ተዋሕዶ በተዐቅቦ
ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በሚነሡ መድረኮች ላይ አንድነትና ኅብር ዋና መከራከሪያዎች ናቸው፡፡ አንዳንዶቻችን የብሔረሰቦች ተናጥላዊ መብትና ማንነት እየጎላ መምጣት፣ ሰዎችም ለአካባቢያዊ ማንነታቸው፣ ቋንቋቸውና ባሕላቸው ይበልጥ እያሳሱ መሄድ ኢትዮጵያዊ የሚባለውን ማንነት እንዳያጠፋውና ቆይቶም ኢትዮጵያ የምትባለውን አንዲት ሀገር እንዳይበታትናት እንሰጋለን፡፡ ሌሎቻችን ደግሞ ኢትዮጵያዊ የሚባለው ባሕል፣ ማንነት፣ ታሪክና ግዛት በውስጡ የሚገኙትን ልዩ ልዩ ቋንቋ፣ ባሕል፣ ታሪክ፣ ማንነት፣ያላቸውን ብሔረሰቦች እንዳይውጣቸው፣ ህልውና እንዳይነፍጋቸው፣ መብታቸውን እንዳይነፍጋቸው እንፈራለን፡፡
በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ አንድነትንና ልዩነቶችን(ኅብርን) አስታርቆና አስማምቶ እንደመጓዝ ያለ ፈታኝ የቤት ሥራ የለም፡፡ ሁለቱም የሀገሪቱ እውነታዎች ናቸውና፡፡ ኢትዮጵያ የምትባል ሁላችንንም እንደሰበዝ ያያያዘችና የያዘች ሀገር አለችን፡፡ ከነ ልዩ ታሪኳ፣ ማንነቷ፣ ባሕሏና ስሜቷ፡፡ ደግሞም እያንዳንዳችን ቀየ፣ ጎጥ፣ ጎሳ፣ ነገድ፣ ብሔረሰብ አለን፡፡ ከነ ልዩ ታሪኩ፣ ባሕሉ፣ ቋንቋው፣ ልማዱና ወጉ፡፡
ጥያቄው እንዴት ሳይጣሉና ሳይጠፋፉ እናስኪዳቸው ነው፡፡
እንደ እኔ እንደ እኔ ኢትዮጵያዊ የምንለው የሁላችንም የሆነው፣ ማንነት፣ ታሪክ፣ ባሕል፣ ሀገር፣ ዜግነትና ክብር ብሔረሰባዊ ማንነትን፣ ታሪክንና ባሕልን ሳይድጠው፣ ሳይውጠው፣ ሳያጠፋውና ሳይመጠው፣ ሳይጨፈልቀውና ሳይጠቀልለው፤ የብሔረሰብ ማንነት፣ ታሪክ፣ ባሕልና ልማድም ኢትዮጵያዊ አንድነትን ሳይከፋፍለውና ሳይበታትነው፤ ሁለቱም ያለ መነጣጠልና ያለ መጠፋፋት፣ በተዐቅቦ ተዋሕደው፤ አካባቢያዊ ባሕል፣ ቋንቋ፣ ልማድና ማንነት ለኢትዮጵያዊነት ውበቱ፣ ጌጡ፣ ሀብቱ፣ ሰበዙና አክርማው ሆኖ፤ ኢትዮጵያዊነትም ለአካባቢያዊ ማንነት ኩራቱ፣ የጋራ መገለጫው፣ መዋሐጃውና መግባቢያው፣ በጋራም የሚገነባው የተግባቦት ቤቱ ሆኖ፤ የአንዱ መኖር ሌላውን ሳያጠፋው፤ የአንዱ መኖርም ሌላኛውን ሳያስክደው፤ አካባቢያዊ ማንነት ለኢትዮጵያዊነት መጋቢው ጅረቱ፣ ኢትዮጵያዊነትም ለየአካባቢያዊ ማንነት መሰባሰቢያው፣ መታያው፣ ዓባዩ ሆኖ፤ አካባቢያዊነት ግብዐቱ፤ ኢትዮጵያዊነት ወጡ፤ አካባቢያዊነት ድርና ማገሩ፣ ኢትዮጵያዊነትም ጋቢና ቀሚሱ፤ አካባቢያዊነት ፊደሉ፤ ኢትዮጵያዊነት ጽሕፈቱ፤ አካባቢያዊነት ቃሉ፣ ኢትዮጵያዊነት ድርሰቱ፣ አካባቢያዊነት ብሎኬት፣ ኢትዮጵያዊነት ሕንጻ፤ አካባቢያዊነት ብልት፣ ኢትዮጰያዊነት አካል ሆኖ መኖር ያለበት ይመስለኛል፡፡
ኢትዮጵያዊነት የሁላችን ድምር ውጤት፣ የሁላችንም የጋራ ቤት፣ የሁላችንም ማንነት ውሕደት ያስገኘው ልዩ የሆነ ማንነት ነውና ከአካባቢያዊ ማንነቶች ሁሉ ይሰፋል፣ ይበልጣልም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከአካባቢያዊ ማንነት የሰፋ ለየት ያለ ማንነት ያላቸው፤ እንዲያውም አካባቢያዊ ማንነትም የሌላቸው ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ ከተለያዩ ጎሳዎች፣ ነገዶችና ማንነቶች ከመጡ ቤተሰቦች የተገኙ፤ አንድ ብቻ የሆነ ማንነት የሌላቸው፤ ሦስትና አራት ማንነቶችን ያዋሐዱ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ እነዚህን የዚህ ጎሳ፣ ነገድ፣ አካባቢ ሰዎች ማለት አንችልም፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሌላ ሀገር ተወልደው፣ ኢትዮጵያዊ ዜግነትን አግኝተው፣ ነገር ግን ከኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ከአንዱ ያልተወለዱ ኢትዮጵያውያንም አሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ የሚጠቀልል ነው ኢትዮጵያዊነት፡፡
ኢትዮጵያዊና አካባቢያዊ ማንነት ተጣጥሞ የመሄጃው መንገድ የተዐቅቦ ተዋሕዶ ይመስለኛል፡፡ ተዐቅቦ ማለት ሁለቱም በየራሳቸው ራሳቸውን እያሳደጉ፣ አንዱ አንዱን ለማጥፋት፣ ለመደፍጠጥና ለመጨፍለቅ፣ ለመበታተንና ለመሰነጣጠቅ ሳይሠራ፣ ሂደቱን ለተፈጥሯዊ ሂደት ትቶ ነገር ግን ዕውቅና ተሰጣጥቶ መኖር ማለት ነው፡፡ ተዋሕዶ ስንል ደግሞ አካባቢያዊ ማንነት ኢትዮጵያዊነትን ገንዘቡ አድርጎ፤ ኢትዮጵያዊ ማንነትም አካባቢያዊ ማንነትን ገንዘቡ አድርጎ፤ በተቃርኖ ሳይሆን በተዋሕዶ መኖር ነው፡፡ በተዐቅቦ ምክንያት መለያየት እንዳይመጣ ተዋሕዶ እያረቀው፤ ተዋሕዶ መጠፋፋትን እንዳያስከትል ተዐቅቦ እያቀናው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ሲባል የአካባቢያዊ ማንነቶች ድምር ውጤት ብቻ ሳይሆን በሂደት ተጣጥመውና ተገናዝበው የፈጠሩት የላቀ አንድ ውሑድ ማንነት ሆኖ መጓዝ ነው፡፡
ይህንን ሂደት ውጤታማ ለማድረግ ሦስት ነገሮች የሚያስፈልጉ ይመስለኛል፡፡ ማከም፣ መተዋወቅና ነጻነት፡፡ በታሪክ ሂደት ውስጥ ሕዝቦችን እንወክላለን የሚሉ አካላት ተጋጭተዋል፡፡ መቼም ሕዝብ ለሕዝብ መክሮና ወስኖ አይጋጭምና፡፡ እነዚህ ግጭቶች በአንደኛው ወይም በሁሉም ላይ ትተውት የሚያልፉት ቁስል አለ፡፡ ይህንን ቁስል እንዲያመረቅዝ በየጊዜው ኮምጣጤ ከመጨመር ይልቅ ወደ ማከም ብናደላ መልካም ነው፡፡ በነበሩት ችግሮች ላይ በይፋ ተወያይቶ፤ በችግሮቹ ላይ ተግባብቶ አብሮ መፍትሔውን መፈለግ፡፡ ትናንትን ምንም ልናደርገው አንችልም፡፡ አልፏል፡፡ ልናክመው ብቻ ነው የምንችለው፡፡ ነገን ግን እንደምንፈልገው አድርገን መቅረጽ እንችላለን፡፡ አሁን እንደሚታየው ቁስሉን እየገላለጥን ታማሚውን አካል ይበልጥ እንዲያመው አድርገን ከመተው ይልቅ፣ ቁስሉን ገላልጦ ትክክለኛውንም ሕክምና ሰጥቶ ማዳን ያስፈልገናል፡፡
በርግጥ ሕመም የህልውናቸው መሠረት የሆኑ አካላት አሉ፡፡ ልክ አንዳንድ ነዳያን ቁስላቸውን ለልመና እንደ ሚጠቀሙበት፤ ከቁስል መዳናቸውን ሳይሆን ራሱን ቁስሉን ለገበያ እንደሚፈልጉት ሁሉ የሕዝቦችን ቁስልም ለገበያ የሚፈልጉት አካላት ይኖራሉ፡፡ የሚያተርፉት ከቁስሉ በመሆኑ ምንጊዜም ስለቁስላችንና ማን እንዳቆሰለን እንጂ እንዴት ልንድን እንደምንችል አይነግሩንም፡፡ መድኃኒቱን አያሳዩን፡፡ ቁስለኞቹ ግን መዳኑን እንፈልገዋለን፡፡ ለዚህ ነው ማከም አለብን የምለው፡፡ አንድ በሽተኛ የሕመሙን ዓይነትና ምክንያት ማወቁ ብቻ ለድኅነት አያበቃውም፡፡ እንዴት ሊድን እንደሚችል ማወቅ፣ መድኃኒቱንም ማግኘት ይበልጥ ይጠቅመዋል፡፡ በኢቦላ በሽታ ያለቁ የምዕራብ አፍሪካ ወገኖቻችን፣ የበሽታውን መነሻና አስተላላፊ ዐውቀውታል፡፡ የቸገራቸው መድኃኒቱ ነው፡፡
ሁለተኛው ደግሞ መተዋወቅ ነው፡፡ አጥር ከመሥራት ድልድይ መሥራት፤ ድንበርተኛ ከመሆን በረኛ መሆን የተሻለ ሕይወት ይሰጠናል፡፡ ሁሉም በአካባቢው ቋንቋ መማሩና ቋንቋውን ማደሳደጉ መልካም ነው፤ መብትም ነው፡፡ ቋንቋ ግን በራሱ ሰዎች ብቻ አድጎ አያውቅም፡፤ እንግሊዝኛ ያደገው በእንግሊዞች ብቻ አይደለም፡፡ ከጃፓን እስከ አሜሪካ ያሉት ሁሉ ተሳትፈውበት ነው፡፡ ተምረውት፤ ዐውቀውት፤ ተጠቅመውበት ነው፡፡ አማርኛን ያሳደጉት ‹አማሮች› ብቻ አይደሉም፡፡ እንዲያውም ከጥንት ጀምሮ የአማርኛን ሥነ ጽሑፍ ያሳደጉት ‹አማራ› ከሚባለው የተለምዶ አካባቢ ውጭ ያሉ ሊቃውንት ናቸው፡፡ አማርኛ የኢትዮጵያ ጎሳዎች፣ ነገዶችና ወገኖች ሁሉ ተሳትፈውበት ነው ያደገው፡፡
ዛሬም የሌሎችን ወገኖቻችንን ቋንቋዎች እናሳድግ ካልን መፍትሔው አጥር ሠርቶ ለብቻ መነጋገር ሳይሆን ሌሎችም እንዲያውቁት፣ እንዲጠቀሙበትና ገንዘብ እንዲያደርጉት ማብቃት ነው፡፡ አሁን የምንከተለው የአንድ ቋንቋ ፖሊሲ የሚያዋጣ አይመስለኝም፡፡ አንድ ሰው ኦሮምኛን ለመቻል ኦሮሞ፣ ሶማልኛን ለመቻል ሶማሌ፣ ትግርኛን ለመቻል ትግራዊ የመሆን ግዴታ ሊኖርበት አይገባም፡፡ ከዚህ ይልቅ በአንድ አካባቢ ያሉ ኢትዮጵያውያን ከክልላቸው ቋንቋ በተጨማሪ ሌሎች ቋንቋዎችን የሚያውቁበት መንገድ መፈጠር አለበት፡፡ ቢያንስ ሶማልኛ፣ ትግርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ሲዳምኛ፣ ወላይትኛ በሁሉም ክልሎች በአማራጭነት ቀርበው፤ አንድ ተማሪ ከክልሉ ቋንቋና ከፌዴራሉ ቋንቋ በተጨማሪ ቢያንስ ሁለቱን ጨምሮ እንዲማር መደረግ አለበት፡፡ ቋንቋ መለያያችን ሳይሆን መግባቢያችን መሆን እንዲችል፡፡ ቋንቋ አጥር ሳይሆን ድልድይ እንዲሆን፡፡
ዛሬ ዛሬ በአንዳንድ ክልሎች ከሌሎች ክልሎች ከሚመጡ ወገኖቻችን ይልቅ የውጭ ሀገር ሰዎች የተሻለ ነጻነት ይሰማቸዋል፡፡ ከክልላቸው ውጭ የሥራ ዕድል ለማግኘት(መያድ ካልሆነ በቀር) የማይችሉ የአንዳንድ ክልሎች ሰዎች አሉ፡፡ ይኼ ሁኔታ በሕዝቦች መካከል መጠራጠርን፣ አለመግባባትንና በጠላትነት መተያየትን ይፈጥራል፡፡ እየቆየ ደግሞ ቂምና በቀልን ለትውልድ ያኖራል፡፡ እያንዳንዱ በሌላው ክልል የደረሰበትን በራሱ ክልል ሲበቀል አገሪቱ የማያልቅ አዙሪት ውስጥ ትገባለች፡፡ የወደፊቱን እያሰበች ከመጓዝ ይልቅ ትናንት የተፈጠሩትንና ዛሬ የሚያገረሹትን ችግሮች በመፍታት ላይ ትጠመዳለች፡፡ ለዚህ ነው ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ክልል ተዘዋውረው ሲኖሩና ሲሠሩ ነጻነት እንዲሸታቸው፤ ደኅንነት እንዲሰማቸው ማድረግ የሚያስፈልገው፡፡ ኢትዮጵያውያን ነጻነትና ደኅንነት የሚሰማቸው በክልላቸው ውስጥ ብቻ ከሆነ ዐውቀንም ይሁን ሳናውቅ በአንዲት ሀገር ውስጥ ሊግባቡ የማይችሉ ብዙ ሀገሮች እየፈጠርን ነው ማለት ነው፡፡
ለዚህ ነው የተዐቅቦ ተዋሕዶ ይሻለናል ያልኩት፡፡ መጠፋፋትን በተዐቅቦ፣ መለያየትን በተዋሕዶ፤ ማጠቃለል ዝርዝሮችን ያስረሳል፤ መዘርዘር ደግሞ ጠቅላላን ነገር ያጠፋል፡፡ ዝርዝርን በተዋሕዶ፤ ጥቅለላን በተዐቅቦ፤ የከረረ አካባቢያዊነት ብሔራዊነትን ይንዳል፤ የተለጠጠ ብሔራዊነትም አካባቢያዊነትን ይጨፈልቃል፣ ስለዚህም ብሔራዊነትን በተዐቅቦ፣ አካባቢያዊነትን በተዋሕዶ እያረቅን ኢትዮጵያን ወደ ልዕልና እንውሰዳት፡፡ መገናዘብ(አንዱ ሌላውን ገንዘቡ ማድረግ) እንጂ መጠፋፋት ለዚህ አይበጀንም፡፡