ተዉኝ
ተዉኝ አትቀስቅሱኝ አታንቁኝ ከእንቅልፌ፥
የናንተን ካልነካሁ መስመር ተላልፌ፥
እንዳሻኝ ልጋደም ላስቲኬን ለብሼ፥
በቃሽኝ ካላለች ምስኪኗ ፍራሼ።
እኮ ተዉኝ በቃ ከቶ አታስጨንቁኝ።
ለምን አትነሺም ብላቹ አጠይቁኝ።
ምን ላደርግ ልነሳ ከሰመመን ልንቃ?
ሀሰት ስልጣን ስትይዝ እውነት ተደብቃ፥
የቃየልን ዙፋን የአቤልን ሰቆቃ፥
የጥጋብ ዳንኪራ የምስኪኑን ሲቃ፥
አፈ ሙዝ ሲያሳዩኝ ፈርቶ ቢዋሽ አፌ፥
ሀቄን የእውነት ቃሌን በልቤ ታቅፌ፥
ደሀ ደም ሲያነባ ሀብታም እያገሳ፥
ይህን ልታሳዩኝ?ይህን ልታሰሙኝ ከእንቅልፌ ልነሳ?
ተዉኝ እባካቹ ወዳጅ ዘመዶቼ፥
ካሻኝ ልዋል ልደር እንቅልፌን ተኝቼ፥
አንድ ቀን መከራን ስቃይን ረስቼ፥
ምናልባት ምናልባት
ነፍሴ ከተፅናናች እድሉን አግኝቼ፥
እኔም እንደ ያእቆብ መልካም ህልም አይቼ፥
በውኔ ካልደላኝ እስኪ ልሙትበት በቅዠት ረክቼ፥
ተነሺ አትበሉኝ ተዉኝ ወዳጆቼ።
ሰላም ንጉሱ(ኪዩ)