ሊቀ ጳጳስ ኦስካር ለፍትህ የቆሙ ጳጳስ – ግርማ ካሳ
እሁድ እለተ ሰንበት ቀን ነበር። አምላካቸዉንና ፈጣሪያቸዉን ሊያመሰግኑ ምእመናን የቤተ ክርስቲያኒቱን አዳራሽ አጣበዉታል። በአዳራሹ የነበረዉ ምእመን ፊቱን ወደ መንበረ ታቦቱ አዙሯል። በመንበረ ታቦቱ በቀኝና በግራ በኩል ነጭ የለበሱ ዲያቆናት ቆመዋል። በዲያቆናቱ መካከል ከመንበረ ታቦቱ በኋላ ምእመኑን ፊት ለፊት የሚያዩ አንድ የእግዚብሄር ሰዉ ይታያሉ። እኝህ ሰዉ በመንበረ ታቦቱ ላይ የነበረዉን ሕብስት በሁለት እጃቸዉ አነሱ። ወደ ሰማይ ዘርግተዉ ሕብስቱን መባረክ ጀመሩ። በእጆቻቸዉ ወደ ላይ ከፍ ያደረጉትን ህብስት ወደ ቦታዉ ሳይመልሱት፣ ድንገት ሕብስቱም እርሳቸዉም መሬት ላይ ወደቁ።
እኝህ ሰዉ ቅዳሴ እየቀደሱ ነበር። ሕብስቱም የጌታ ሥጋ (ቅዱስ ቁርባን) ነበር። ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዉስጥ ከሚገኝ የከፍታ ቦታ የተተኮሰ ጥይት የእኝህ የእግዚአብሄር አገልጋይ ደረት ላይ አረፈ። የተኮሱት ታጣቂዎች ወዲያዉ ስፍራዉን ለቀዉ ጠፉ። ህዝቡ ተደናገጠ። ለቅሶና ዋይታ አዳራሹን አቀለጠዉ።
ቅዳሴ ሲያስቀድሱ በጥይት የተገደሉት እኝህ የእግዚብሄር ሰዉ፣ የኤልሳልቫዶር (ላቲን አሜሪካ ዉስጥ ያለች አገር ናት) ሊቀ ጳጳስ ኦስካር ሮሚሮ ነበሩ። ኦስካር ሮሚሮ በኤልሳልቫዶር የተስፋፋዉን ኢፍትሃዊነት፣ በመንግስት የሚደረገዉን ሽብርና ግድያ፣ በአገሪቱም የነበረዉን የከፋ ድህነት አጥበቀዉ የሚያወግዙ ታላቅ የእግዚአብሄር ሰዉ ነበሩ። የሚመሩበትና የሚሰብኩት ወንጌል የፍትህ መጽሃፍ፣ የሚከተሉትና የሚያመልኩት ጌታ የፍትህ አምላክ መሆኑን በመረዳታቸዉ፣ ይሉኝታ፣ ፍርሃት ሳይዛቸዉ፣ ጥቅምና ምቾት ሳያታልላቸዉ ለፍትህ የቆሙ ነበሩ።
በአሜሪካዉ ዴሞክራስቲኩ ፕሬዘዳንት ጂሚ ካርተር ይደገፍ የነበረዉ፣ የወቅቱ የኤልሳልቫአዶር ወታደራዊ ጁንታ፣ እኝህን ሰዉ በመግደል ዝም ለማሰኘት የመረጠዉ፣ የሊቀ ጳጳስ ኦስካር ጠንካራ የፍትህ አቋም ስላልተመቸዉና ስላሰጋዉ ነበር።
ኦስካር ሮሜሮ ለእዉነት፣ ለፍትህ፣ ለድሆች በመቆማቸዉ በወቅቱ ጉልበተኞች በተተኮሰ ጥይት እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በ 1981 ዓ.ም ነበር የወደቁት። ኦስካር ሮሜሮ እንደ ሌሎች አደርባይ የሃይማኖት መሪዎች ከመንግስት ባለሥልጣናት ጋር ተሻርከዉ፣ የሕሊናቸዉንና የአምላካቸዉን ድምጽ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለዉ መኖር ይችሉ ነበር። ነገር ግን የእግዚብሄር ሰዉ ምን መሆን እንዳለበት ሕይወታቸዉን በመስጠት ያሳዩ ታላቅና የተከበሩ የዘመናችን ሰዉ ነበሩ።
የኛ የሃይማኖት አባቶች፣ ቅዳሴ የሚያስቀድሱ፣ ወንጌል የሚሰብኩ ከሊቀ ጳጳስ ኦስካር ምን ይማሩ ይሆን ? እኛ ክርስቲያኖች ነን የምንል . መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስትስን እንወዳለን የምንል፣ ከ እኝህ ከ እግዚአብሄር ሰው ምን እንማር ይሆን ?
The post ሊቀ ጳጳስ ኦስካር ለፍትህ የቆሙ ጳጳስ – ግርማ ካሳ appeared first on ሳተናው (Satenaw) – Latest & Current Ethiopian News, Breaking News,.