የመጽሐፍ ግምገማ – መለስ ዜናዊና የህወኃት የትግል ጉዞ
የመጽሐፍ ግምገማ
መለስ ዜናዊና የህወኃት የትግል ጉዞ
የመጽሐፉ አጠናቃሪ – ኮ/ሌ እያሱ መንገሻ
በሃያ አንድ ማዕራፍ ተከፍሎ በሶስት መቶ አስራ- ሶስት ገጾች የተጎፈጫጨረው ይህ መጽሃፍ ከእጄ የገባው በቅርብ ጊዜ ነበር። ወዲያውኑ ጀምርኩትና አንብቤ ጨረስኩት። ንባብ እንዳይመስላቹህ ትግል እንጂ። ሰው ያኘከው ነገር አልዋጥ ብሎት እንደሚጣጣር ያክል።
የወያኔው አለቃ የህይወት ታሪክና የትግል ጉዞ እዚህ ግባ የማይባል፤ የጸሃፊውን ሃሳብ ለመከተል ግራ የሚያጋባ ባጭሩ በነበሩና በስማ በለው ላይ የተመረኮዘ አልፎ ተርፎም ሃሳቡ ራሱን በራሱ የሚቃረን ነው።
ከአንድ ምዕራፍ ወደ ሌላኛው በተሽጋገርኩ ቁጥር እንደ ሰነበተ እንጀራ ጠጉር አብቅሎ ይጠብቀኛል። እስቲ ግድ የለም ለቀጥል በማለት ወደ መጽሃፉ አጋማሽ ስቃረብ ደግም እጅ እጅ እንደሚል የተልባ ወጥ ቀደም በማለት ያለፍኩትን የመጽሃፍ ከፍል አስታውሶና አሁን ያለሁበትን የመጽሃፍ ከፍል አዳምሮ ሊያስመልስኝ (ሊያስታውከኝ) ትንሽ ነው የቀረው። ድንገት ሳላስበው ወደ መጽሃፉ ሽፋን ተመልሼ ስመለከት ቅጽ አንድ የሚል አየሁና ጭራሹን ዝገነነኝ። ይህ ጸሃፊ ምን አስቦ ይሆን? ሌላ መጽሃፍ – የሚቅጥል – ሱባኤ ያስገባል እንደዛ ከሆነ።
መጽሃፉ ከሽፋኑ ምስል ጀምሮ የፊደላት ንፍገት የሚታይበት፤ የአጻጻፍ ዘይቤው ከዚህ ግባ የማይባል ነው። የሃገራችን ተረት “ውሻ በበላበት ይጮሃል” እንዲሉ ካልሆነ ይህ መጽሃፍ ከመጽሃፍት ተራ ሊሰለፍ አይገባውም። እኔ የመጽሃፉን ይዘት ለመንቀፍ የወያኔን የበረሃ ታሪክ አላውቅም። እሱን ወንድማቸውን ሲገድሉ፤ የሃይል ማመንጫ አውታሮችንና ድልድይን ሲያፈራርሱ፤ በወገናቸው ደም ሲነግድ ለነበሩት ዛሬ በሃገር ውስጥ በስልጣን ላይ ላሉና የወያኔ ፉከራ አስበርግጓቸው በየአለማቱ ለተበተኑ የቀድሞ የህወኃት የመለስ የትግል አጋሮች እተዋለሁ። የእኔው ትችት በይዘቱ ሳይሆን በአቀራርቡ ላይ ነው።
በመጨረሻም ታጋይ (ኮ/ሌ) ኢያሱ ከዚህ መጽሃፍ ግድፈት ተመክሮ ተዘክረው የሚቀጥለው ስራቸው ያማረ እንደሚሆን ተስፋ አረጋለሁ።
አደፍርስ ተሰማ