢሜይል፡- [email protected]
              ገጸ ድር     www.begosew.com
             ፖስታ፡- 150035  
የመጠቆሚያው ጊዜ
ከየካቲት 13 እስከ መጋቢት 12 ቀን፣ 2007 ዓም ድረስ
 ዕጩዎችን በሚጠቁሙበት ጊዜ
1.      የተጠቋሚዎችን ሙሉ ስም ይጻፉ
2.     የሚገኙበትን ልዩ ቦታ ይግለጡ
3.     የሠሩትን ሥራ በአጭሩ ይግለጡ
4.     ስለ ተጠቋሚው ተጨማሪ መረጃ ሊገኝ የሚችልበትን ምንጭ ይጠቁሙ
5.     ከተቻለ የስልክና የኢሜይል አድራሻቸውን ይግለጡ
6.     የራስዎንም አድራሻ ይግለጡ(ተጨማሪ መረጃ ለመጠየቅ)
7.     ስለሚጠቁሙት ዕጩ ተጨማሪ መረጃ ሊሰጡን ከቻሉ በኢሜይል ወይም በገጸ ድራችን ያያይዙልን