ግን ምንድን ነው ችግራችን ? ግርማ ካሳ
ሶፋ ላይ ቁጭ ብያለሁ። ነገሮችን ማውጣትና ማውረድ ጀመርኩ። አንዲ ሴት ወደ አይምሮዬ ትመላለስ ጀመር። እንደገና ደግሞ በቅርብ ያየሁት፣ የተሰባበረ አጥንት ድቅን አለብኝ። አንዴ አጥንቱ፣ አንዴ ልጅቷ መፈራረቅ ጀመሩ። አይምሮዬ ተናወጠ። በጥያቄ ተሞላ። «ለምን ግን ? እኛ ኢትዮጵያዉያን ምንድን ነው የነካን ? ምንድን ነው ችግራችን ? ለምንድን ነው እንደ አዉሬ የሆንነው ? » ማለት ጀመርኩ።
ልጅቱ ኮተቤ አካባቢ ነበር የምትኖረው። በእጇ የያዘችው ነገር የለም። ድንጋይ አልወረወረችም። በመንደሯ የዪኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተጭነው ወደ ሸዋ ሮቢት ሲሄዱ፣ በአካባቢው ከነበሩ የኮተቤ ተማሪዎች ጋር ሆና፣ ሕገ መንግስቱ የሚፈቅድላትን መብት ተጠቅማ ተቃዉሞ ነው ያሰማችው። በጭካኔ ግንባሯን በጥይት ተመታ ወደቀች። በጨቅላ እድሜዋ ደሟ ፈሰሰ። አሥራ ስድስት አመቷ ነበር። ይሄን ጊዜ 26 አመቷ ይሆን ነበር። ይሄን ጊዜ ባለ ትድርና የልጆች እናት ትሆንም ነበር። በኢትዮጵያዉያን እጅ ይች ኢትዮጵያዊት ተገደለች።ሽብሬ ደሳለኝ ትባላለች። ይሄ ከአሥር አመት በፊት የተፈጸም አሰቃቂ ግፍና ጭካኔ ነበር።
አሥር አመት ቆጠርን። ጋዜጠኛ ነው። እጆቹ ብእር እንጂ መድፍና ነፍጥ ይዘው አያዉቁም። የሚጽፈው የክፋት ነገር አይደለም። የሚጽፈው ስለ ነጻነት፣ ስለ ፍትህ፣ ስለ አንድነት ፣ ስለ መብት ፣ ስለ ሕግ የበላይነት ነው። የሚጽፈው ስለ ሕሊና እስረኞች ነው። ህገ መንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት ሰላማዊ ሰልፍ ዜጎች በወጡ፣ እርሱም በሰልፉ ተገኘ። ሕግን አልጣሰም። ሕግ እናስጠበቃለን ያሉቱ ግን፣ እንደ አህያ መሬት ላይ ጥለው ደበደቡት። አጥንቶቹን ሰባበሩ። ኢሰብዓዊ ጭካኔ ኢትዮጵያውያኖች በዚህ ኢትዮጵያዊ ላይ ፈጸሙ። ስለሺ ሐጎስ ይባላል።
ለምን ግን ? ምንድን ነው እንደዚህ እንድንጨካከን ያደረገን ? ለምንድን ነው እንደ አዉሬ የምንሆነው ? እዉነቴን ነው የምላችሁ እንደ ኢትዮጵያው በጣም ባዘር አያደረገኝ መጣ።
በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ አሰላሰልኩበት። እንደ ሕዝብ መሰረታዊ ችግር ያለብን መሰለኝ። ይቅርታ አድርጉልኝና ወያኔዎች ቢወድቁም ቀጥለው የሚመጡትም ያው ነው የሚሆኑት። መለስ ዜናዊ ሞቶ ኃይለማሪያም ሲመጣ፣ «ጴንጤው፣ መጽሀፍ ቅዱስ የሚያነበውና የሚጸልየው ስልጣን ይዟል፣ ጥሩ ነገር ሊመጣ ነው» ተብሎ ሲጠበቅ እንደዉም ባሰ።
ግድ የለም ወገኖቼ ፣ አንድ መሰረታዊ ችግር አለብን። “ይሄ ህዝብ በአፉ ያከብረኛል ፣ ልቡ ግን ከኔ የራቀ” ተብሎ እንደተጻፈ፣ ላይ ላዩን ሃይማኖተኞች እንመስላለን እንጂ፣ ከእግዚአብሄር ጋር ስለተጣላን ፣ የእግዚአብሄር መንፈስ ስለራቀን ፣ የደረሰብን ጣጣ መስለኝ። እስቲ ተመልከቱ በየቦታው ነው የጥንቆላ ቤቶች ያሉት። በየቦታው ነው የዳንኪራ፣ የጫትና ሺሻ ቤቶች የተስፋፉት። በኢንተርኔት እና በሳተላይት ቲቪ ከዉጭ አገር የመጡ ቁሻሻዎች አገራችን ላይ እየተደፉ ነው። ቤተ ክርስቲያንም ተብሎ ቄሶቹ ካባ የደረቡ ግን እርስ በርስ የማይስማሙ ናቸው። ፓስተሮቹ ወንጌል ከመስበክ ቢዝነስ ነው የያዙት።ብዙ ጉድ በየ አብያተ ከርስቲያናቱ እየሰማን ነው።
እንግዲህ ሁላችንም ንስሐ እንግባ። ወደ ቀኝ ወደ ግራ ሳይሆን ወደኛው እንመልከት። በተዋረደ ልብና በተሰበረ መንፈስ ወደ እግዚአብሄር እንመለስ። ለዉጥ በአገራችን እንዲታይ ከፈለግን፣ ለዉጡን ከራሳችን እንጀምር። “እሺ ብትሉ ብትታዘዙ የምድርን በረከት ተበላላችሁ፣ እምቢ ብትሉ ግን ሰይፍ የባላቹሃል” ተብሎ በኢሳያስ እንደተጻፈ፣ ለጌታ ቃል እንታዘዝ። አለበለዚያ እንደ ህዝብ እንጠፋለን። አገር የምትባልም አይኖረንም። አንድ ወቅት አሲሪያ የምትባል ትልቅ አገር ነበረች። አሁን የት ነው ያለችው ያች አገር? ኢትዮጵያም እንደ አሲሪያ የማትሆንበት ምክንይታ የለም። ወደ ፈጣሪያችን እንመለስ። መድሃኔ አለም ኢየሱስ ክርስቶ ይርዳን !
The post ግን ምንድን ነው ችግራችን ? ግርማ ካሳ appeared first on ሳተናው (Satenaw) – Latest & Current Ethiopian News, Breaking News,.