የኢትዮጵያውያን ልጆች የአሰተዳደግ ችግር በአሜሪካ

በከበደ ሃይሌ

የኢትዮጵያውያን ልጆች የአሰተዳደግ ችግር በአሜሪካ በሚል ርዕስ በወጣት ልጆች አስተዳደግ ጉዳይ ላይ ያተኮረው አዲስ መጽሐፍ ታትሞ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ በአሜሪካ የሚኖሩ ወላጆች የገጠማቸውን የልጆች የማሳደግ ችግር፤ በምግባረ ብልሹ ወጣቶች ላይ ስለሚንጸባረቁ ባህርያትን የሚዳስስና ለችግሩ መፍትሄ ይሆናሉ ተብሎ ከባለሙያዎች የተሰጡትን ምክሮችና ከርዕሱ ጋር ቀጥታ ተዛምዶ ባላቸው ነጥቦች ዙሪያ ያጠነጠነ መጽሐፍ ነው፡፡

መጽሐፉ በተለይ በአሜሪካ በሚኖሩ ወጣቶችና በወላጆች መካከል ስላለው የአስተዳደግ ችግር ላይ ይበልጡን ያተኩር እንጂ ተመሳሳይ የማህበራዊ ችግሩ በአገር ቤትም መስፋፋቱን ከእነምክንያቶቻቸው ይገልጻል፡፡የጥናቱ ፍሬ ሃሳብ ወጣቶች የሚያሳዩትን ጸረ-ባህል ምግባር በማስተካከል ለትምህርታቸው ትኩረት እንዲሰጡ፤ የወላጆች ነጸብራቅ ሆነው እራሳቸውንና ህብረተሰቡን በጥሩ ስም እንዲያስጠሩ ለማድረግ ወላጆች ስለሚወስዱት ባህላዊ የድስፕሊን እርምጃ፤ ብሎም የባህል ቅርሳቸውን ለልጆቻቸው ለማስተላለፍ የሚያደርጉት ጥረት እንዳይሰምር የተፈታተናቸውን የአካባቢ ተጽዕኖ ለመቋቋም ስለሚያደርጉት ተጋድሎ ይዳስሳል። የዓለም ህብረተሰብ ተሰባስቦ በሚኖርባት አሜሪካ እየኖሩ ችግሩን ለማቃለል ወላጆች በወሰዱት እርምጃ በአጻፋው የደረሰባቸውን የማህብርዊ ችግሮች፤ህጋዊና የአኗኗር ጉስቁል ከማብራራቱም በላይ ከቤተሰብ ጉያ የወጡትንና በባሕርያቸው የተገለሉ ልጆችን ጠባይ ለማስተካከል የሚረዱ የባለሙያዎችን ምክር አቅፏል፡፡እንዲሁም የጤና ችግርና የአካል ጉዳት ያለባቸው ልጆችና ቤተሰብን ለመርዳት ስለተቋቋመው ህጋዊ ድርጅት ህልውና እና ስለሚሰጠው ግልግሎት ይጠቁማል፡፡

በተለይ በአሜሪካ ልጆች የሚያሳድጉ ወላጆች በገጠማቸው የኑሮ ውጣ-ውረድ ምክንያት ወጣቶች ከወላጆች ቁጥጥር ውጭ ለመሆን በቅተው ከወላጆቻቸውና ከኮሚኒቲው በአካልና በምግባር ርቀዋል፡፡በእርግጥ ወላጆች ልጆቻቸውን መከታተል ተስኗቸው ነውን፤ የባህል መበረዝ፤የትውልድ ዘመን ልዩነት፤ ወይስ የወጣቶች ፍላጎት ያለሟሟላት ነው ስለሚሉትና ስለሌሎች ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል፡፡እንኝህ የማህበራዊ ችግሮች በኢትዮጵያም ሊዳረስ የቻለው ከኢኮኖሚ፤ከፖለቲካና ከማህበራዊ ኑሮ አኳያ በማያት የኢትዮጵያ መንግሥትና ወላጆች የችግሩ ዋነኛ ተቋዳሽ እንደሆኑ ያስረዳል፡፡

ወላጆች ከአገራቸው የተሰደዱበት ምክንያት አንዱ ልጆቻቸውን በማስተማር እራሳቸውን ችለው ሲተዳደሩ ለማየት ነበር፡፡ነገር ግን የኑሮው ውጥረትና በየግል ምክንያቶቻቸው በልጆቻቸው የት/ቤት ጉዳይ ላይ ተሳትፏቸው እጅግም በመሆኑ ለልጆቻቸው ምግባር መበከል ምክንያት ሆነዋል ይባላል፡፡ሆኖም ልጆቻቸው ባህሪያቸው የመለወጥ ምልክት ሲያዩባቸውና በትምህርታቸው ደክመው ሲታዩ ችግሩን ለመቅረፍ ከምክክር እስከ ባህላዊ የሰውነት ቅጣት መስጠት እየደረሱ በህግ የመጠየቅ ደረጃ ላይ የደረሱ ወላጆች አልታጡም፡፡የባህል ቅርስን በማስተላለፍ ረገድ ከመኖሪያ ቤት እስከ ማኀበራዊ ሥፍራ የቻለም ወደ አገር ቤት በመላክ የወላጆቻቸውን ባህልና የሕዙብን አኗኗር እንዲረዱ ቢያደርጉም የሚኖሩበት አካባቢ ተጽዕኖ ስለተፈታተናቸው ያቀዱትን ያህል እንዳልተራመዱ ያብራራል፡፡ በመሆኑም ወላጆች ልጆቻቸው ተምረውና በመልካም መግባር ታንጸው እራሳቸውን በመቻል ይጦሩናል የሚለውን አስተሳሰብ ትተው እራሳቸውን ችለው ሲተዳደሩ ባሳየን ማለት ጀምረዋል፡፡

በተጨማሪም ወላጆች ለልጆች፤ልጆች ለወላጆች ያልተመቻቸበት ምክንያት የኢኮኖሚ ውድቀት፤የኑሮ ውድነት፤ የወላጆች የሥራ ፈረቃ ያለማመቻቸት፤ ቴክኖሎጂ፤ ነጋዴዎች፤ አምራቾች፤ ሕግጋት፤ ፖለቲካና የብዙሃን መግለጫ ህትመቶች ለጥቂት ወጣቶች ሥነ-ምግባር መለወጥ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ የሚገልጹ መረጃዎችን ያቀፈ ስለሆነ የበለጠ ግንዛቤ ለማገኘት መጽሐፉን አግኝቶ ማንበብ ይመከራል፡፡

መጽሐፉ ወቅታዊና ሁልገብ በሆኑ የወጣቶች ማህበራዊ ችግሮች ላይ ጥናት ተደርጎበት የተዘጋጀ ስለሆነ ልጆች የሚያሰድጉና ታሳቢ የሆኑ ወላጆች የቅብጥብ ወጣቶችን ችግር በቅድሚያ ለመገንዘብና መፍትሔ ለማግኘት ይረዳ ዘንድ ችግሩ የደረሰባቸው ወላጆችና ወጣቶች የኑሮ ተሞክሮአቸውን ለአንባቢያን ለማካፈል የሰጡት ቃለ ምልልስ መጽሐፋ አቅፏል፡፡

ስለሆነም መጽህፉን ለማግኘት የሚፈልግ አንባቢያን አትላንታ በሚገኙት የኢትዮጵያውያን የንግድ ድርጅቶች አማካይነት ማግኘት ይቻላል፡፡