ትንሿ ጋዜጠኛ
እስከዳር አለሙ
ልጅ ሆነን ማታ ማታ በቤታችን ዉስጥ ሁሌም የማይቀር አንድ ፕሮግራም ነበር ሁሉም ቤተሰብ በግድም ቢሆን ሳያየዉ የማይተኛዉ። ምን መሰላችሁ? የርዕዮት አለሙ የዜና ፕሮግራም። ልክ ሲመሽ ርዕዮት አንዲት ሁሌም ዜና ብላ ያሰበችዉን የምትፅፍባትን ደብተሯን ይዛ ጉሮሮዋን እያጠራረገች ከጓዳ ብቅ ትላለች። ያን ጊዜ ሁላችንም የዜና ሰዐት መድረሱን ተገንዝበን ለመስማት ዝም እንላለን፡፡ ርዕዮት ድምጽ ማጉያ ለማስመሰል ባትሪ ትይዛለች (በኋላ ላይ ባትሪዎቹን ሰብራ ስለጨረሰቻቸዉ ወደ እንጨት መያዝ ተሸጋግራ ነበር።) ከዛም አቤት ዉስጥ ሲፈፀም የዋለዉን ሁሉ አንድ በአንድ በዜና መልክ ማቅረብ ትጀምራለች።
ከዜናዎቹ ጥቂቱን ልንገራቸችሁ
– በዛሬዉ እለት ሁለት የወ/ሮ አሰለፈች ጓደኞች መጥተዉ ስጫወቱ ዉለዉ ሄዱ፡፡ ለዝርዝሩ ትልና የራሷን ስም ትጠራና ራሷ ዝርዝሩን ታቀርባለች። (ያወሩት አይቀራት የበሉት ብቻ ያየችዉን የሰማቸችዉን ዜናዉ ላይ ታሰማናለች።)
– እስከዳር አለሙ ዛሬ ስታለቅስ አመሸች፡፡ ይህ የሆነዉም ከትምህርት ቤት ስትመጣ የታላቅ እህቷን እጅ ያዢ ተብላ እምቢ ብላ ስትሮጥ ወድቃ እግሯ ላይ ስለተላጠች ነዉ። (የዚህ ጊዜ እኔ ሉሉን ማኩረፍ ስጀምር አባቴ አየት አርጎኝ ይስቃል። ኮስታራዋ እናታችን ቆይ ሁለተኛ የእህትሽን እጅ ትለቂና ትለኛለች። ያኔ አቤት! ዜናዉን ስጠላዉ።)
– አቶ አለሙ ዛሬ ትላንት ከመጡበት ሰአት ቆይተዉ መጡ፡፡ ምክንያቱም ደግሞ ስራ ስለበዛባቸዉ ነዉ፡፡
– በመጨረሻም (የልጅነተ ድምጿን ለማጎርነን እየሞከረች) ወ/ሮ አሰለፈች ዛሬ እራት ሊሰሩ ኩሺና ሲገቡ እሳት አቃጠላቸቸዉ፡፡ (አንቺ! አሁን ይሄ ይወራል የእቴቴ ንግግር ነበር ጋሼ በሳቁ አቋረጣት እንጂ።)
እስኪ ከልጅነት ትዝታችን ላካፍላችሁ ብዬ ነዉ፤ የርዕዮት የጋዜጠኝነት ሙያ ፍቅር እንግዲህ እያለ ነበር የጀመረዉ፡፡