የክልል ከተሞች የመኖሪያ ቤት ፍላጎታቸውን በምዝገባ እንዲያረጋግጡ መመርያ ተሰጠ Directive given to regional cities to demonstrate their interest to construct condominium houses by registration
ተጻፈ በ ውድነህ ዘነበ
የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የክልል ክተሞች ትክክለኛ የመኖሪያ ቤቶች ፍላጎት መኖሩን በምዝገባ እንዲያረጋግጡ መመርያ ሰጠ፡፡ ሚኒስቴሩ ይህንን መመርያ የሰጠው ትላልቅ የክልል ከተሞች ለነዋሪዎቻቸው የመኖሪያ ቤቶች ለመገንባት ጥያቄ በማቅረባቸው ምክንያት መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ከደቡብ፣ ከኦሮሚያና ከአማራ ክልል ከተሞች የቀረበለትን ጥያቄዎች ከመረመረ በኋላ ሚኒስቴሩ ሰሞኑን ይህንን መመርያ መስጠቱን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ሚኒስቴሩ በሰጠው አዲስ አቅጣጫ፣ በክልል ከተሞች የሚኖሩ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ፍላጎትና የመቆጠብ አቅም በምዝገባ ይረጋገጣል፡፡ ምዝገባው ከተካሄደ በኋላ በተመዝጋቢዎቹ ቁጥር ልክ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ሊካሄድ እንደሚችል የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሸን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ካሳሁን ጎፌ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የመኖሪያ ቤቶች ፈላጊዎች ቁጥር በትክክል ካልታወቀ ግንባታ ማካሄድ አይቻልም የሚሉት አቶ ካሳሁን፣ ከዚህ ቀደም በክልሎች የኮንዶሚኒየም ግንባታ ተካሂዶ ተጠቃሚ መጥፋቱን በማስታወስ፣ ይህ አዲስ መመርያ መሰጠቱን አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት አራቱም የመኖሪያ ቤቶች ፕሮግራም እየተካሄዱ ያሉት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ክልል ውስጥ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በ1996 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የኮንዶሚየም ቤቶች ግንባታ መካሄድ ከጀመረ በኋላ፣ የክልል መንግሥታት በዋና ዋና ከተሞች የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ እንዲካሄድ አድርገዋል፡፡ ነገር ግን ተጠቃሚ ባለመኖሩ ቤቶቹ ቆመው ቀርተዋል፡፡ ነገር ግን ከቆይታ በኋላ የመኖሪያ ቤቶች ፍላጎት በድጋሚ በመቅረቡ የክልል ከተሞች የግንባታ ጥያቄ ለማቅረብ መገደዳቸው ታውቋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በክልሎች የሚገኙ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞች በማኅበር ተደራጅተው የመኖሪያ ቤቶች እንዲገነቡ ሁኔታዎች እየተመቻቹ መሆኑን አቶ ካሳሁን ገልጸዋል፡፡ የከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ ባለፈው ሳምንት ለአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ባደረጉት ንግግር፣ የከተማው አስተዳደር ለመንግሥት ሠራተኞች የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ማካሄድ የሚቻልበትን መንገድ ማመቻቸት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
Receive Ethiopian News and Videos by email. Sign up for Email alerts ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን፣ ጠቃሚ ምክሮችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜሎን ያስመዘግቡ።