የመርጋና የትግስቱ ታንጎ ዳንስ (አንድነትን በተመለከተ)

ናኦሚን በጋሻው

ጥያቄዉ አሁን ምርጫዉን ቦይኮት የማድረግ እና ያለማድረግ አይደለም። የአንድነት ፓርቲ ምርጫዉን እንደሚወዳደር ይፋ በማድረግ እንቅስቃሴ ላይ ነበር። ብዙዎች “አንድነት እንዴት ምርጫዉን እወዳደራለሁ ይላል” የሚል ትችት አቅርበው ነበር። የአንድነት አመራሮች ግን፣ አንድነት በምርጫዉ የሚሳተፈው በምርጫ ቦርድ ተማምኖ ሳይሆን በሕዝቡ ተማምኖ እንደሆነ በመገልጽ፣ አንድነት ከምርጫው ቢወጣ ደስ የሚሰኘዉና የሚጠቀመው ገዢው ፓርቲ ብቻ እንደሆነ በመግለጽ ገለጹ። በአንድነት እና በተወሰኑ የተቃዋሚ ወገኖች መካከል ክርክሮች ተነሱ።

ሕወሃት ክርክሮቹን በጥሞና ተከታተለ። እንደዉም ሰላዮቹን በመላክ ማሟሟቅ ጀመረ። አንድነት ከምርጫዉ እንዲወጣ በተቃዋሚዎች የሚደረገዉ ግፊት አይሎ ከምርጫዉ እንዲወጣ ኔብር ጉጉቱና ምኞቱ።
ነገር ግን ሕወሃት እንደጠበቀው አልሆነም። የአንድነት አመራሮች በተለያዩ ሜዲያዎች በስፋት በከፈቱት ህዝቡን የማስተማር ዘመቻ፣ የወሰዱት አቋም ተቀባይነት እያገኝ መጣ። የምርጫ ዘመቻዉም ተጧጧፈ። ከሰላሳ አራት በላይ ጽ/ቤቶች በአገሪቷ ባሉ ዞኖች ተከፈቱ። ከ480 በላይ ባሉ ወረዳዎች ለፓርላማና ለክልል ተወዳዳሪዎች ተዘጋጁ። እነ ብአዴን ደነገጡ። ሽንፈትን ማሽተት ጀመሩ። ሕውሃትን ተማጸኑ። የሕውሃት ባለስልጣናት፣ አሽከሮቻቸው ከሌሉ የነርሱም መጨረሻ እንደሆነ ተረዱ። የምርጫ ቦርድ ም/ሃላፊ በሆኑትና በሕወሃቱ በዶር አዲሱ ገብረ እግዚአብሄር በኩል፣ “አንድነት በዚህ ምርጫ መወዳደር የለበትም” የሚል ትእዛዝ አስተላለፉ። የምርጫ ቦርድ ሃላፊው፣ የከብት ሃኪሙ ፕሮፌሰር መርጋ፣ ከምክትላቸው የተሰጣቸውን ትእዛዝ ተቀብለው አቶ ትእግስቱ አወል ከሚባሉ ሰው ታንጎ ዳንስ ጀመሩ። ተለጣፊ የአንድነት ፓርቲን ለመመስረት ተንቀሳቀሱ። ለሕጋዊው የአንድነት ፓርቲ አመራር ከሕግና ከአሰራሩ ዉጭ እውቅና አንሰጥም አሉ።

Tigistu Awol
[አቶ ትእግስቱ አወል]

ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ከሃላፊነታቸው በፍቃዳቸው እንደለቀቁ፣ ጥቅምት 3 ቀን የአንድነት ብሄራዊ ምክር ቤት እርሳቸዉን የሚተካ ፕሬዘዳንት መርጦ ነበር። በወቅቱ ሶስት እጩዎች ነበር የቀረቡት። እነርሱም አቶ ትእግስቱ አወል፣ አቶ ደረጄ እና አቶ በላይ ፍቃዱ። ከ49 የምክር ቤት አባላት 38 በስብሰባው ተገኝተው ነበር። አቶ በላይ 26 ድምጽ፣ አቶ ደረጄ 11 ድምጽ ሲያገኙ፣ አቶ ትእግስቱ አወል ደግም አንድ ደምጽ ብቻ ነበር ያገኙት፤ እርሱም የራሳቸው ድምጽ። ከምክር ቤት አባላት፣ ማንም ለአቶ ትእግስቱ አወል ድምጹን አልሰጠም ማለት ነው። በዚህ ምክንያት ስልጣን እንደ ዉህ የሚጠማቸው አቶ ትእግስቱ አኮረፉ። ማኩረፋቸውን የተገነዘበው ምርጫ ቦርድ ወደ 2 ሚሊዮን ብር ባጀት መድቦ፣ ዱርዬዎችን ሰብሰቦ ከርሳቸው ጋር መስራት ጀመረ።

ሐሙስ ታህሳስ 30 2007 ዓ.ም የአንድነት ፓርቲ ከምርጫ ቦርድ ደብዳቤ ደረሰው። ከጥር 4 ቀን በፊት ጠቅላላ ጉባኤ ጠርቶ አመራሩን ካልመረጠ እርምጃ እንደሚወሰድበት የሚገልጽ ደብዳቤ ነበር። ሐሳባቸው የነበረው በአራት ቀናት ዉስጥ አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ መጥራት ስለማይችል ከጨዋታ ዉጭ እናደርገዋልን የሚል ነበር። ነገር ግን በዚያኑ ቀን ብሄራዊ ምክር ቤቱ ተሰብስቦ ለእሁድ ጥር 3 ቀን ጠቅላላ ጉባኤ ጠራ። ከየከፍለ ሃገራቱ የአንድነት ተወካዮች በአንድ ፊሽካ ጥሪ በሁለት ቀናት ዉስጥ በወኔና በቁጭት እየተመሙ መጡ። አርብ ጥር 3 ቀን በሚደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ፣ በሕጉ መሰረት ምርጫ ቦርድ ታዛቢ እንዲልክ የሚጠይቅ ደብዳቤ የአንድነት ፓርቲ አስገባ። ምርጫ ቦርድ ተደናገጠ። ፕሮፌሰር መርጋ እነ አቶ ትእግስቱ ጋር ደወሉ ። “ቶሎ ቶሎ ብላችሁ አንድ ነገር አድርጉ” አሏቸው። እነ ትግስቱ፣ እነርሱም “አንድነት ነን” ብለው ጠቅላላ ጉባኤ እንደጠሩ የሚገልጽ ደብዳቤ አስገቡ። ምርጫ ቦርድ በሁለት ስብሰባ መገኘት ስለማይችል አንድነት በጠራው ስብሰባ ላይ ታዛቢ እንደማይልክ በደብዳቤ ገለጸ። አስቂኝ የታንጎ ዳንስ በአቶ ትግስቱና በፕሮፌሰር መርጋ !!!

ሆቴል ቤቶች ለአንድነት አዳራሾችን አንፈቅድም በማለታቸው አንድነት ጠቅላላ ጉባኤዉን ያደረገው በጽ/ቤቱ በድንኳን ዉስጥ ነበር። በስብሰባዉ አቶ በላይ ፍቃዱ 189 ድምጽ በማግኘት ድርጅቱን እንዲመሩ በድጋሚ በጠቅላላ ጉባኤ ይመረጣሉ። የወያኔ ተለጣፊ የሆነው፣ የአቶ ትግስቱ ቡድን በዲ አፍሪክ ሆቴል ቤት አዳራሽ ወደ አርባ የሚሆኑ የወያኔ ካድሬዎችን አሰባስቦ (የለቀቁት ፎቶ እንደሚያሳየው) ጠቅላላ ጉባዬ አድርገን፣ ከዚህ በፊት ከምክር ቤት አባላት ዜሮ ድምጽ ያገኘውን ትግስቱ አወል በ190 ድምጽ አንድነትን እንዲመራ መርጠናል ብለው አወጁ።ፕሮፌሰር መርጋ፣ “አንድነት ፓርቲ ሕጋዊ አይደለም” በሚል የአንድነት ፓርቲን ስም ለትግስቱ ቡድን በሚጠቅሉት ጥቂት ቀናት ዉስጥ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ያ ብቻ አይደለም። ጉዳዩ ከስም ስላልሆነ፣ የአንድነት ፓርቲን ስም ለሌላ ቢሰጥም፣ የአንድነት አባላትና ደጋፊዎች መዋቅራቸዉን እና መረባቸውን ይዘው እንዳለ መኢአድን ተቀላቅለው ትግሉን መግፋት ይችላሉ። አንድነትን አንድነት ያሰኘው የምርጫ ቦርድ እወቅና ወይም ሰርተፊኬት ሳይሆን ህዝብ በመሆኑ። ነገር ግን ምርጫ ቦርድ መኢአድንም ለማገድ ተዘጋጅቷል። መኢአድ እና አንድነት ሲታገዱ፣ የሁለቱም ድርጅቶች አባላትና ደጋፊዎች ወደ ሰማያዊ ፓርቲ እንዳለ መግባታቸው በቀጣይነት የሚታሰብ ነው የሚሆነው። ይህንን የተረዳው ምርጫ ቦርድ ደግሞ በሰማያዊ ፓርቲ ላይ ”ይቅርታ ጠይቁኝ” የሚል ተልካሻ ደብዳቤ ጽፎ ሰማያዊን ለማገድም እየጠነሰሰ ነው።

ሰማያዊ፣ አንድነት፣ መኢአድ ከታገዱ የአንድነት ኃይሎች ተደራጅተው ለምርጫው የሚንቀሳቀሱበት ህጋዊ ድርጅት አይኖራቸውም ማለት ነው። ወያኔ ከሌሎች ትርኪምርኪና ምናምንቴ ድርጅቶች ጋር በመሆን ፣ ምርጫ አደረኩኝ ብሎ ለማወጅ እየተንደረደረ ነው ማለት ነው።

ነገር ግን የጊዜዉን ሁኔታና ፣ የመዉደቂያቸውን ጊዜ በእጅጉ ያፋጠኑት እንደሆነ የተረዱት አልመሰለኝም። ሃብታሙ አያሌው እንዳለው “ ደርግም ወድቋል፣ ወያኔም ይወድቃል”። የወያኔ አወዳደቅ ደግሞ እጅግ በጣም የከፋ ነው የሚሆነው።