ቅጥረኛ ሐበሾች
ከሄኖክ የሺጥላ
ሳስበው አንድ የጋንግ ቡድን ያለ ይመስለኛል ። በፊት ለፊት በር ሀገር ሀገር የሚል ፣ በጉዋሮ በር ከሱ ሌላ ቀና ያለ ካለ ፣ እየጠበቀ በመዶሻ የሚያስመታ ፣ የሚመታ ። ሳስበው አንድ እንዲሁ በድፍኑ በደጋፊነት ታውሮ ፣ ከሚያምነው ነገር / ድርጅት / በስተቀር ምንንም ለማመዛዘን ጊዜ የሌለው ፣ እሱ ስለሚለው ብቻ እንድታወራለት ሰው ሳይሆን አፍ ሆነህ የተፈጠርክ የሚመስለው ፣ እጅግ ስር የሰደደ የፖለቲካ ዳፍንት በፖለቲካ ጠበብትነት ተተክቶ ፣ በየሄደበት እኛ እያለ የሌለ ማንነቱ ላይ ፈርኦናዊ ተክለ ሰውነት የተላበሰ ጉም ፖለቲከኛ ያለ ይመስለኛል ። እንዲሁ ይሸተኛል ። እንዲሁ ሳስበው ደጋፊ የሚለው ቃል ተደጋፊ ከሚለው ጋ የተወራረሰ ይመስለኛል ። እንዲሁ ሳስበው አባላት የሚለው አባባል ” በላት ” ወይም በላዎች ከሚለው ጋ የተሰናሰነ ይመስለኛል ። እንዲሁ ዝም ብዬ ሳስበው አንድ የሆነ ተአምር እፈጥራለሁ የሚል ካቦ እና ተአምር ይፈጠራል ብለው የሚያወሩ ደቂቆች ፣ በሚፈጠረው አስማት ለመደመም በጣም ከመጉዋጉዋታቸው የተነሳ ሕልም እንኩዋ ለማየት ፍቃደኛ የማይመስሉበት የፖለቲካ ስሜት የፈጠሩ ይመስለኛል ። የሽር ጉድ ፖለቲካ !!! እንዲሁ ሳስበው ፣ ውሽት ከመልመድ አልፈን ማስተማርና ማቀሰስ የጀመርን ይመስለኛል ። እንዲሁ ዝም ብዬ ነገሩን ሳጤነው ጠኔኝነት ማለት እንዴት ፣ ለምን ፣ ወዴት ብሎ አለመጠየቅ ነው ተብሎ የታመነ ይመስለኛል ። እንዲሁ ሳሰላስል ፣ አካሄዳችንን ቁጭ ብዬ ስቃኘው ያልተሰራ ቤት ሊያከራይ ላይ ታች የሚል አይነት ደላላ ነገር ይሰማኛል ። ወይም ደሞ ” የግቢው ስሚንቶ እግዜርን ካልፈሩ እንጀራ አንጥፈው ይበሉበታል ” ብሎ ሊያግባባ የሚያስብ አይነት ደላላ ።
ብቻ አሁን ያለንበትን ሁኔታ ሳስበው በትክክል ዘመኔ ያደረሰብንን የሞራል ኪሳራ ፣ ይሉኝታ ቢስነት እና ቅጥፈት ግልጽ አድርጎ ያሳየኛል ። እንዲሁ ሳስበው ” ዛሬም ዲግሪ ከድግር ” የተሻለ ነገር መስራት እንዳልቻለ እረዳለሁ ። ዛሬም መነሻችን ገበሬው መድረሻችን ግን የቡድን ፖለቲካ እንደሆነ ይሰማኛል ። ዛሬም ምንም አልተማርንም ። የምናማርራቸው ፣ የምንጠላቸው ፣ ወይም የምንጠየፋቸው እድሜ ጠገብ የፖለቲካ ድርጅቶች ” ይህን አረጉ ወይም እንዲህ ናቸው ” ብለን ተናግረን ሳንጨርስ ፣ የተናገርነው በኛ ሲከፋ አየሁ ። መብላቱ ፣ መበላላቱ ፣ የተሻለ ብቅ ሲል ትግሉ የውርስ ይመስል ከኔ ወዲያ ላሳር ማላቱን እያየን ነው ። ይሄ ማንነታችን ይቀጥላል። ደሞ ታጋይነታችንም እንዲሁ !
በዚ በመሰሪ ፖለቲካ ብዙ ሰዎች ተገፍተው ከሜዳው ወጥተዋል ። እኔ ዶ/ር ጥላሁን በዚህ በመሰሪ የፖለቲካ መዳፍ ተመተው ነው ከጫወታ የወጡት ፣ እነ ዶ/ር ታዬ ወ/ሰማያት የተቀመጠላቸውን ቦምብ ረግጠው ነው በራቸውን ዘግተው ቁጭ ያሉት ፣ ሌሎችም ብዙ አሉ ። ቤቱ ይቁጠራቸው ። አሁን አሁን እየገባኝ ያለው ነገር ኢትዮጵያዊነት ማለት የአንድን ድርጅት ፖለቲካዊ ዲስኩር ማቀንቀን እንደሆነ ተረድቻለሁ ። እኛ ማለት ሕዝብ ሳይሆን የተወስኑ እና ራሳቸውን ያበዙ ኢምንቶች ስብስብ እንደሆነ ይሰማኛል ። ሀገር የሚለውን ነገር ሳስብ ፣ በዚች አዛዥ ነዛዥ በሌላት የቁንጽል ፖለቲከኞች ፖለቲካ የተሰፈረች ባለቤት የሌላት ትንሽዬ ሰፈር ነገር አስመስለዋታል ። በግራም በቀኝም በፍክክር የተጠመደች ሀገር ። በልጅነቴ አያቴ ሞሰቡ ውስጥ አንድ ዳቦ አለ ቀድሞ ከትምህርት ቤት የደረሰ ይብላት ይሉ ነበር ። ይህንን የሚሉበት ምክንያት መንገድ ለመንገድ ስንጫወት አደጋ እንዳይገጥመን ለዛች ለአንድ ዳቦ ስንል ቤት በጊዜ እንድንገባ ነበር ። ታዲያ አያቴ ያልገባቸው አጎቴ እየተማረም ስለ ዳቦዋ ነበርና የሚያስበው በዛች ባንድ ዳቦ ምክንያት መጨረሻ ላይ የወጣለት ሰነፍ ተማሪ ሆነ እኔም የአጎቴን ነገር ካየሁ በሁዋላ ምግብ ጠላሁ ። አሁንም አንድ ዙፋን አለችና ቀድሞ የደረሰ ይውሰዳት የተባለ ይመስል ፣ ሰው ሰነቱን ረስቶ በያለበት ስለ ዙፋኗ ነው የሚያስበው ። በእውነት ያሳዝናል !
ትግላችን ለመሻል ሳይሆን ለመሻሻል እየመሰለኝ ነው ። በሃሳብ ለመሻል ሳይሆን በኑሮ ለመሻሻል ። በተራችን የኪቤአድ ቤቶችን ለመውረስ ፣ ህንጻዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ፣ የሚንስትር መስሪያቤቶችን እኛም በዘመዶቻችን ለመሙላት ። ነገሩ ሁሉ ይሄንን ይመስላል ። ምክንያቱም ገና በጨቅላነታችን ፣ ገና የትም ሳንደርስ ነገረ ስራችን ሁሉ ይሄንን ያሳብቃልና ። ብቻ ድለላና ፖለቲካ የተምታታብን መሰለኝ ። የሆነ የገባን ብለን ያልነው ግራ የገባንን እንደሆነ እገምታለሁ ። ወይም በቃ እኔ አብጄ ነው !