የሥራ ባልደረቦች በፍቅር ሲጣመሩ Office Romance: Ethiopians share their experience about falling in love with someone they work with

ማሕሌት አሰፋ (ስሟ ተቀይሯል) በልደታ ክፍለ ከተማ የቤቶች ልማት አስተዳደር ውስጥ የተቀጠረችው በ2001 ዓ.ም. ነበር፡፡ በመሥሪያ ቤቱ ካሉ የሙያ አጋሮቿ ጋር ጥሩ የሚባል ግንኙነት ነበራት፡፡ በተለይም በሥራው ምክንያት ከሌሎቹ የሙያ ጓደኞቿ በበለጠ በቅርበት አብሯት ከሚሠራ ወጣት ጋር ተግባብታለች፡፡

ለሻይ፣ ለምሳና በሌሎች መሰል ጉዳዮች የሚወጡትና የሚገቡት አብረው ነበር፡፡ የነበራቸው ጓደኝነትም ቀስ በቀስ መልኩን ቀይሮ ወደ ፍቅር ተለወጠ፡፡ ቢሆንም ቢሮ ውስጥ የተለየ ባሕሪ ስላላሳዩ የፍቅር ግንኙነት መጀመራቸው በሌሎች ሠራተኞች ዘንድ አልታወቀም ነበር፡፡ እነሱም በምሥጢር መያዙን ወደውታል፡፡ 

በግንኙነታቸው ደስተኞች ቢሆኑም አልፎ አልፎ ሲጋጩና በሥራ ቦታ ሲገናኙ ምንም እንዳልተፈጠረ ለማስመሰል ብዙ ይጥራሉ፡፡ በዚህም የሚደርስባቸው የሥነ ልቦና ጫና ከባድ እንደሆነ ማሕሌት ትናገራለች፡፡ ‹‹በሆነ ነገር ተጋጭተን ስንኮራረፍ ቢሮ መግባት ሁሉ ያስጠላኛል፡፡ የፍቅር ግንኙነቴ ከቢሮ ውጭ ከሆነ ሰው ጋር ቢሆን ሥራ ስገባ ልረሳው እችል ነበር፡፡ ነገር ግን ጓደኛዬን በሥራ ምክንያት መልሼ ስለማገኘው የባሰ የሚከብድ ስሜት ውስጥ እገባለሁ፤›› ትላለች፡፡ 

እነዚህና መሰል ገጠመኞች ቢከብዷትም ‹‹እንደ ምንም ኮስተር ብዬ ሥራ ለመሥራት እጥራለሁ›› ትላለች፡፡  ግንኙነታቸው በምሥጢር ተይዞ ዓመታት ካሳለፉ በኋላ ነበር ጓደኝነታቸው ወደ ትዳር ያደገው፡፡ በጓደኝነታቸው ወቅት ያሳለፉት ጊዜም እርስ በርስ እንዲተዋወቁ ረድቷቸዋል፡፡ ‹‹የተደበቀ ባሕሪ ይመጣል የሚል ሥጋት አይኖርም፤›› ትላለች፡፡ ዛሬ ላይ የአንድ ልጅ እናት ስትሆን መሥሪያ ቤት ቀይራለች፡፡ እንደ እሷ ገለጻ፣ ከሥራ ባልደረባ የሚጀመር የፍቅር ግንኙነት ከባድ ጫና ቢኖረውም አሉታዊ አጋጣሚዎችን ጠንክሮ በማለፍ ከቁም ነገር ማድረስ ይቻላል፡፡ 

በብዙ አጋጣሚዎች የሚፈጠረው የሰዎች ትውውቅ እየጠነከረና ትስስራቸው እየጎለበተ ይመጣል፡፡ ይህ አጋጣሚ በተቃራኒ ጾታ መካከል ሲከሰት ወደ ፍቅር የሚያድግበት አጋጣሚ ከፍተኛ ነው፡፡ አንድነታቸውም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ይጠነክራል፡፡ በአብሮነታቸው የሚከሰቱ ችግሮች እንደሚኖሩ ሲገምቱ፣ ግንኙነታቸውን በምሥጢር ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡ በተለይም ግንኙነቱ የተከሰተው በአንድ መሥሪያ ቤት ወይም ቢሮ ውስጥ በሚሠሩ ሰዎች መካከል ሲሆን፣ የሚኖራቸው ግንኙነት በአብዛኛው በምሥጢር ይያዛል፡፡ አልፎ አልፎም ሥራው ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ይኖራል ተብሎ ስለሚታሰብ መሰል ግንኙነቶች እና ትዳር መመሥረት በአንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ሲከለከል ይስተዋላል፡፡

‹‹ፍቅር ሁሌ ጉሮ ወሸባ አይደለም፡፡ በአንዳንድ አጋጣሚዎች ግጭቶች ይኖራሉ፤›› የሚለው ወጣት ሐፊዝ መሐመድ ከሥራ ባልደረባ  ጋር የሚጀመር የፍቅር ግንኙነት ከሌላው በተለየ ለብዙ ግጭቶች እንደሚዳርግ ያምናል፡፡ ስለዚህም እንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች እንዳይፈጠሩ ከሩቁ ይሸሻል፡፡ ይሁን እንጂ ጥረቱ ሳይሳካ ቀርቶ በአንድ ወቅት በዚህ ግንኙነት ውስጥ እንዳለፈ ያስታውሳል፡፡

‹‹አዲስ ተቀጣሪ ናት፡፡ አንድ ቢሮ ውስጥ የምንሠራ ቢሆንም የእሷ ዲፓርትመንት ሌላ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ አሠራሮች ላይ እንድረዳት ትጠይቀኛለች፡፡ ቀስ በቀስም ተግባባን፤›› በማለት በመጀመርያዎቹ ጊዜያት የነበሩትን ሁኔታዎች ያስታውሳል፡፡ አብዛኛዎቹን ጊዜያት የሚያሳልፉትም አብረው ነበር፡፡ በሁኔታው ብዙ ደስተኛ ባይሆንም አልተከፋም፡፡ ነገር ግን በመሥሪያ ቤት ውስጥ ስለ እነሱ የሚወራው ወሬ፣ በቀልድ መልክ የሚወረወሩ ቃላትና የብዙዎቹን ትኩረት መሳቡ ምቾት አልሰጠውም፡፡ 

ረዥም ጊዜ አብረው ስለሚያሳልፉ ለጓደኞቹና ለራሱ የሚሆን ጊዜ ያሳጣው ጀመር፡፡ ‹‹ለሻይና ለምሳ የምወጣው ከሷ ጋር ብቻ ነው፡፡ ነገሮች ተደበላለቁብኝ፡፡ ብዙ ስለተለማመድንም የፍቅር ጓደኛ ከመሆን ይልቅ እንደመደበኛ ጓደኛ እቆጥራት ጀመር፤›› በማለት አብዛኛውን ሰዓት አብረው ማሳለፋቸው የፈጠረበትን ስሜት ይገልጻል፡፡

እንደ ሐፊዝ ገለጻ፣ ከሥራ ባልደረባ ጋር የሚጀመር የፍቅር ግንኙነት በጥንዶች ላይ ከሚፈጥረው የቀዘቀዘ ስሜት ባሻገር ከሌሎች የሥራ ባልደረቦች ጋር በሚኖረው መስተጋብር ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ ‹‹መጀመርያ ከሥራ ጓደኞቼ ጋር የነበረኝ ግንኙነት ፍፁም ነፃ ነበር፡፡ ነገር ግን ከእሷ ጋር ከሆንኩኝ በኋላ የሚከታተለኝ ሰው እንዳለ በማሰብ ከፍላጎቴ እቆጠብ ነበር፤›› ይላል፡፡ 

ከሥራ ባልደረባው ጋር የጀመረው ፍቅር ዕድሜው ከወራት አልዘለለም፡፡ ፍቅረኛው  መሥሪያ ቤቱን ስትለቅ ግንኙነታቸውም ቀስ በቀስ ተቋጨ፡፡ ‹‹በዚህ ሁኔታ ብንቆይ ጥሩ ያልሆኑ ነገሮች ይከሰቱ ነበር፤›› በማለት መቋጨቱን እንደወደደው ይናገራል፡፡ እሱ እንደሚለው፣ ከሥራ ባልደረባ ጋር የሚጀመሩ የፍቅር ግንኙነቶች አሰልቺ ከመሆናቸውም ባሻገር በሥራ ላይ የሚፈጥሩት ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡

አልፎ አልፎ በየመሥሪያ ቤቱ የሚታዩት በባልደረቦች መካከል የሚደረጉ የፍቅር ግንኙነቶች ውስጣዊ ስሜቶችን መሠረት ያላደረጉና ጥቅምን ፍለጋ የሚከሰቱ ናቸው፡፡ ይህ በአብዛኛው በአለቃና በበታች ሠራተኞች መካከል የሚከሰት ሲሆን፣ ሥራ ከመበደል ባለፈ የሌሎች ሠራተኞች መብት የሚጋፋበት አጋጣሚ መኖሩን አንዳንዶች ይናገራሉ፡፡ ስለዚህም ጥቂት በማይባሉ መሥሪያ ቤቶች የሚከለከልበት አጋጣሚ አለ፡፡    

አቶ ያሬድ አረጋዊ ይባላሉ፡፡  በአንድ ቢሮ ሠራተኞች መካከል ምንም ዓይነት የፍቅር ግንኙነት መኖር የለበትም የሚል እምነት አላቸው፡፡ በሚሠሩበት መሥሪያ ቤት የውስጥ ደንብ መሠረትም ከሥራ ባልደረቦች ጋር የፍቅር ጓደኝነት መመሥረት የተከለከለ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ደንብ ከመውጣቱ በፊት አብዛኛዎቹ አለቆችና የበታች ሠራተኞች ጥቅምን መሠረት ያደረገ የፍቅር ግንኙነት ይመሠርቱ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

ከዚህ ቀደም የነበሩትን ሁኔታዎች ሲያስታውሱም ‹‹ጥቂት የማይባሉ ሠራተኞች ከአለቃቸው ጋር የፍቅር ግንኙነት ለመጀመር ይጥራሉ፡፡ አለቆቻቸውም ቢሆኑ አጋጣሚውን የመጠቀም ፍላጎታቸው ከፍተኛ ነው፡፡ እንደ ስኬትም ያዩታል፡፡ ከዚያም ቢሮው ለሚያቀርበው ማንኛውም ዕድል ግንባር ቀደም ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ይህ ደግሞ ሥራውን አስቀያሚ ያደርገዋል፤›› ይላሉ፡፡

አልፎ አልፎም ያልተገባ እሰጣ ገባ ውስጥ እንደሚገቡ ይናገራሉ፡፡ ‹‹የእኔ የበላይ አለቃ ነበር፡፡ በተለመደው አጋጣሚ ከእኔ ሥር ካለች አንዲት ሠራተኛ ጋር የፍቅር ግንኙነት ጀመሩ፡፡ ብዙ አስቸጋሪ ነገሮችም ይገጥመኝ ጀመር፡፡ ልጅቷ እሱን እንደ መከታ ትጠቀመዋለች፡፡ ሥራ በአግባቡ መሥራትም ተወች፡፡ ተጠያቂው እኔ በመሆኔ ሥራ በአግባቡ መሥራት እንዳለባት ነገርኳት፡፡ አለቃዬ ግን አኮረፈኝ፡፡ ከዚያም በሆነ ባልሆነ መንገድ መጋጨት ጀመርን፤›› በማለት የገጠማቸውን ችግር ያስታውሳሉ፡፡ 

ምንም እንኳ በማንኛውም የፍቅር ግንኙነቶች አለመግባባቶችና ሌሎችም ችግሮች ሲከሰቱ ቢታይም፣ በሥራ ባልደረቦች መካከል የሚፈጠሩ የፍቅር ግንኙነቶች የሚያስከትሉት ተፅዕኖ ጠንከር እንደሚል የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ‹‹አብዛኛውን ጊዜ አብረው የሚሠሩ ሰዎች የሚጋቡበት ሁኔታ አለ፤›› ያሉት ወ/ሮ መስከረም አሰፋ የሶሻል ሳይኮሎጂ ባለሙያ ናቸው፡፡ 

እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ፍቅር ማለት ከጓደኝነት እያደገ የሚሄድ ስሜት ነው፡፡ ይህም የሚፈጠረው በመላመድ ነው፡፡ በዚህ ግንኙነት የሚፈጠሩ ግጭቶች ቢኖሩም በሰዎቹ ማንነትና አካሄዳቸው ላይ የተመረኮዘ ይሆናል፡፡ በተለይም በሥራ አካባቢ በሚከሰቱ የፍቅር ግንኙነቶች ጓደኛሞቹ የሚያሳዩት እንቅስቃሴዎች የሥራ ባልደረቦችን ይረብሻል፡፡ ስለዚህም በሥራ ቦታ እንደ ማንኛውም የሥራ ባልደረባ ሊተያዩ ይገባል፡፡ በዚህም በሥራ ላይ ከሚፈጥሩት አሉታዊ ተፅዕኖ ነፃ መሆን ይቻላል፡፡ ነገሮችን በዚህ መልኩ ማስኬድ የቻሉ ጥንዶችም በሥራ ላይ የበለጠ ውጤታማ ይሆናሉ ይላሉ፡፡

እንደ ወ/ሮ መስከረም አነጋገር፣ ከሥራ ውጪ በራሳቸው ላይ የሚደርስባቸው የሥነ ልቦና ጫና ከፍተኛ ነው፡፡ ግጭቶች ሲፈጠሩ በተለይም ደግሞ በመጥፎ አጋጣሚ ሲለያዩ መልሰው በሥራ ምክንያት ይገናኛሉ፡፡ ስሜታቸውም በእጅጉ ይጎዳል፡፡ ለመርሳት ይከብዳቸዋል፡፡ በተለይም አንደኛው አካል ከሌላ ሰው ጋር ግንኙነት በሚጀምርበት ጊዜ የሚገጥመው የሥነ ልቦና ችግር በሥራም ሆነ በግለሰቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል፡፡

Receive Ethiopian News and Videos by email. Sign up for Email alerts ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን፣ ጠቃሚ ምክሮችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜሎን ያስመዘግቡ።