አንተ ድሃ ዝም በል (ሄኖክ የሺጥላ)
( በሄኖክ የሺጥላ )
ጸጥ በል
ለጥ በል
ዝም በል አንተ ድሃ
ባላቤት የሌለህ የሰው ወራጅ ውሃ !
አትናገር ባፍህ
በጅህ አትመገብ
ልመና ነው ግብርህ ስራህ ነው መስገብገብ ።
አንተ ድሃ ዝም በል
ቢርብህ ራበኝ ጠማኝ እንዳይወጣህ
ይህን ለመናገር ማን ነጻ አወጣህ !
ደሞ ነጻ ልውጣ
አንድ ቀን ንጹ ውሃ ሞልቶልህ ሳትጠጣ ?
ትግሉን ልመናውን አመጹን ባንተ ስም
ሁልም የቀና ቀን ፣ አንተ ዝም በለን ዝም !
ስምህን ለትግል
መከራክን ለድል
ሁልም የሞላ ቀን እያረዱ ገደል !
አንተ ድሃ ዝም በል
ድሃ ነኝ አትበል
ድህነት ውርስህ ነው እንኩዋንስ በትግል አይለቅም በጸበል !
ለኔ አንተ ከሌለህ በማን ስም ልነግድ
ነጻ ልሁን አትበል ሂድ ከብትህን አግድ !
ወግድ !
አንተ ድሃ ዝም በል
መሬተ ተቀማ ፣ ከብቴ ተዘረፈ
አትበለ አትለፍፍ ፣ ሰብሌ ረገፈ
ያንተ ከብት የኔ ነው
ባለቤት የሌለው
ያንተ ቤት የኔ ነው
አባወራ የሌለው
አንተም የኔ እኮ ነህ
ስንዴ መለመኛ
መቀፈያ ፎቶ የዶላር መገኛ ።
ታዲያ የምን ሀብት ምኞት
የምን ቀና ቀና
አንተን ድሃ ማድረግ አልበቃኝም ገና !