ባልንጀራውን በሽጉጥ ለሞት ያበቃው በ21 ዓመት እስራት ተቀጣ Man sentenced to 21 years for the murder of colleague

 በ 

በጋራ በሚሰሩበት ጋራዥ ምክንያት በተፈጠረ አለመግባባት በቂም በቀል ተነሳስቶ በሶስት ጥይት ተኩሶ በመምታት በባልንጀራው ላይ ጉዳት በማድረስ የሞት መንስኤ ሆኗል ሲል የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተበት ተከሳሽ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 20ኛ ወንጀል ችሎት ጥር 15 ቀን 2007 ዓ.ም ውሎው በተከሳሽ ላይ የ21 ዓመት ፅኑ እስራት ፈረደበት።

     ዐቃቤ ሕግ በክስ መዝገቡ እንደሚያስረዳው ሟችና ተከሳሽ የቅርብ ግንኙነት የነበራቸው መሆኑን ይዘረዝራል። በክሱም ውስጥ ተከሳሽ በመግደል አስቦ በጥር 26 ቀን 2002 ዓ.ም ከምሽቱ 3፡30 ሰዓት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 19/20 ልዩ ቦታው ራስ ኃይሉ ስፖርት ማዕከል አካባቢ ተከሳሽ አቶ በላይ ታፈሰ ከሟች አላና ኦና ጋር በመሆን በጋራ የሚሰሩበትን ጋራዥ በተመለከተ በተፈጠረ አለመግባባት ቂም በመያዝ ለመግደል እንደተነሳም ክሱ ያትታል። ከላይ በተጠቀሰው ቀንና ሰዓትም ሟች ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ከፀሎት ቦታ ወደቤቱ እየሄደ ባለበት መንገድ ላይ ጠብቆ የወግ ቁጥሩ ባልታወቀ ሽጉጥ ሶስት ጊዜ በመተኮስ ጭንቅላቱ፣ የቀኝ ጎኑ እና የቀኝ እጁ ላይ በመምታት ጉዳት ያደረሰበት በመሆኑና በዚሁ ምክንያትም ሟች ለረጅም ጊዜ በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በነሐሴ 30 ቀን 2003 ዓ.ም ህይወቱ ያለፈ በመሆኑ በፈፀመው ከባድ የሰው መግደል ወንጀል መከሰሱን ያስረዳል።

     ተከሳሽ ድርጊቱን አልፈፀምኩም ሲል ክዶ ቢከራከርም ዐቃቤ ሕግ በሰውና በሰነድ ማስረጃዎች ጉዳዩን ለችሎቱ አቅርቧል። የግራ ቀኙን ክርክር ሲያዳምጥ የቆየው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 20ኛ ወንጀል ችሎትም ተከሳሽ የቀረበበትን ማስረጃ በሚገባ ሊከላከል ባለመቻሉ ጥፋተኛ ያለው ሲሆን፤ በዚህም ባሳለፍነው አርብ ውሎው በተከሳሽ ላይ የ21 ዓመት ፅኑ እስራት ቅጣትን አስተላልፎበታል።

Receive Ethiopian News and Videos by email. Sign up for Email alerts ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን፣ ጠቃሚ ምክሮችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜሎን ያስመዘግቡ።