የህዝበ ሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች የኦዲዮና ቪዲዮ ምስክር የማቅረብ ሂደት ‹‹መብራት የለም›› በሚል ሳይካሄድ ቀረ!!! – ድምፃችን ይሰማ!

የውድ ኮሚቴዎቻችን የኦዲዮና ቪዲዮ ምስክር የማቅረብ ሂደት ‹‹መብራት የለም›› በሚል ሳይካሄድ ቀረ!!!
በአርብ ጥር 15ቱ ችሎት የየካቲት 26ቱ ውይይት የድምጽ መረጃ መቅረቡ ይታወሳል!

ማክሰኞ ጥር 19/2007

1513760_898357176882306_1142078233042720208_nየውድ ኮሚቴዎቻችን የኦዲዮ ቪዲዮ መረጃ የማቅረብ ሂደት በዛሬው እለት ሳይካሄድ ቀረ!!! ችሎቱ ላለመካሄዱ የተሰጠው ምክንያት ‹‹መብራት ጠፋ›› የሚል ሲሆን ይህም የመሪዎቻችንን ችሎት ለዓመታት ለማጓተት እስካሁን ጥቅም ላይ ሲውል የቆየ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ለዛሬ የተቀጠረው አርብ ጥር 19 በዋለው ችሎት የነበረ ሲሆን በወቅቱም የህዝበ ሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች በየካቲት 26/2004 ከፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ጋር ያደረጉት ውይይት የድምጽ ቅጂ ሁለተኛ ክፍል የቀረበ መሆኑ ይታወሳል፡፡ በተደመጠው ማስረጃም ፕሮፌሰር አደም ካሚል፣ ሸኽ ዩሱፍ፣ ኡስታዝ ያሲን ኑሩ፣ ኡስታዝ አቡበክር አህመድ፣ ኡስታዝ አህመዲን ጀበል፣ እንዲሁም ሸኽ ሱልጣን ንግግር ሲያደርጉ የተደመጠ ሲሆን ከፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ደግሞ ዶክተር ሽፈራው ተ/ማሪያም የማጠቃለያ ንግግር ሲያደርጉ ተደምጠዋል።

በቀረበው ማስረጃ ከላይ የተጠቀሱት የኮሚቴ አባላት ንግግሮች ቀርበዋል፡፡ ፕሮፌሰር አደም ካሚል ‹‹መጅሊስ አይወክለንም፤ ምርጫ ተደርጎ ህጋዊ መጅሊስ ይቋቋምልን፤ አወሊያ በቦርድ ይተዳደርልን፤ የአህባሽ አስተምሮ በግድ አይጫንብን›› በማለት ሰፊ ትንተና ሰጥተዋል፡፡ ሸኽ ዩሱፍ በበኩላቸው ‹‹መጅሊስ የእኛ ሀብት ነው፤ በህገ ወጥ መልኩ የተቀመጡ አመራሮች ከቦታው ሊነሱ ይገባል፤ አህባሽ በግድ ሊጫንብንም አይገባም›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ዳዒ ኡስታዝ ያሲን ኑሩ ደግሞ ‹‹አህባሽን አስመልክቶ ምንም አይነት ስልጠና እንዳልተሰጠ ቢገለፅልንም በስልጠናው ውስጥ የተሳተፉ አባላት መረጃዎች አሉን›› ያለ ሲሆን በስልጠናው ላይ የመሳጂድ ኢማሞችና ሙአዚኖች እንደ ሃዲስ ‹‹ሸሃዳ›› (የእምነት ምስክርነት) እየሰጡ እንደነበር፣ ይህንንም አልቀበል ያሉ ከኢማምነታቸውና ከስራ ገበታቸው እየተባረሩ እንደነበር አብራርቷል፡፡ የኮሚቴው ሰብሳቢ ኡስታዝ አቡበክር አህመድ በበኩሉ ህዝበ ሙስሊሙ የጠየቃቸውን ሶስቱን መሰረታዊ ጥያቄዎች በማስመልከት ትንታኔ ሲሰጥ የተደመጠ ሲሆን የ1992ቱን የመጅሊስ ምርጫና አህባሽን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡
የታሪክ ምሁሩ ኡስታዝ አህመዲን ጀበልም ስለ1992ቱ ምርጫ ማብራሪያ ሲሰጥ ተደምጧል፡፡ በአህባሽ ስልጠና ወቅትም በጅማ ወረዳ ‹‹የአህባሽን ስልጠና ልትዘግብ ነው የመጣኸው›› ተብሎ በ24 ሰዓት ከከተማው እንዲወጣ እንደተደረገም ገልጿል። በሌላ በኩል ሸኽ ሱልጣን በ1992 የነበረውን የመጅሊስ ምርጫ አንስተው በወቅቱ 44 ያህል ሰዎች ከተመረጡ በኋላ የተመረጡት ተሽረው የማይታወቁ ህገ ወጥ አካላት ቦታውን እንደትቆጣጠሩት ሲገልፁም በድምፅ በቀረበው ማስረጃ ላይ ንግግራቸው ተደምጧል።
በዚሁ ማረጃ ከፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶክተር ሽፈራው ተ/ማሪያም የማጠቃለያ ንግግር ሲያደርጉ የተሰማ ሲሆን ‹‹እናንተ ስለማታውቁ ነው እንጂ በአረብኛ ትምህርት ሽፋን አወሊያ የአክራሪና የአሸባሪዎች መፈንጫ ሆኖ ቆይቷል›› የሚል ውንጀላ ሲሰነዝሩም ተደምጠዋል፡፡
ዛሬ ችሎቱ ‹‹በመብራት መጥፋት›› ሳይካሄድ ቢቀርም በቦታው ግን የኮሚቴው አባላትና ሌሎችም ተከሳሾች ከጠበቆቻቸው ጋር በሰዓቱ መገኘታቸው ታውቋል!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምፃችን ይሰማ!

The post የህዝበ ሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች የኦዲዮና ቪዲዮ ምስክር የማቅረብ ሂደት ‹‹መብራት የለም›› በሚል ሳይካሄድ ቀረ!!! – ድምፃችን ይሰማ! appeared first on ሳተናው (Satenaw) – Latest & Current Ethiopian News, Breaking News,.