አገራችንን ከጦርነት የሚያወጣ የመፍትሄ ሀሳብ – ግርማ ካሳ
የአርበኞች ግንቦት ሰባት ግንባር ሊቀመንበር ዶር ብርሃኑ ነጋ ከኢሳት ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ አደመጥኩ። ዶር ብርሃኑ በኢሳት ላይ ሲቀርቡ የመጀመሪያቸው አይደለም። ከዚህ በፊት በሰጧቸው ቃለ ምልልሶች ላይ ጠንካራ ትችቶችን በማቅረብ እታወቃለሁ። ብዙ ጊዜ እርሳቸው የሚያራምዱት “ወያኔ በኃይል ብቻ ነው ሊወገድ የሚችለው” የሚለውን ፖለቲካ እንደማይመቸኝ በመገልጽ ጽፊያለሁ። እርሳቸውና ድርጅታቸው የሚቆጣጠረዉ ኢሳት፣ በየጊዜው ዶር ብርሃኑን እያቀረበ ቃለ መጠይቅ ሲያቀርብ፣ አገር ቤት የሚደረገዉን ትግል ግን በስፋት ለምን አይዘግብም በሚል፣ ከኢሳቶችም ጋር አንድ ሁለት የተመላለስንበት ጊዜ ጥቂት አይደለም።
ሆኖም ኢሳት ላለፉት በርካታ ወራት አገር ቤት ለሚደረገው ትግል ሰፊ ሽፋን ሰጥቶ ሲዘግብ ታዝቢያለሁ። አገር ቤት ለሚደረገዉ ሰላማዊ ትግል ኢሳት በርግጥ እንደ ትልቅ አማራጭ ሜዲያ የሆነበት ሁኔታ እንደነበረ ነው ያየሁት። ህዝብን ገለልተኛ በሆነ ሁኔታ ማገለግል የነበረበት ኢትቪ ወይም ኢቢሲ ከአንድ ወር በላይ በአንድነት ፓርቲና በመኢአድ ላይ እንዲሁም ሰማያዊ ላይ የፍየል ወጠጤ አይነት የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ሲከፍት፣ አገር ቤት ያሉ ሰላማዊ የለውጥ ኃይሎች ድምጻቸዉን ሲያሰሙ የነበሩት በኢሳት ነበር። አሁን በርግጥ ኢሳት የግንቦት ሰባት ነው ብቻ ሊባል አይችልም። ኢሳት የግንቦት ሰባትን ጉዳይ በስፋት ቢዘግብም( አስመራ ቢኬድም) የአንድነት፣ የሰማያዊ፣ የመድረክ፣ የመኢአድም ሆኗል። አስመራ ያለውን ብቻ ሳይሆን ዱራሜ፣ ባህር አድር፣ ሶዳ ፣ አዲስ አበባ ፣ አምቦ ….በአገሪቷ ሁሉ እየተደረገ ያለውን፣ የሕዝቡን የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሲዘግብ እየሰማን ነው። በርግጥ ኢሳት በጣም፣ በጣም ተሻሽሏል። በፊት ኢሳትን አላዳምጥም ነበር። አሁን ግን በደንብ አዳምጣለሁ።
ወደ ዶር ብርሃኑ ቃለ ምልልስ ልመለስና፣ አንድ የተናገሩት ነገር ላይ ላተኩር። «አሁን በኢትዮጵያ ዉስጥ የሚደረገውን ምርጫ ተስፋ አድርገው የነበረ ካለ፣ ምርጫዉን በተመለከተ ወያኔ እየወሰደ ባለው እርምጃ፣ አገሩ ጭለማ ሆኗል.፣ ምንም መንቀሳቀሻ የለም ብለው ለሚያስቡት ነው መግለጫ ያወጣነው» ሲሉ ነው ዶር ብርሃኑ የተናገሩት። ዶክተሩ ትንሽ ከወትሮ በተለየ ሁኔታ ኮንፊደንስ ያለባቸው ይመስላል።
አትጠራጠሩ አንደኛ ኢሳት በኢትዮጵያ ዉስጥ ባለው ትልቅ ተደራሽነት፣ ሁለተኛ ግንቦት ሰባት በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ ሰርጎ መግባቱ፣ ሶስተኛ ግንቦት ሰባትን የሚረዳዉና የሚደግፈው የዉጭ ኃይል መኖሩ፣ አራተኛ ግንባሩ በሚታወቁ ፖለቲከኞች መመራቱና አምስተኛ በሰላማዊና ሕጋዊ ትግል ተገፍተው የትጥቅ ትግሉን ሚቀላቀሉ እጅግ በጣም በርካታ ወገኖችን የማግኘት እድሉ ከፍ ማለቱ በጦር ግንባሮች አካባቢ አሁን ያለው ሁኔታ ከወትሮ በጣም የተለየና ትኩረት የሚሰብ አድርጎታል። በርግጠኝነት እንደ አንድነት ፓርቲ ያሉ በአገር ቤት ሕጋዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሚታገሉ ድርጅቶችን፣ ሕወሃት አሳዛኝና ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በኃይል መጨፍለቁ፣ በዜጎች ላይ አገዛዙ እየወሰደ ያለው አሰቃቂ የሽብርተኘኝት ተግባር፣ ለነዶር ብርሃኑ ፣ ፈልገዉትና ተመኝተዉት የነበረ ባይሆንም፣ በእጅጉ ትልቅ ጥቅም አስገኝቶላቸዋል። “የሰላም በር ሲዘጋ የአመጽ በር ይከፈታል» እንዳለው አብርሃ ደስታ፣ የሰላማዊ ታጋይቾ ሲመቱ አማራጩ የታወቀ ነው የሚሆነው። «ሌላ አማራጭ አለ። እንደበፊቱ አይደለም። በጣም ግልጽ የሆነ፣ ችሎታ ያለው። ብቃት ያለው፤፡ ይሄንን ስርዓት በደንብ አርጎ መመከት የሚችል ኃይል አለ» ሲሉ ዶር ብርሃኑ የገለጹትም ለዚህ ነው።
እንደ አንድ ሰላማዊ ታጋይ ከነዶር ብርሃኑ ጋር እንደ ከዚህ በፊቱ መከራከር አልችልም። «ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ለከሸፈው አንተ ግን በጣም ተስፋ ጥለህበት የነበረውን ሰላማዊ ትግል የሚተካ አንድ ልዩ ነገር ፈልግና እንከተልህ» ሲል ነበር ወንድም ኪሩቤል በቀለ (የግንቦት ሰባት ደጋፊ) በፊት ያለውን ጨለማ ያስታወሰኝ። መልስ አልነበረኝም። የማቀርበው መከራከሪያ አጣሁ። ወንድም ፍቃደ ሸዋቀና እንዳለው “ We lost the debate” ። እኛ መድረኩን ለቀን አሁን እነርሱ ይዘዉታል። እድሜ ለህወሃት !!!!!
ዶር መሳይ ከበደ “ Ethiopians gear up for the worst” እንዳሉት ከአሁን በኋላ ጦርነትና ደም መፋሰስ ነው እየሸተተኝ ያለው። ፖለቲካው በጣም ከሯል። ገመዱ በጣም ተስቧል። አገሪቷ ወዳልታሰበ አስከፊ ደረጃ ከመዉደቋ በፊት አንድ ነገር መደረግ አለበት ባይ ነኝ። በዋናነት ሕወሃቶች አሁን ካሉበት የፖለቲካ ስካራቸው ወጥተው የሚከተሉትን እንዲያደረጉ እጠይቃለሁ፡
1. የፊታችን ግንቦት የሚደረገው ምርጫ ጨዋታና ቀልድ በመሆኑ ተሰርዞ፣ አገር ዉስጥም ሆነ ከአገር ዉጭ ያሉ ድርጅቶን ሁሉ ያቀፈ፣ የእርቅ ኮንፈራንስ መዘጋጀት አለበት። አገዛዙ በምንም ተዓምር አሁን ባለበት ሁኔታ ሊቀጥል አይችልም። አንደኛ አባይ ጸሃዬ ኦህድዶችን ሲሳደቡ እንደሰማነው፣ በኢሕአዴግ ዉስጥ በራሱ ትልቅ አለመስማማትና ብጥብጥ አለ። ሁለተኛ ከኮሎኔል በታች ያሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በዋናነት ከሕወሃት ብቻ በመጡ የጦር መኮንኖች ላይ ትልቅ ችግር እንዳለባቸው እየሰማን ነው። ሶስተኛ የኑሮ ዉድነቱ ከቁጥጥር በላይ ሆኗል። አንድ ኩንታል ጤፍ ከ2000 ብር በላይ ነው። የብር የመግዛት አቅሙ ወድቋል። የበለጠም ይወድቃል። አራተኛ ሙስናው ህዝብን ማንገላታቱ አይጣል ነው። አምስተኛ በዜጎች ላይ የሚደርሰው ግፍና መከራ ዜጎች የበለጠ እንዲያከሩ እያደረጋቸው ነው። ስድስተኛ በቂ የዉጭ ምንዛሪ የለም። ሰባተኛ በዘረኝነታቸው ሕወሃቶች በጣም እየተጠሉ ነው። ስምንተኛ ተቃዉሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረባቸው ነው። (በትጥቅ ትግሉም ሆነ በሰላማዊ ትግሉ ረገድ)። ዘጠነኛ ሚስጥራቸው ሁሉ እየወጣ ነው። በደርግ መጨረሻ ጊዜ እንደነበረው እየተፍረከረኩ ነው። በመሆኑም ለራሳቸው፣ ለአባላቶቻቸው፣ ለደጋፊዎቻቸው ሲሉ ፣ ከትእቢታቸው ተንፈስ ብለው፣ ራሳቸውን አዋርደው ለብሄራዊ እርቅ ይዘጋጁ።
2. በአስቸኳይ ይሄ ሕዝብን የሚያሸብሩበት የጸረ-ሽብርተኛ ሕግ ሰርዘው፣ የታሰሩ የሕሊና እስረኞችን በሙሉ፣ ዝባ ዝንኪ ሳያበዙ መፍታት አለባቸው።
እግርጠኛ ነኝ አገር ቤት ያሉ እንደ አንድነት፣ ሰማያዊ መድረክ ያሉ ደርጅቶች፣ በዉጭ አገር ያሉ እንደ ሸንጎ፣ ግንቦት ሰባት፣ ኦዴፍ የመሳሰሉትም ከአገዝዙ ለሰላምና ለእርቅ ፍቃደኝነት እንዳለ ከተረዱ ፣ አሁን ካሉት ባለስልጣናት ጋር ቁጭ ብለው ለመነጋገር እምቢ የሚሉ አይመስለኝም። እነ ዶር ብርሃኑ ነጋ፣ የሸንጎ፣ የመድረክ፣ የአንድነት ..በርካታ አመራሮችን አውቃቸዋለሁ። ማንም ተሸናፊ ያለሆነበት፣ ሁሉም (ራሳቸው ሕወሃቶችም ሳይቀሩ) አሸናፊ የሆኑበት አንድ አይነት የ እርቅ ፎርሙላ ማዘጋጀት ቢቻል አይከፋቸውም። የግድ ሕወሃት መትፋት አለበት የሚሉ አይደሉም።
እስከአሁን ለሰላም በሩን ቀርቅረው የዘጉት፣ ሁሉንም ወደ ጠርፍ እንዲሄዱ የገፉት ሕወሃቶች ራሳቸው ናቸው። ቁልፍ ያለው ሙሉ ለሙሉ የህወሃት የፖሊት ቢሮ ጽ/ቤት ነው። ቆም ብለው ያስባሉ፣ የጊዜውን ሁኔታ ያጠናሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ያ ከሆነ ጦርነት አይኖርም ፣ አገራችን ሰላም ትሆናለች።
ያ ካልሆነ ግን ምንም ማድረግ አይቻልም። ዛሬ በመቀሌ ሲያደረጉት እንደነበረው፣ ሁሌ ዳንኪራ የሚሆን ከመሰላቸው ምንም ማድረግ አይቻልም። “ሰይፍን የሚያነሳ እርሱ በሰይፍ ይወድቃል” እንደተባለ፣ እንደ ሰለጠነ ማህበረሰ ሳይሆን ጫካ የነበሩ ጊዜ እንደሚያስቡት ሰይፍ ካነሱ፣ በርግጥ በሰይፍ ይወድቃለይ። አወዳደቃቸው እጅግ በጣም ታላቅ ነው የሚሆነው። ESAT News Analysis