የህክምና ባለሙያዎች የሥነ-ምግባር ጉድለት እናቶችን ከጤና ተቋማት እያራቀ ነው Mothers stay away from health centers, forced to give birth at home due to unethical medical practice

በ 

በተለያዩ የጤና ተቋማት የሚያገለግሉ የህክምና ባለሙያዎች የሚያሳዩዋቸው ያልተገቡ የሥነ-ምግባር ግድፈቶች እናቶችን ወደ ጤና ተቋማት እንዳይሄዱ እያደረጓቸው መሆኑ ተገለፀ።

የጤናማ እናትነት ሳምንት ማጠቃለያ ፕሮግራም ላይ ትናንት ማክሰኞ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ከተለያዩ የህክምና ተቋማት ኃላፊዎች እና አዋላጅ ነርሶች ጋር በተደረገ ውይይት ላይ እንደተገለፀው፤ እናቶች ወደ ህክምና ተቋማት በሚሄዱበት ወቅት ባለሙያዎች ከሙያው ውጪ የሆነ ሥነ-ምግባር ስለሚያሳዩዋቸው ወደ ጤና ተቋማት አለመምጣትን ይመርጣሉ። የተለያዩ እናቶችን ግብረመልስ ለማግኘት ከእናቶች ጋር ውይይት ተደርጐ እንደነበረ የገለፁት የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ አለምፀሐይ ጳውሎስ፤ በውይይቱ ወቅት በርካታ ሴቶች በጤና ተቋማት የተለያዩ ከሥነ-ምግባር ውጪ የሆኑ ተግባራት ስለሚፈፀሙባቸው በቤታቸው ውስጥ ለመውለድ መገደዳቸውን ገልፀዋል ብለዋል። እናቶች ወደ ጤና ተቋማት ሲሄዱ የጤና ባለሙያዎቹ አፀያፊ ቃላትን ከመናገር አንስቶ እስከመማታት የሚደርሱ አላስፈላጊ ተግባራትን እንደሚፈፅሙባቸውም ነው የተገለፀው።

እናቶች በምጥ ወቅት ወደ ጤና ተቋማት ሲያመሩ የሚቆዩበትን ቦታ እንኳን ማግኘት ስለማይችሉ እና ባለሙያዎችም ትኩረት ስለማይሰጧቸው በቀላሉ እርዳታ ሊያገኙ ሲችሉ ህይወታቸውን ያጣሉ። በዚህም ሳቢያ በከተማዋ ከሚሞቱ እናቶች መካከል 35 በመቶዎቹ አስፈላጊውን የባለሙያ እርዳታ ሳያገኙ ለረጅም ጊዜ ደም ፈሷቸው የሚሞቱ ናቸው ተብሏል።

በውይይት መድረኩ ላይ የቀረበ ጥናት ውጤት እንዳመለከተውም፤ ለእናቶች ሞት ዋና ዋና ተብለው ከቀረቡት ምክንያቶች ውስጥ የህክምና መሣሪያ እጥረት እና የባለሙያው የሥነ-ምግባር ችግር ተጠቃሽ ናቸው ብሏል። ከዚህ በተጨማሪም እናቶች በአዳዲስ ጤና ተቋማት ለመገልገል ፈቃደኛ አለመሆን እንደ ምክንያት የተጠቀሰ ሲሆን፤ በአንድ ወር ውስጥ አንድ እናት እንኳን ሳያዋልዱ የሚቀሩ አዳዲስ ጤና ተቋማት በአዲስ አበባ እንዳሉ ተገልጿል። በከተማዋ ካሉ ጤና ጣቢያዎች መካከል በጣም ጥቂቶቹ ብቻ የእናቶች ሞት ቅኝት ሪፖርትን ወቅቱን ጠብቀው እንደሚያቀርቡ የተገለፀ ሲሆን፤ በዚህም ምክንያት በየጊዜው የሚሞቱ እናቶችን ትክክለኛ ቁጥር ለማወቅ ችግር እንደፈጠረ ነው ጥናቱ ያመለከተው።

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት ባለሙያዎች በበኩላቸው በጤና ጣቢያዎች ደረጃ መታከም ለማይችሉ እናቶች ወደ ሆስፒታሎች ሪፈር ሲፅፉ በሆስፒታሎች ያለውን አቀባበል እንደተጨማሪ ችግር አንስተዋል። ባለሙያዎቹ እንደሚገልፁት ከሆነ፤ እናቶች ወደ ሆስፒታል ሪፈር ተፅፎላቸው በሁለት እና ሦስት ሆስፒታሎች ተቀባይነት ማግኘት ሳይችሉ ቀርተው ተመልሰው በጤና ጣቢያ ለመውለድ ይገደዳሉ። በዚህ መካከልም ህይወታቸውን ያጣሉ ብለዋል።

Receive Ethiopian News and Videos by email. Sign up for Email alerts ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን፣ ጠቃሚ ምክሮችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜሎን ያስመዘግቡ።