የሠላማዊ ትግል ፈተና (መርስኤ ኪዳን)

መርስኤ ኪዳን

ግንቦት 15 ቀን 2002 ዓ.ም. የተካሄደው ምርጫ ማንም ባልገመተው መልኩ በኢህአዲግ ሙሉ በሙሉ አሸናፊነት ተጠናቅቋል። ይህ ውጤት ለተለያዩ አካሎች የተለያየ ትርጉም ይኖረዋል። በውጭ ሀገር ሆነው ”ሠላማዊ ትግል ዋጋ የለውም፤ ኢህአዲግን በተገኘው መንገድ ሁሉ በማጥቃት መደምሰስ ያስፈልጋል” ለሚሉ ለዚህ አቋማቸው ማረጋገጫ እንደሆነ አድርገው ይወስዱታል። በሀገር ውስጥ በሠላማዊ መንገድ ዓላማቸውን ለማሳካት ሲጥሩ ለቆዩት ደግሞ በሠላማዊ ትግልና በአመፅ መካከል አንዱን እንዲመርጡ የሚያስገድድ ሁኔታ ፈጥሯል። የዚህ ጽሑፌ ትኩረት የሚሆነው እነዚህ በሠላማዊ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ፓርቲዎች የገጠማቸውን ፈተና ለመዳሰስና በበኩሌ ያዋጣል የሚለውን ለመጠቆም ነው። ወደዋናው ጉዳይ ከማምራቴ በፊት ግን፤ ይህ ያልተጠበቀ ውጤት እንዴት ተከሰተ የሚለውን ለማየት እሞክራለሁ።