መነገር ያለበት ቁጥር 8 አብዮቱ ሱማሌ ደርሷል በልጅግ ዓሊ

የአብዮቱን ፍንዳታ ከ40 ዓመት በኋላ ስናስታውስ ሁላችንም በአብዮቱ ሂደት ውስጥ ያየናቸውን ገጠመኞች ማስታወሳችን አይቀርም። በተለይም የ17 ዓመቱን የደርግ አገዛዝ የሁላችንም ትዝታ ነው። ከፊሎቻችን የተደሰትንበት፣ በተስፋ የፈነደቅንበት፣ ሌሎቻችን ደግሞ ያዘንበት፣ የተጎዳንበት፣ ወቅት ነበር። የዝብርቅርቅ ዘመን። በዚህ በደርግ ዘመን ውስጥ የብዙዎቻችን ሕይወት የለወጡ ክስተቶች ነበሩ። አንዳንዶቹ ገጠመኞች አስቂኞች ሊሆኑ ይችላሉ። ግን ደግሞ የሕብረተሰቡን የውስጥ ስሜትን የሚገልጹ ነበሩ። በእኔ አመለካከት እነዚህ በቀልድ፣ ወይም በተረት ወይም ደግሞ በአባባል የሚገለጹ ብሶቶች ናቸው የደርግን ዘመን በደንብ ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩት። ታሪክን ሠሪው ሕዝብ ነውና ከእሱ በላይ ታሪክን ገላጭ አይኖርም።

በደርግ አገዛዝ ዘመን በተለይ በቀይ ሽብር ወቅት የጀርመን ሃገር የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ የነበረው ዶክተር፣ ጀርመናዊ ሚስት የነበረችው ዶክተር፣ ለሃገሬ ትንሽ ብሰራ ብሎ፣ ሕይወቱን አደጋ ላይ ጥሎ፣ወደ ሃገሩ ተመልሶ ይሠራ ነበር ብለን ዛሬ ብንመሰክር ይህንን የማይታመን አፈ ታሪክ አቁሙ ልንባል እንቻላለን። ግን ሆኗልና መነገር አለበት። ካልተናገርንና ካልመሰከርን ደግሞ የታሪክ ተወቃሽ እንሆናለን። በእርግጥም እንመሰክራለን። የአሁኑ ዘመን ስለ ፖለቲከኞች ትልቅነት የሚወራበት ዘመን እንጂ ሃገራቸውን ወደው፣ ሕዝቧን አፍቅረው የቻሉትን ያክል የሠሩትን እንድናስታውስ የሚፈቅድ ዘመን አይደለም። የሆኖ ሁሉ ሆኖ ለዛሬው የአዋሳ የእርሻ ኮሌጅ ዲን የነበረውን የዶክተር ገረመው ኃይሌን ሥራ በጨረፍታም ቢሆን እንየው።

ዶክተር ገረመው ኃይሌበአብዮቱ ወቅት የአዋሳ እርሻ ኮሌጅ ዲን ነበር። ረዘምና ቀጥ ያለ ቁመና የነበረው ሲሆን ዓይኖቹ ጎላ ጎላ ያሉ ነበሩ። ፊቱ ላይ ሽበት ጣል ጣል ያደረገበት ጥቅጥቅ ያለው ጢሙ የአንበሳ ግርማ ሞገስ ሰጥቶታል። በጣም የሚያስፈራው ግን ከዓይኖቹ ውስጥ የሚወጣው አስፈሪ አስተያየቱ ነበር። በሩቅ ሲመጣ ራሱን የማያምነው ተማሪ ሳይታይ ለማለፍ ጥረት ያደርጋል። ገና ኮሌጅ ሳይገቡ ተማሪዎች ስለ ዶክተር ገረመው ብዙ ብዙ በመስማት ፍርሃት ያድርባቸዋል። ቀድመው ኮሌጁ የገቡት ተማሪዎቹም ስለ ዶክተሩ ጀግንነት፣ ዲሲፕሊንና ቆራጥነት እያጋነኑ ለአዲስ ለመጡት ማውራት የተለመደ ነው። ተማሪው ይኽንን እየሰማ ይርበደበዳል። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ሃገሩን በጣም ይወዳል ተብሎም ይሞገሳል።

ዶክተሩን ያወቅሁት ከቀይ ሽብር በኋላ አዋሳ እርሻ ኮሌጅ ገብቼ በነበረበት ወቅት ነው። ተማሪዎች በጣም ስለምንወደው አንተ ነበር የምንለው። ተማሪው አፍሮው ጠጉሩን አሳጥሮ፣ መጥፎ ጸባይ ያለው ጸባዩን አስተካክሎ እንዲመጣ ይነገረዋል። ጩኸት፣ መረበሽ ፣ መደባደብ የሚያስከፍለው ውድ የሆነውን የትምህርት እድል ማጣት መሆኑን ይገለጽለታል። ትምህርቱን ማጣት ደግሞ ለወታደርነት ተመልምሎ ወደ ጦርነት መሄድ ወይም ኑሮ የከበዳቸውን ወላጆቻችን ላይ ሸክም መሆን ስለሆነ በጣም አስፈሪ ነበር። እሱን ባይሆን ሁሉንም በእኩልነት የሚያስተዳደረውን የዶክተር ገረመውን ሥነ ሥርዓት መተዳደርን ማን ጠልቶት? ተማሪው ለመጀመሪያ ጊዜ ከዶክተሩ ጋር የሚተዋወቅበት ስብሰባ(orientation) ይደረጋል። ዶክተሩ ተማሪውን በሞላ አንድ ጊዜ ይመለከትና ይጀምራል።

“አዋሳ ኮሌጅ ለእርሻ ከተመደበልን መሬት ጨምሮ 22 ሄክታር ነው። ። በዚህ ትንሽ ቦታ ከ2000 ሰው የሚበልጥ ሰው አስተዳደር ተብያለሁ። በዚህ ግቢ ውስጥ ሁላችንም በዘፈቀደ የምንኖር ከሆነ እርስ በርሳችን ተጋጭተን እናልቃለን። ስለዚህም መተዳደሪያ ሕግ ያስፈልገናል። የዚህ ግቢ ሃላፊ እኔ ነኝ ። ይህንን የምናግራችሁን ሕግ አስፈጽመዋለሁ። በዚህ አትጠራጠሩ። አብዮት ጥበቃም የሆንክ፣ ቀበሌ ተመራጭ የሆንክ እዚህ ግቢ ተማሪ ነህና ሸጉጥህንም ይሁን ጠብመንጃህን እዛው ደጅህ ጥለህ ና። እዚህ የመጣኸው ልትማር ነው። እዚህ ግቢ ከአንተ የሚያንስ ማንም የለም። ሌላው ቀርቶ እነዚህ ተስፈኛ የሚባሉት፤ እዚህ እየሰሩ ከተማ ውስጥ የሚማሩ፣ የምንረዳቸው ልጆች እንኳን የአንተ የበላይህ ናቸው። የታዘዝከውን መፈጸም አለብህ። መጣላት፣ መደባደብ፣ ሁሉም ከኮሌጅ ያስባርራሉ። መዳራትም እንደዚሁ። ልትማሪ/ልትማር እንጂ ልትራቢ/ልትራባ አይደለም እዚህ የመጣሽው/የመጣኸው።“

ተማሪዎቹ ስንስቅ

“እውነቴን ነው የምለው ምን ትገለፍጣለህ? ድሮ ደርግ እረኛውን ነበር የሚልከው አሁንስ በጉን መላክ ጀመረ እንዴ? ልትማር ነው የመጣኸው ። ምግብ፣ አልጋ ፣ ለብቻህ ነው የሰጠንህ። ምንም የሚያዳርስህ የለም። ጠጅህን ተግተህ ስክሬ እመጣለሁ ብለህ እንዳታስብ ፣ ትጣላኛለህ። በጠፍ ጨረቃ ሰው አየኝ አላየኝ ብለህ እቃህን ጠቅልለህ ትወጣታለህ። ይህ ብቻ አይደለም ሳታጠና ብትቀርም እንዲዚሁ ነው። ሻንጣህን እንኳን ለመሰብስብ ታፍርና ሰው ሳያይህ ነው የምትጠፋው፣ ስለዚህ ብታጠና ይሻልሃል። እኛ እናንተን ልናስተምር ተዘጋጅተን ነው የምንጠብቃችሁ። ትንሽ የእርሻ እውቀት አግኝታችሁ ይህንን መከረኛ ሕዝብ ትረዱታላችሁ ተብላችሁ ነው እዚህ የመጣችሁት ። እዚህ በድጋፍ ወረቀት፣ በማስፈራራት አልፋለሁ ብለህ ቀበሌ የተማርከውን ማስፈራራት ይዘህ ከመጣህ አይሆንም ። የበረታው ነው የሚመረቀው ፣ የደከመው ዕቃውን ጠቅልሎ ይሄዳል። “

ተማሪው ጸጥ እረጭ ብሎ ነው የሚያዳምጠው። ትንሽ ዝም ብሎ ወደ ተማሪዎቹ እየተመለከተ ቆይቶ አንዱን ተማሪ፦

“አንተ እዚያ ጋ ደረትህን ገልብጠህ የተቀመጥከው አብዮት ጥበቃ ነበርክ?“
ማንን ማለቱ እንደሆነ ስላልገባን እርሱ በሚመለከትበት አካባቢ ያለን ተማሪዎች እርስ በርሳችን መተያየት ጀመርን።
“አንተ እዛ ጋ ደረትህን ገልብጠህ የተቀመጥከው።“
አንዱ ተነስቶ
“እኔን ነው?“ ብሎ ጠየቀ።
“አዎ አንተም ብትሆን።“
ተማሪው “አልነበርኩም“ ብሎ መለስ ።
“ጥሩ አንተ ካልሆንክ፣ እዚህ ውስጥ ቀበሌ ያዙኝ ልቀቁኝ የምትል አብዮት ጥበቃ ወይም የወጣቶች ሊቀመንበር የነበራችሁ አትጠፋም። እሱን እዛው ጥለኸው ና እዚህ ግቢ የወገብ ሳይሆን የእውቀት ትጥቅ ነው የሚስፈልግህ።“

የሚነገረንን ሁሉ ሰምተን በጸጥታ እንወጣለን።

በደርግ ዘመን ምንም እንኳን የሃገሪቱ ሁኔታ አሳዛኝ ደረጃ ላይ የነበረ ቢሆንም ሃገራቸው ውስጥ ተቀምጠው፣ “ከደርጉ አብዮት“ እራሳቸውን አርቀው፣ የቻሉትን ለመሥራት ጥረት ያደርጉ የነበሩ ጀግኖች ዜጎች ነበሩ። በዚህ ዘመን ምሁራን (አሁንም ጭምር) ለሃገራቸው የሚችሉትን ለማበርከት ምን ያህል ፈታኝ ችግር ይገጥማቸው እንደነበር በቃላት ለመግለጽ አስቸጋሪ ነው። ደርግ ምሁራንን ያስር፣ ይገርፍ፣ ይገድል እንደነበር መካድ አይቻልም።

ያ ጀግና ዲን ግን በተራ ካድሬዎች እየተዋከበ፣ በማያምነው ሥርዓት ውስጥ ተቀምጦ ለሃገሪቱ ልማትና እድገት ይበጃሉ የሚላቸውን የግብርና ባለሙያዎች ሲያሰለጥን ነበር። እረፍት ሳይኖረው ከአዋሳ ሳይወጣ ሙሉ ጊዜውን በግቢው ውስጥ በማሳለፍ የእርሻ ባለሙያዎች በወጉ እንዲማሩ ትልቅ ጥረት ያደርግ ነበር። ወቅቱ ለአንድ ካድሬ የማሰር፣ የመግረፍ፣ የመግደል መብት የተሰጠበት ስለነበር ዶክተሩ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በውጥረት ውስጥ ነበር የሚኖረው። ያም ሆኖ ግን ሃገር እናስተዳድራለን ከሚሉ ማይም ካድሬዎች ጋር በቆራጥነት እየተዋጋ፣ የተማሪውን መብት እያስጠበቀ፣ ሥነ ሥርዓት አስከብሮ ለዓመታት ቁጥራቸው ብዙ የሆነን የግብርና ባለሙያዎችን አስመርቋል። ዛሬ በሃገሪቱ ውስጥ በብዙ በከፍተኛ ሃላፊነት ላይ የሚገኙ መለስተኛና ፣ ከፍተኛ ባለሙያዎች የዚህ ጀግና ምሁር ውጤቶች ናቸው።

ዶክተር ገረመው በጣም የሚታወቀው አብዮቱን አለመደገፉ ነበር። ሃገሩን ይወዳል ግን ካድሬ፣ ፖለቲካ፣ ስብሰባ፣ የሚባል ነገር ያንገሸግሸዋል። ኮሌጁ ለትምህርት ብቻ እንዲውል ይታገላል። ይህ አቋሙ በክፍለ ሃገሩ ፖለቲከኞችም በጣም የሚታወቅ ነበር። በምዕራብ ጀርመን የተማረን ዶክተር የቀበሌ ተራ ፖለቲከኛ ምንም ባይገባው ለማንም አይደነቅም ወይም ኮሌጅ ለትምህርት የመጣው ተማሪ የሚናገረውን የማያውቅ የምርት ካድሬ ጭቅጭቅ ጆሮውን እንዳያደነቁረው ቢታገል አያስገርምም። ዶክተሩ ጎበዝ ተማሪ ማምረት እንጂ ራሱ እንደሚለው የቀበሌ ስንዴ የሚያከፋፍል ካድሬን ማምረትን አይሻም ነበር።

እውነት እንደሆነ ማረጋገጥ ባይቻልም አንድ የክፍለ ሃገሩ ካድሬ የመማሪያውን አዳራሽ ለቅዳሜና እሁድ ለስብሰባ ዶክተር ገረመውን ፍቃድ ይጠይቃል። ዶክተሩ እንደተለመደው አዳራሹ መማሪያ እንጂ መሰብሰቢያ አይደለም ብሎ ይከለክላል። ጮሌው ካድሬ “ከተማራችሁት ይኸ አይጠበቅም ይለዋል።“ መልስ የማያጣው ዶክተር ገረመው “ማትሪክ እንደ ከዘራ ጠሞብህ ነው እንጂ ኮሌጁን አልዘጋነውም፣ ደፍሮ ገብቶ ተምሮ ዲን መሆን ነው“ አለው ይባላል።

ይህንን ዓይነት ሁኔታ በተለይ ሥራ ከገባን በኋላ ምን ያህል የልማት ነፍሰ ገዳይ መሆኑን በተግባር ያየነው ነው። ለእርሻ የተመደበን ትራክተርን አስገድደው ወስደው የቤት እቃ የሚያመላልሱ የኢሠፓ አባላት ብዙ ነበሩ። ለግብርና የተመደበውን መኪና ወስደው ገበሬው ጋ መሄድ የሚገባው ሠራተኛ እንዲቀር የተገደደበት ብዙ አጋጣሚዎች ነበሩ። ለእርሻ የሚያገለግሉ ዶዘሮች ለእግር ኳስ ሜዳ ያስተካክሉ ተብለው በአውራጃ ኢሠፓ (በዘመኑ አነጋገር አመራር ተሰጥቶበት )ተወስደው የእርሻው ጊዜ ያለፈበትም ወቅት ነበር። እንቢ ማለት ደግሞ የሚያስከትለውን መገመት ይቻላል። የኢሠፓ አባላትን ያስቀየመ ምን እንደሚደርስበት የኢሠፓአኮ ምሥረታ አዋጅ በአጭሩ የኢሠፓ አባላትን ያስቀየመ ወይም ለማስቀየም ያሰበም እንኳን ወንጀለኛ ነው በሚል ደንግጎ ነበር።

ዶክተሩ ስለተማሪው ምግብ መኝታ ቁጥጥር ያደርጋል። አንድ ቀን ራት ሰዓት ላይ ዶክተሩ ተማሪዎች ምግብ መብያ አዳራሽ ይመጣል። አንድ ተማሪ ኮፍያ ሳያወልቅ ሲበላ ያየዋል። ተማሪውን ዶክተሩ አጠገቡ ቆሞ ይመለከተው ጀመር። ተማሪው ደነገጠ። ግን ዶክተሩ ለምን እንደሚመለከተው አላወቀም። ተማሪው ሊነሳ ሲል ዶክተሩ ቁጭ በል አለው። መፋጠጥ ሆነ። በመጨረሻም ዶክተሩ ኮፍያ አድርገህ ነው የምትበላው? ብሎ ጠየቀው። እስከ አሁን አስታውሰዋለሁ ልጁ ኮፍያውን አንስቶ መሬት ላይ በድንጋጤ ወረወረው። ዶክተሩም ስቆ ጥሎት ሄደ። ከዛም ሴቶቹ ጋ ሄዶ ከሚበሉት ምግብ አጉርሱኝ አለ። ምግቡ አልጣፈጠውም መሰለኝ የምግብ ቤት አላፊውን አቶ አሰፋ የሚባለውን አስጠራው። አሰፋ መጥቶ አጠገቡ ቆመ። ዶክተሩ የዛሬው ራት ቀይ ነው ወይ አልጫ ? ብሎ ጠየቀው። አሰፋ በምሳ ሰዓት ምግብ ስለተረፈ ቀይኑን አልጫውን . . . ብሎ ሊያስረዳ ሲጀምር አቋረጠውና ዶክተሩ ቀይ ነው ወይስ አልጫ ? ብሎ ደግሞ ጠየቀው። አሰፋ ደንግጦ የሚናገረው ጠፋው። ዶክተሩ ከዛሬ ጀምሮ ቀይና አልጫ እንዳታደባልቅ ብሎ ከለከለው። ከዚያ በኋላ ለተማሪውም የተደባለቀ ወጥ መቅረብ አቆመ።

እራሴ የነበርኩበትና የተከታተልኩትን ምንም ጊዜ የማልረሳው አንድ ጉዳይ አለ ። ከክፍለ ሃገሩ ጽሕፈት ቤት የተላከ አንድ ካድሬ የወጣት ማህበር ለማቋቋም ወደ ኮሌጁ ይመጣል። ሁላችንም እንሰባሰባለን ። ካድሬው የነቃና የተደራጀ ምሁር ለአብዮቱ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያስረዳናል። ከዛም የወጣቶች ማህበር መቋቋም አስፈላጊ ስለሆነ እንድናቋቁም ያሳስበናል። ችግሩ የዶክተሩንና የብዙሃኑን መምህራን አቋም ስለምናውቅ ማን ይመረጥ? አብዮቱ በጣም በማይደገፍበት የኮሌጅ ግቢ ማነው የወጣት ማህበር የሚመረጠው? ማነው ሊቀመንበር ሆኖ የሚመረጠውስ? ማነውስ የሚጠቁመውስ? ሂደቱ ብዙ ጊዜ ወሰደ። ካድሬውም ተናደደ። ምሳ ሰዓት አለፈ። ከምሳ በኋላ ምርጫ እናደርጋል አለና ምሳ ተበላ። ከምሳ በኋላም ጸጥታ ሰፈነ። ተማሪውም አልመርጥም አለ። ከብዙ ዝምታ በኋላ ዶክተሩ ተጠራ።

በዚያ በሚያስፈራ ድምጹ “ለምንድነው የተፈለግሁት ?“ ብሎ ጠየቀ።
“ተማሪዎቹ አንመርጥም ብለዋል“ ካድሬው መለሰ ።
“ካልመረጡ ታዲያ ምን ላድርግ?“ ዶክተሩ ካድሬውን ጠየቀው።
ካድሬው በንዴት “የኢትዮጵያ አብዮት እንኳን አዋሳ ኮሌጅ ሱማሌ ገብቷል። እዚህ ግቢ የተጠቀጠቁትን ጸረ አብዮተኞችን ማጽዳት አያቅተንም።“ ሲል አምርሮ ተናገረ።

ለመጀመሪያ ጊዜ ዶክተሩ ዓይን ላይ ሊደርስ የሚችለው ችግር ታየ ። ከዛም በሚያሳዝን ድምጽ ፡ –

“ባለፉት ዓመታት ብዙ ችግር ሁላችንም አይተናል። ይህ እዚህ የምታዩት ሰውዬ ደግሞ የሚዝተው ያየነውን ሁሉ አሰቃቂ ተግባር እዚህ ለመድገም ነው። እኔ በበኩሌ ይህንን ዳግም ለመመልከት አልፈልግም። ምን አለ የምትችሉ ከሆናችሁ መርጣችሁ ብንገላገል። ለማንኛውም ሃላፊነቱን ለአንተ(ለካድሬው) ሰጥቻለሁ“ ብሎት ጥሎት ሄደ ።

ተማሪዎቹ ግን ይህ ችግር ከእሱም በላይ እንደ ሆነ ተረዳን። በአንድ ሰዓት ውስጥ ጠቁመን መርጠን ጨረስንና ከዛ አስቃቂ አደጋ ተገላገልን። ነገር ግን የተመረጠው ኮሚቴ ምንም የረባ ጉዳይ ሳይፈጽም ተመረቅን ። አዎ “የደርጉ አብዮት“ በግድያ አዋሳ ኮሌጅ ቀርቶ ብዙ ቦታ መድረስ ችሏል። ይህ ሂደት ብዙዎቹን ሃገራቸውን የሚወዱ አስተማሪዎችን ከሃገር አባርሯል ወይም ገሏል።

ዶክተር ገረመው በዚህ ስቃይ ውስጥ ኖሮ ቁጥራቸው ብዙ የሆኑ የእርሻ ባለሙያዎችንን ለሃገሪቷ ስላፈራ ሊመሰገን ይገባዋል። ከእርሱ ጎን የቆሙ አስተማሪዎችም ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። በየቦታው ብዙ ያልተነገረላቸው የውጭ ሃገር የተንደላቀቀ ኑሮን ትተው ለሃገራቸው ብዙ የሠሩ ምንም ሳይነገርላቸው ታሪካቸው ተቀብሮ ቀርቷል። ምንአልባትም ዛሬ ያንን የቀውጢ ቀን ሸሽቶ የበረረ ፣ ለሃገሩ ምንም አስተዋፅዖ ያላበረከት እንደ ጀግና ሲመሰገን ለሃገሩ የሞተ ሊወቀስ ይችላል። ለማጠቃለል ያህል ከሁሉ በላይ የማስታውስው የመጨረሻ በምረቃችን ቀን ዶክተሩ የተናገረውን በማስታወስ ነው። ብዙ ይናገራል ተብሎ ሲጠበቅ፡-

“እዚህ ኮሌጅ ሁለት ዓመት ቆይታችኋል። ትንሽ በጣም ትንሽ እውቀት ገብይታችኋል። ታዲያ እቺን እውቅት ይዘህ ገበሬውን ከመርዳት ተቆጥበህ ገበሬውን አዛዥህ ነኝ ካልከው፣ አትረባም ማለት ነው። ገበሬው ከአንተ በላይ ብዙ ያውቃል። ከገበሬው እየተማርክ ስለ እርሻ ካስተማርከው ደግሞ ትንሽ ለሃገርህም፣ ለገበሬውም ትንሽ ጥቅም ትሰጣለህ ። አይ ብለህ ግን ካድሬ ልሁን ካልክ እዚህ እኛም ጋር መምጣት አያስፈልግህም ነበር። ጨርሻለሁ።“

ብዙ ይናገራል የተባለው ዶክተር በሁለት ደቂቃ ጨረሰ።

ብዙዎቻችን ወደ ሥራ ስንሰማራ የዶክተር ገረመው የአደራ ቃል ጭንቅላታችን ውስጥ ያቃጭል ነበር። በተለይ በደርግ አገዛዝ ጊዜ በነበረው ድርቅ ወቅት በሠፈራና ስግሰጋ ውስጥ እንሰራ የነበርነው የእርሻ ባለሙያዎች ችግሩን ተጋፍጠናል። የሰው ሕይወት እየረገፈ ባለበት ወቅት የኢሠፓ አባላት አመራር ምን ያህል ችግር ይፈጥሩ እንደነበር ገና ያልተጻፈ ጉድ ነው። ሰው መኖር በማይችልበት አካባቢ መስፈር አለባቸው ተብሎ የተወሰዱ የሰሜን ሰዎች በበሽታ ሲያልቁ አይተናል። እንደ ዶክተር ጠንካራ ያልሆኑ ዶክተሮች የተሳሳተውን የኢሠፓ አመራር ሲያደንቁም ተሰምተዋል። የሚያሳዝን ብዙ ታሪክ ተፈጽሟል።

ዶክተር ገረመውን እየፈራነው ወደድነው፣ እየወደድነው አከበርነው፣ እያከበርነው ቃሉን ለመፈጸም ሞከርን፣ የተሳካልንም ያልተሳካልንም ነበርን። ሌሎች ብዙ ስለ ዶክተር ገረመው ብዙ ያልተነገሩ ስላሉ ወደ ፊት ሌሎች ጸሐፊዎች በተለይ የእርሻ ሳይንስን በሚመለከት በሰፊው ይጽፋሉ የሚል እምነት አለኝ።

27.01.15

ስለ ሃገራችን ደህንነት የሚያስቡ ሁሉ በሰላም ይክረሙ!

[email protected]