አቡነ ማትያስ ግብጽን ይጎበኛሉ
ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በግብጽ የአምስት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ነገ፣ ጥር ፩ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ማምሻውን ወደዚያው እንደሚያመሩ ተገለጸ፡፡
የመንበረ ተክለ ሃይማኖት ስድስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ግብጽን የሚጎበኙት፣ ከመንበረ ማርቆስ ፻፲፰ኛ ፖፕ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎድሮስ ካልዕ በተደጋጋሚ ሲቀርብ በነበረ ግብዣ እንደኾነ ተገልጧል፡፡
ፓትርያርኩ ከጥር ፪ – ፮ ቀን በግብጽ በሚኖራቸው ቆይታ፣ የኹለቱ አኃት አብያተ ክርስቲያን በሃይማኖት አንድነት የመደጋገፍና የቆየውን ግንኙነት አጠናክሮ የመቀጠል ወቅታዊ ጉዳይ ላይ እንደሚነጋገሩ ቀደም ብለው የጠቆሙ ቢኾንም የታላቁ የሕዳሴ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብን በተመለከተ ከየአገሮቻቸው መንግሥታት አቋም አኳያ የሚኖራቸው ሚና የውይይታቸው ቀዳሚ አጀንዳ እንደሚኾን ተመልክቷል፡፡
ከሢመተ ፕትርክናቸው አስቀድሞ የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ፓትርያርኩ፣ ስለ ዴር ሡልጣን የታሪክና የቅድስና ይዞታችን ከኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋራ የገባንበትን ውዝግብ ለመፍታት በዘመነ ፕትርክናቸው ስለሚኖረው አማራጭ መፍትሔ በሚያዝያ ወር ፳፻፭ ዓ.ም. ከታተመው ዜና ቤተ ክርስቲያን መጽሔት ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ‹‹የኛ ሲኖዶስ ከግብጽ ሲኖዶስ ጋራ ተወያይቶ ችግሩን ለመፍታት መሞከር ነው፤›› ብለው ነበር፡፡ የአኹኑ ጉብኝታቸው በግፍ ለተነጠቅነው የታሪክና የቅድስና ይዞታችን ሲኖዶሳዊ መፍትሔ የሚመቻችበት ስለመኾኑ ለጊዜው የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከሢመተ ፕትርክናቸው በኋላ በግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሚያካሒዱት ጉብኝት የመጀመሪያቸው ሲኾን በጥቅምት ወር ፳፻፮ ዓ.ም. በአሜሪካ ካደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ቀጥሎ ደግሞ ኹለተኛው ይኾናል፡፡
ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጋራ ብፁዓን አባቶች÷ አቡነ አትናቴዎስ የደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ አቡነ ገብርኤል የሲዳማና ጉጂ ሊበን ቦረና አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ አቡነ እስጢፋኖስ የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና አቡነ ያሬድ የሶማሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ የበላይ ሓላፊ አብረው እንደሚጓዙ ታውቋል፡፡
በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ቤተ ክርስቲያን ከውጭ አኃት አብያተ ክርስቲያን ጋራ ያላትንና የሚኖራትን ግንኙነት ከሃይማኖትና ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን አንጻር እየገመገመ የሚያስፋፋና የሚያጠናክር ሲኾን፣ የዚኹ ጉብኝት አስፈላጊነትም በቅዱስ ሲኖዶሱ ቀርቦ ከታየ በኋላ የታመነበትና የተወሰነበት መኾኑ ተጠቅሷል፡፡
