Entertaining interview with Dana Drama actress Bezawit Mesfin አዝናኝ ቆይታ ከዳና ድራማ ተዋናይት ቤዛዊት መስፍን ጋር
የተወለደችው በደብረ ማርቆስ ከተማ ቀበሌ ዘጠኝ የሚባለው አካባቢነው፡፡ በልጅነቷ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በተለምዶ አስራ ሥምንት ማዞሪያ የሚባለው አካባቢ አደገች ፡ ፡ ገና በለጋ እድሜዋ እሷ ሳታስበው የኪነጥበብ ፍቅሩ ቀድሞ በሯን አንኳኳ፡፡ የመጀመሪያ ስራዋ ብዙም ነፍስ ባላወቀችበት ጊዜ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ሆና የሎተሪ ማስታወቂያ እንድትሰራ ተጋበዘች ፤በሎተሪ ማስታወቂያ የጀመረችው ስራ እሷ ባላሰበችው መንገድ ገፍቶ ገፍቶ እዚህ እንዳደረሳት የምትናገረው የዛሬዎ የመሿለኪያ አምዳችን እንግዳ ቤዛዊት መስፍን ትባላለች፡፡ ወጣቷ ተዋናይ ቤዛዊት መስፍን በአሁኑ ወቅት ከዘጠኝ በላይ የሚሆኑ ፊልሞች የሰራች ሲሆን ‹ጊዜ ግዙን› የተባለ ፊልምም ፕሮዲውስ አድርጋለች፡፡ በኢትዮጲያ ቴሌቨዥን በሚቀርበው ዳና ተከታታይ የቴሌቨዥን ድራማ ለየት ባለ ገፀ ባህሪ አጨዋወቷ በመልካቾች ዘንድ ተወዳጅነትን አትርፎላታል፡፡ ከቤዛዊት ጋር የነበረን ቆይታ ይህን ይመስላል፡፡
ቁም ነገር፡- ብዙ ጊዜ የምትጫወቻቸው ገፀ ባህሪዎች ቀልቃላና በጥባጭ መሆናቸው በሥራሽና በማህበራዊ ህይወትሽ ላይ ተጽዕኖ አይፈጥርብሽም?
ቤዛዊት፡- አዎ በጣም ተጽዕኖ አለው፡፡ ሌላው ይቅርና ከቤተሰቦቼ ብጀምርልሽ እነሱ በቅርበት የሚያቁኝ እንደዛ ካሰቡ ሌላው የማያቀኝ ተመልካች ምን ሊል እንደሚችል መገመት ትችያለሽ፡፡ አያቴ ሁል ጊዜ ‹‹አሁን በቴሌቭዥን እንዲህ ስትንቀዠቀዢ የሚያይሽ ቁም ነገረኛ አድርጎ አያስብሽም፤ ቆይ አሁን አንቺ እንዴት ነው ትዳር የምትይዥው ›› እያለች ትጨነቃለች፡፡ ብዙ ሰው ቁም ነገረኛ አድርጎ አያስበኝም ፤ሳወራ የምቀልድባቸው ወይም ሙድ የምይዝባቸው ነው የሚመስላቸው፡፡ በኔ አይተማመኑም የሆነ ቦታ ቀጥረውኝ አስሬ ግን ትመጫለሽ ‹‹ግን ትመጫለሽ፤›› እያሉ ይጠይቁኛል፡ ፡ ቀረጻ እንኳን ሆኖ፤ የዚህ ምክንያቱ አንዱም የገፀ ባህሪያት መደጋገም ቢሆንም የፊት ገጽታዬ በራሱ ቀልቃላ፣ ቀበጥ፣ ግዴለሽ እመስላለሁ መሰለኝ፡ ፡ ሰው ደግሞ ቀርቦ ካላየሽ በስተቀር መጀመሪያ ከላይ አይቶሽ ነው የራሱን ግምት የሚወስደው፡፡
ቁም ነገር፡- ዕድሜሽን መናገር አሳፍሮሽ ያውቃል ? ዕድሜሽ ስንት ነው?
ቤዛዊት፡- አዎ ድሮ ትምርት ቤት እያለሁ ዕድሜዬን ሲጠይቁኝ እናደድ ነበር፤ ምክንያቱም ትንሽ ስለነበርኩ እኔ ደግሞ እንደ ትልቅ ነው መታየት የምፈልገው፡፡ አሁን ደግሞ ሲጠይቁኝ ትንሽ ይደብረኛል፤ ሄድኩኝ እኮ የዕድሜን ቁልቁለት /….ሳቅ/፡፡ አሁን ሃያ አራት አመቴ ነው፡፡
ቁም ነገር፡- የምትወጂው መጠጥ ምንድ ነው?
ቤዛዊት፡- ጠላ! /…ሳቅ/ ጠላ በጣም በጣም ነው የምወደው፡፡ ያውም ይሄ ዝምብሎ ምናምን አይደለም፤ አለ አይደል ቆይቶ የሚቆመጥጠው ፤ ልክ እንደ ቅራሪ ?እሱነው የምወደው፡፡ እቤት እራሱ በቁም ነገር ጠላ የሚጠምቁት እኔ በጣም ስለምወድ ለኔ ብለው ነው፡፡
ቁም ነገር፡- ድብን ያለ ፍቅር እንዴት ያደርጋል? አንቺን ይዞሻል?
ቤዛዊት፡- ያቅለሸልሻል! የሆነ አየር የሚያሳጣ፤ ከተሳካ በጣም ደስ ይላል፡፡ ድብን ያለፍቅር ይዞኛል፤ ጆሮዬ ሁሉ ተደፍኖ /…ሳቅ/ አላይ ሲጠሩኝ አልሰማ /…..ሳቅ/ ብቻ አየር ያጥራል፡፡
ቁም ነገር፡- ትዳር በልጅነት ሲሆን ጥሩ ነው ይባላል፤ አንቺ በዚህ ሀሳብ ትስማሚያለሽ?
ቤዛዊት፡- ውይ አዎ በጣም ! /….ሳቅ/ ትዳር በልጅነት ደስ ይላል፤ልጅ በልጅነትም እኔ በጣም ደስ የሚል ነው የሚመስለኝ፡፡ እኔ ባላገባም በልጅነታቸው ያገቡ ጓደኞቼንም ሆነ ሌሎች ሰዎች ስመለከታቸው ከኛ ካላገባነው በተሻለ ለህይወት ትርጉም አላቸው፡፡ ደስተኞች ናቸው፡፡ ህይወት ትርጉም የሚኖረው ልጅ ሲኖርሽ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ትዳር ያላቸው ሀላፊነት ይሰማቸዋል ፤ ይበልጥ ጠንቃቃ ብልህ ሲሆኑ፣ራሳቸውን ሲጠብቁ ነው የማየው፡፡
ቁም ነገር፡- ሙያሽን የጠላሽበት ጊዜ አለ?
ቤዛዊት፡- አዎ ! መቼ መሰለሽ የምጠላው አንዳንዴ ማግኘት ያለብሽን ክብር ማግኘት አለብሽ፤ ተዋናይ ስለሆንኩ አይደለም፤አንዳንዴ ፕሮዲውሰሮች ከሌላ ሙያ ወይ ገንዘብ ስላላቸው በአጋጣሚ የምገቡበት ነገር አለ፤ለሰው ክብር አይኖራቸውም ፡፡ አንዳንድ ዳይሬክተሮች ደግሞ አሉ በቃ አሰለቺ የሆኑ፤ ወይ እንዳትተይው እሷ እኮ ጥሩ ጸባይ የላትም እያሉ ሌላ ስራ እንዳትሰሪ ያደርጉሻል፡፡ አሁን ለምሳሌ በጣም አስመሽተው ካሰሩን መሸኘት አለብን፡፡ በተለይ ሴት ከሆንን የግድ ነው በምሽት ብዙ ነገር ሊገጥመን ይችላል ፡፡ ያንን እንደ መጥፎ ጸባይ የሚያዩት አሉ፡፡ በስራ ምክንያት እዛው ቀረፃ የሚደረግበት ቤት ሁለት ሦስት ቀን ልናድር እንችላለን፤ በዛን ጊዜ ምግብ በሥርአቱ ልንበላ ይገባል፡፡ ቀረፃ እየተጓተተ ደጋግመው ሲያሰሩሽ በጣም ያሰለቻል፤ ብቻ ውስጡ ብዙ ችግሮች አሉት፤ እነዚህ ችግሮች ሲመጡ ወይኔ በቃ ይሄ ስራ ያስጠላል እላለሁ፡፡ ለስራውና ለሙያተኛው ክብር የሌላቸው ባለሙያዎች ሲያጋጥሙኝ በጣም ያማርራል፡፡
ቁም ነገር፡- ከሞቱ ሰዎች መካከል የማስነሳት ዕድሉ ቢሰጠሸ ማንን ታስነሻለሽ?
ቤዛዊት፡- እኔ እናቴንም አባቴንም ልጅ ሆኜ ነው ያጣኋቸው፤ ታናሽ እህቴን ደግሞ በቅርቡ ነው በሞት ያጣኋት ፤አንዴም ሁለቴም እሷ ትነሳልኝ፡፡ እኔ ሁላ ሞቼ እሷ ብትነሳ አልደራደርም፡፡
ቁም ነገር፡- የሚስኮል ጥቅሙ ነው ጉዳቱ የሚያመዝ ነው?
ቤዛዊት፡- እንዴ ጥቅሙ ነው እንጂ የሚያመዝ ነው፡፡ እኔ እንደውም ኮልሚ ባክ በመላክ አንደኛ ነኝ፡፡ ካርድ መሙላት አልወድም፡፡ ገዝቶ መሙላት የሚሉት ነገር በጣም ይጨንቀኛል፤ ትልቅ ስራ ነው የሚመስለኝ፡፡ ብዙ ጊዜ እኔ ኮልሚ ባክ ነው የምልከው፡፡ ቢኖረውም ተሳስቼ እሞክራለሁ፡፡
ቁም ነገር፡- ዳጉሳ ምንድ ነው፡፡ ለምን አገልግሎት ይውላል?
ቤዛዊት፡- እንዴ! ምነው የት እንደ ተወለድኩ ነግሬሽ! ሌላ ከበድ ያለ ጥያቄ አጠይቂኝም? ዳጉሳ እህል ነዋ፤የሚጠቅመው ለመሰበር፡፡ ይሄ እንትን ጉልበት የሚሰብረው ነገር አይደል ? ውይ ጎጃሜ ነኝ ብዬ አቅራርቼ ጠፋኝ! /…….ሳቅ/ /ትንሽ እንደማሰብ/ ውይ ካሰብኩትማ ጭራሽ ይጠፋብኛል፡፡
ቁም ነገር፡- ተዋናይ ባትሆኚ ኖሮ በምን ሙያ ውስጥ እናገኝሽ ነበር?
ቤዛዊት፡- ነጋዴ እሆን ነበር፤የተማርኩት ራጉኤል መርካቶ ነው፡፡ ትምህርት ቤት ስገባም ሆነ ስወጣ የማየው እሱኑ ነው፡፡ ኮሌጅም ገብቼ የጀመርኩት ማርኬቲንግ ማኔጅመንት ነበር፤ የቤተሰቦቼም ስራ ንግድ ስለሆነ ያንን ነው ላደርግ የምችለው፡፡ አሁንም ቢሆን ወደፊት ወደ ንግዱ መሄዴ አይቀርም፤ በዚህ ሙያ ብቻ ተወስኜ መቅረት አልፈልግም፡፡
ቁም ነገር፡- በአሁኑ ጊዜ የወጣቱ አንገብጋቢ ጥያቄ ምንድ ነው ትያለሽ?
ቤዛዊት፡- ብር ነዋ! ምን ጥያቄ አለው፡፡ ወጣቱ ብር ማግኘት ነው የሚፈልገው፡፡ ምክንያቱም ምንም ነገር ለማድረግ ብር ያስፈልጋል፡፡ መብላት ቢፈልግ ብር ያስፈልገዋል ፤ካልበላ መ ኖር አይችልም ፡፡ ቤተሰቦቹን መርዳት ቢፈልግ ብቻ አብዛኛው ነገር በብር ነው የሚገኘው፡፡
ቁም ነገር፡- እቁብ ትጥያለሽ ? የእቁብ ጥቅሙ ምንድነው?
ቤዛዊት፡- ከቤተሰቦቼ ጋር የሆነ ጊዜ ጀምሬ ነበር፤በኋላ ላይ አፍሬ ተውኩት፡፡ ልክ እቁብ የሚከፈልበት ቀን ሲደርስ እበሳጫለሁ በዚህ የተነሳ ተውኩት፡፡ ጥቅሙ ገንዘብ ይጠራቀማል ፣እንደልብ የሚወጣ ገንዘብ አይደለም፤ ሲደርስ አንዴ ጠርቀም ብሎ የሚመጣ ስለሆነ ደና ነገር ይደረግበታል፡፡
ቁም ነገር፡- ከቀናተኛና ከተጠራጣሪ የትኛው ይሻላል?
ቤዛዊት፡- በፍቅር ግኑኙነት ውስጥ ከሆነ ቅናት አንዳንዴ ፍቅር ነው፡፡ ያንን ስው በጣም ስለምትወጂው ነው የምትቀኝው፡፡ መጠራጠር ግን ማንኛውንም ሰው አለማመን ነው ፡፡ እሱ በጣም መጥፎ ነው፡፡ አለማመን ሁሌ ህመም ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ ቅናት ይሻላል፡፡
ቁም ነገር፡- ሰው ሁሉ ወደ እንስሳት የሚቀየርበት አጋጣሚ ቢከሰት፤ የትኛውን እንስሳ መሆን ትመርጫለሽ?ለምን? ቤዛዊት፡- ወፍ ! በባህሪዬ ችኩል ስለሆንኩኝ የምፈልግበት ቶሎ ለመድረስ መብረር እፈልጋለሁ፡፡ ክንፍ ኖሮኝ ብበር ደስ ይለኛል፡፡
ቁም ነገር፡- ፊልም ከመስራትና ቴአትር ከመስራት የትኛው ይከብዳል?
ቤዛዊት፡- እንዴ ሁለቱን ምን አገናኘው! ፊልም እኮ ማስተካከል ይቻላል፡፡ ብትሳሳቺ፣ ከስሜት ብትወጪ ሰዎች እየተከታተሉ እንዲ አድርጊ፣ እንዲህ ይሻላል ትባያለሽ፡፡ ድንገት ትወናሽ ጥሩ ባይሆን በድጋሚ ትቀረፂያለሽ፤ ወይ ለሌላ ቀን ይተላለፋል፤ ሊቆረጥም ይችላል፡፡ ቴአትር ግን ተለማምደሽ ፣ተለማምደሽ ብዙ ጊዜ ቢፈጅም የተለማመድሽውን ነገር መድረክ ላይ ቁጭ ማድረግ ነው፡፡ ሰዉ ሊከተልሽ ይገባል፤ ስታለቅሺም ስትስቂም ስሜት ሊኖረውና አሳማኝ መሆን አለበት ፡ ፡ ስለዚህ ቴአትር በጣም ከባድ ነው ፡፡ የተዋናይን ብቃት ይፈትናል፡፡ ዝም ብሎ ተዘሎ የሚገባበት ነገርም አይመስለኝም፡፡
ቁም ነገር፡- ፅንስ ማስወረድ ወንጀል ነው ? ሀጥያት?
ቤዛዊት፡- ወንጀል ነው ከተባለ፤ ወንጀልነቱን የምናውቀው ሲታወቅ ወይም ሲጋለጥ ነው፡፡ ግን ወንጀል ነው ብለን ከምናስብ ይልቅ ሀጥያት ነው ብለን ብናስበው የተሻለ ነው፡፡
ቁም ነገር፡- በቀን ውስጥ ምን ያህል ገንዘብ ታጠፊያለሽ?
ቤዛዊት፡- እንደ ሁኔታው ነው፡፡ ከቤት ከወጣሁ ላጠፋ እችላለሁ፡፡ በትንሹ ከመቶ ብር እስከ አንድ ሺህ ብር ላወጣ እችላለሁ፡፡
ቁም ነገር፡- አሁን ባለው የሀገራችን የፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ በአብዛኛው የሚሰራው የኮሜዲ ዘውግ ያላቸው ፊልሞች ናቸው፡፡ ባለሙያዎች ለዚህ እንደ ምክንያት የሚያቀርቡት ተመልካቹ የኮሜዲ ስራ ብቻ ስለሚፈልግ ነው የሚል ነው፡፡ አንቺ በዚህ ሀሳብ ትስማሚያለሽ?
ቤዛዊት፡- በፍጹም አልስማማም፡ ፡ ትራጄዲም ሆነ ድራማ በደንብ ታስቦበት በጣም ጥሩ አድረገን ከሰራ ነው ተመልካች አያጣም፡፡ ምንድንው ችግሩ ትራጄድም ሆነ ደራማ ኮሜዲን በምንሰራበት ኃይል ወይም ሀቅም አይደለም የምንሰራው፡፡ እንደ ኮሜዲው አይቀልም ፤እያንዳንዱ ነገር ጥንቃቄ ይጠይቃል፡፡ ለዚ መድከም ስለማይፈለግና ወጪም ለመቀነስ ሲባል በቀላሉ ኮሜዲ ፊልም ይሰራል፡፡ ፊልምም ሆነ መዝናኛ ነገር ሁሉ ሁል ጊዜ የሚያስቅ ነገር ብቻ መሆን የለበትም፡፡ የምንማርበት ውስጣችን የሚቀርና የገሀዱ ዓለም ነፀብራቅም መሆን አለበት፡፡ ኑሯችን ደግሞ የምናውቀው ነው ሁል ጊዜ ሳቅ የለበትም፡፡
ቁም ነገር፡- በመጨረሻ የጠቅላላ ዕውቀት ጥያቄ ነው የቀረን፤‹የታንጉት ሚስጥር›፣ ‹አደፍርስ›፣ ‹መረቅ› የነዚህ መጸሐፍቶች ደራሲዎቻቸው ማን ይባላሉ? ቤዛዊት፡- ሁሉንም አላቃቸውም፡፡ እንዲህ የሚባል መፅሐፍ አለ እንዴ ? እኔ ስልቹ ስለሆንኩኝ ብዙ አላነብም፡፡ አሁን አሁን ግን የግድ ማንበብ ስላለብኝ በወር ውስጥ አንድ መጽሐፍ ለማንበብ እሞክራለሁ፡፡ ቁም ነገር፡- አመሠግናለሁ፡
ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን፣ ጠቃሚ ምክሮችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜላችሁን አስመዘግቡ።