ዋጋሽ ደም ሆነና!!!
ዋጋሽ ደም ሆነና!!!
አገሬ ኢትዮጵያ ዋጋሽ ተወደደ፤
አልደረስንበትም እየላቀ ሄደ፤
እንደ አልማዝ፤ እንደ ወርቅ፤ ከእንቁም የከበረ፤
እንደ ፕላትነም፤ እንደ ሩቢ ናረ።
ቁመትና፤ ዉርዱ፤ ፈርጅና፤ መጠኑ፤
የዋጋሽ መለኪያው፤ ምን ይሆን ሚዛኑ?
ቢሆንማ ኖሮ፤ ዋጋሽ ኢሮ/ ዶላር፤
ያለው ን ይሚያፈስ ሞልቶሽ ነበር ቱጃር።
ታስሮ የሚንገላታ፤ ወህኒ የሚሰቃይ፤
አሣር፤ ፈተናውን፤ መከራውን የሚያይ፤
በሽበሽ፤ ነበር ሞልቷል የህሊና እስረኛ፤
ዕውነትን አብሳሪ ጀግና ጋዜጠኛ።
ፖሊቲካ ተንታኝ፤ የሚያፈዝ፤ ሲናገር፤
ባለ ፒኤች ዲ፤ ዶክቶር ፤ ፕሮፌሶር፤
ሞልቷል ጥበበኛ፤ ሊቅና ፈላስፋ፤
ጽፎ የማይደክመው፤ የማይቆርጥ ተስፋ።
በአደባባይ ቆሞ ፤ ላንቺ የሚከራከር፤
ጠበቃስ መች ጠፋ ፤ የሚሟገት ላገር።
እግዚአብሔርን ፈሪ ለነፍሱ ያድረ፤
ሁሉን በቃኝ ብሎ፤ ባለም፤ ያመረረ፤
የሚያድር ከዋሻ፤ በገዳም መንኖ፤
ጿሚ፤ ጸሎተኛ፤ የመነኩሴ ፋኖ፤
ፅላት ተሸክሞ ባርኮ የሚቀድስ፤
አውግዞ የሚያስር፤ አቡንና ጳጳስ፤
ዲያቆናት ፤ ቀሳውስት፤ የክነት አለቆች፤
መች አጣሽ ! ኢትዮጵያ ሞልተውሻል ሊቆች።
ሰደቃ እያበላ፤ ለድሃ እየቸረ፤
ተውሂድና፤ ተውፊቅ፤ ቁራን ያስተማረ፤
ሼህ፤ ኢማሙ፤ ሃጂው፤ አላህን የፈራ፤
ሙ አ ዘን ማልዳ ለሶላት ሲጣራ፡
ሙስሊም ሶላት ሲያቀርብ በአንገቱ ተደፍቶ፤
አላህ! ዋክበር ብሎ ፤ በስሙ ተጣርቶ፤
ጌታን ተማጸነ ፤ ላላህም፤ ሰገደ፤
ያም አልበቃ፤ ላንቺ ዋጋሽ ተወደደ።
ሞልቶሻል ኢትዮጵያ ቤት ዘግቶ የሚናደድ፤
ውስጥውጡን የሚጨስ ተቃጥሎ የሚነድ።
ቆራጥ አጣሽ እንጂ ያል፤ ታደልሽ አገሬ፤
ሞት ባርኮ የሚቀድስ እንደኔሰው ገብሬ።
ሞልቷል መቼ ጠፋ ባፉ የሚደነፋ፤
ጠላትሽን የጠላ፤ አክ! ብሎ የተፋ፤
ግ ና ምን ያደርጋል! ዋጋሽ ደም ሆነና ጠብ! የሚለው ጠፋ።
ይፍሩ ኃይሉ
ኔው ሄድቨን፤ ከነቲከት