የአማርኛ ሞክሼ ሆሄያት

በአማርኛ ቋንቋ ዕድገትና ብልጸጋ ጎዳና ላይ ከሚገኙት ተግዳሮቶች አንዱ ተገቢ የሆነ፣ ሁሉም የሚቀበለው፣ በቀላሉ የሚገኝና ደረጃውን የጠበቀ የአማርኛ ሥርዓተ ጽሕፈት አለመኖር ነው፡፡ የአጻጻፍ መንገዶችን፣ መልክዐ ፊደልና ሥርዓተ ፊደልን፣ በቃላት አጻጻፍ የሆሄ መረጣን፣ የፊደል መጠንን፣ የስያሜ ቃላት አሰጣጥን፣ የትርጎማ መንገድን፣ ወዘተ የተመለከተ ሥርዓተ ጽሕፈት ያስፈልገናል፡፡ ለዛሬው ግን ብዙዎቻችን የምንስትበትንና የምንምታታበትን የሞክሼ ሆሄያት (ሀ፣ ሐ፣ ኀ፣ ኸ፤ ሠ፣ሰ፣ አ፣ ዐ፤ ጸ፣ ፀ) አጻጻፍን በተመለከተ ታዋቂው ሊቅ ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ(ነፍሳቸውን ይማርና) አዘጋጅተውት ሻማ ቡክስያሳተመውን ‹‹የአማርኛን ሞክሼ ሆሄያት  ጠንቅቆ ያለመጻፍ ችግርና መፍትሔ›› የሚለው መጽሐፍ ላስተዋውቃችሁ፡፡
መጽሐፏ የኪስ መጠን ብትሆንም እስከዛሬ በጉዳዩ ከተዘጋጁት የተሻለች፣ በአመክንዮ የቀረበችና በጥናት ላይ የተመሠረተች ናት፡፡ በተለይም ለደራስያን፣ ለቢሮ ጸሐፊዎች፣ ለፖለቲካ ሰዎች፣ ለጋዜጠኞች፣ ለማስታወቂያ ባለሞያዎች፣ ለአርታዕያን፣ ለፌስ ቡክ ደንበኞችና ለሌሎቻችንም በሞክሼ ቃላት ዙሪያ መመሪያ የምትሆን ናት፡፡ እባካችሁ ነገራችን ወጥ እንዲሆን በሊቁ መንገድ እንሥራ፡፡ ዋጋው 25 ብር ነው ገዝተን በጠረጴዛችን ላይ እናስቀምጥና እንመራባት፡፡
ከምር ሁላችንም ቤትና ቢሮ መጥፋት የሌለባት ናት፡፡