ጣይቱ ( ከሄኖክ የሺጥላ ) ክፍል አንድ
(ከሄኖክ የሺጥላ)
ጸሐይቱ
የድል ብርሃኒቱ
የነጻነት ቀንዲሊቱ
እምቢታሽ ያስጨነቃቸው
ድልሽ የረበሻቸው
ባንዳነት የወለዳቸው
ባንዳነት ያሳደጋቸው
ባንዳነት የሰየማቸው
ይኸው ምን ቀራቸው ?
እንደ እባብ እየተሳቡ
ጠግበውም ስለ ተራቡ
የማጀትሽ እንጀራ ሞሰብሽ ባይመልሳቸው
እልፍኝሽን አቃጠሉት ያው በለመደ እጃቸው !
ጣይቱ
አንቺ እናቲቱ
የአፍሪካ እልፍኝቱ
ጣይቱ የትናንትናዋ
የክንደ ብርቱ ማዳሪያ የጀግናዎች መጠጊያዋ
ይኸው በዘመን መተት
ዛሬም በጊዜ ንፍገት
ዛሬም በታሪክ ዝቅጠት
እልፍኝሽ ላይ የባንዳ መርዝ ፣ የቂም እሳት ወረደበት !
አንቺ የእምሩ ጉልበት
አንቺ የአበበ አረጋይ ፣ የራስ ሙልጌታ ሹመት
አንቺ የአንባላጌ ፣ የአድዋ ድል ቁመት
ዛሬ ገበየሁ የለም፣ ያ የጦሩ ባፈና
እሳትሽን እንዲውጠው ይስማ ነገሩን ጎበና ?
ለብዲሳጋ እንንገረው ፣ የ እልፍኝሽን መንደድ
ዛሬም እንደ ትናንቱ በጎራዴው ላንቺ እንዲፈረድ ።
ሃይለማርያም ማሞ ይምጣ ከመንዝ አፈሩን አራግፎ
እሳትሽን እንዲያወጣ በሳት እጁ እሳት አቅፎ ?
ጣይቱ የስምሽ በረከት ፣ የስያሜሽ አፈ ጽጌ
ምሕዋሩ ተገርስሶ ፣ ቁመቱ አመድ ሆነና ዛሬ አደረ ከግርጌ !
አንቺ የ ደርመሙሳ የሸኖ አምባ ጀግና
የዳስሽ እሳት ሰማዩን አረገው ጥቁር ደመና ።
ይኸው ቤትሽ ፈረሰ
መሰረቱ በወላፈን ቁ’ዋሚው ተደረመሰ
ጴጥሮስን ትናንትና በመንገድ ስም ፈነቀሉት
ወመዘክርን በኪሎ እየሰፈሩ ሸጡት
ደሞ ዛሬ በትሽን እንደ ደመራ ከበው ፣ እንደ ችቦ አቃጠሉት
ገና በርሃ እያሉ ነው ጣይቱ ስምሽን የጠሉት !
ለነገሩ የቤትሽ የማጀትሽ ባለቤቶች
እነሱ ሆነውማ አይደል የዘንድሮ ባለ ‘ርስቶች
ገዝተው ያስተዳደሩሽ
እንዳቀዱት እንዳለሙት ደሞ ዛሬ አቃጠሉሽ !
ምን ይሰራል ታዲያ ቤቱ ባንዳ እየቀለበ
ምን ይሰራል ያንቺ ጉዋዳ ፣ ያንቺን ቀሚስ እየሳበ
ምን ይሰራል ጣይቱ ሆቴል ፣ ባንዳ ተሰይሞበት
ምን ይሰራል ቤተ ጊዮርጊስ ፣ ፓስታ እየተሳበበት !
ምን ይሰራል የጨዋ ቤት ፣ ባለጌ እያዘዘበት
ምን ይሰራል ያንቺ ማጀት ፣ ከንፈር እየተሳመበት !
ጣይቱ
ብርሃኒቱ
አንቺ ጸሐይቱ
መቀነትሽ ተፈታ
ህዝብሽ ስሙን ረስቶ ፣ ለሆዳም ባንዳ ተራታ !
ጣይቱ
ብርሃኒቱ
አንቺ የአድዋ ጽላት ፣ የነጻነት ቤተ መቅደስ
ወጣት ነበርኩ ስትቃጠይ ፣ መጠሪያሽ በእሳት ሲፈርስ !
ወጣት ነበርኩ ጉልበት ያለኝ
ልጠቀመው ያላደለኝ !
ፈሪ ሆኘ ራሴን አጣሁ
ፈሪ ሆኘ ካገር ወጣሁ
ይኸው ዛሬም ፈሪ ሆኘ ስትቃጠይ
በሰቀቀን ራሴን ቀጣሁ !
ጣይቱ ልጆችሽ አልተወለዱም
እሳትሽን የሚያጠፉት
አሁን ያሉት የሚዘርፉሽ አፈርሽን የሚገፉት
እነሱ ናቸው ጣይቱ አመድሽን ያረቀቁት
በአደባባይ ስትቃጠይ ፣ በንዳድሽም የሳቁት !
ጣይቱ
ብርሃኒቱ
አንቺ ጸሐይቱ
መቀነትሽ ተፈታ
ህዝብሽ ስሙን ረስቶ ፣ ለሆዳም ባንዳ ተራታ !