አንዳርጋቸው የኔ ጀግና ነው እያሉ በፌስ ቡክ መለጠፍ የትም አያደርስም – ኪሩቤል በቀለ

Andargachewአንዳርጋቸው የኔ ጀግና ነው እያሉ በፌስ ቡክ መለጠፍ የትም አያደርስም:: ማቅራራቱና ግጥሙን መደርደሩም ብቻውን ዋጋ የለውም:: ደግሞ ደጋግሞ ስለወያኔ ፀረ-ሕዝብነት ማውራት ምን ዓይነት ግራ የተጋባው አካሄድ ነው? ስለወያኔ ከዚህ በላይ ምንም ማወቅ አያስፈልገንም:: አየነው እኮ 23 ዓመታት ሙሉ::ኢትዮጵያ ጫካ ውስጥ ያሉ ዝንጀሮዎች እንኳ ወያኔን ደን እየመነጠረና እያቃጠለ መኖርያ ሲያሳጣቸው ያቁታል::
 
ከአንድ ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በመላው ዓለም ተሰራጭተው ኢሳት 5000 ሰው በወር 20 ዶላር ማለት በቀን 65 ሳንቲም የሚሰጡ ሰዎች አላገኘም:: ይህ ብቻ አይደለም:: አሁን በእስር ላይ የሚገኙትን የእነ እስክንድርና የእነ በቀለ ገርባን ቤተሰቦችን የሚረዱ ሰዎችም አልተገኙም:: አንዳርጋቸውንና ኢትዮጵያን ነጻ ለማውጣት ቀርቶ በቀን 65 ሳንቲም ለመስጠት ጽናቱና ቁርጠኝነቱ የለንም:: ታዲያ ኢትዮጵያ እንዴት ነው  ነጻ የምትወጣው?  በባዶ ሜዳ መፎከሩንና ሽለላውን ተወት አርገን ማተኮር ያለብን ወያኔን እንዴትና የት ላይ እንምታው ነው:: 
 
አንዳርጋቸው አሁን የሚፈልገው ጅግና እያለ የሚያሞካሸውን ባዶ ሙገሳ ሳይሆን እሱን ተክቶ ትግሉን አፋፍሞ እሱንም ሌሎችንም ጅግኖች እንዲሁም መላውን ኢትዮጵያ ነጻ ማውጣት ነው::እውነት የዛሬው ወጣት ወያኔን ለማውረድ ሃሞት የለውም እንዴ? መሰደድ መፈርጠጥና ጫት መቃም መጠጣት መዝፈን በገንዘብና በወሲብ ፍቅር ማበድ ነው እንዴ የሚያውቀው? ወደ ሳኡዲ ዓረቢያ በወር 25,000 ወጣቶች ገረድና አሽከር የመሆናቸው ሳያንስ እየተደበደቡና እየተዋረዱ ለመኖር የሚመርጡት በምን ሂሳብ ነው? ለነጻነት ወደ ጫካ ሳይሆን ለባርነትና ለውርደት ወደ አረብ አገር መሄድን የሚመርጡ ወጣቶችን ኢትዮጵያ እንዴት አፈራች?  ወደ መሬት ወርደው ወጣቱናን ሕዝቡን ለመምራት ወኔውም ችሎታውም ያላቸው መሪዎች ኢትዮጵያ እንዴት አጣች? 
 
ምናልባት ከዚህ የወያኔ ውርደት አንድ ጥሩ ነገር ያለ ይመስላል:: ሳይደግስ አይጣላም ነው ነገሩ:: አንዳርጋቸው በዚህ ቭድዮ ሁለት መልእክቶችን ለማስተላለፍ እድል ያገኘበት አጋጣሚ ነው::
 
1) ለወጣቱ ትልቅ መልእክት አስተላልፏል:: እንደ በፊቱ ትውልድ በቆራጥነት አገራችሁን ነጻ አውጡ ብሎ ተናግሯል:: አለበለዚያ ባርነቱ ይቀጥላል ብሏል:: ስለዚህ የዘመኑ ወጣቶች የአንዳርጋቸውን መልእክት ሰምታችሁ አገራችሁን ነጻ ለማውጣት ተነሱ::
 
2)ለተለያዩ የተቃዋሚ መሪዎችም አንዳርጋቸው መልእክት አስተላልፏል:: በድጋሚ ወደ መሬት ወርዳችሁ ሃቀኛውን ትግል ተቀላቀሉ ብሏል:: በሪሞት ኮንትሮል ትግል ብሎ ነገር የለም ብሎአል:: እኔ ወደ መሬት ወርጄ ስታገል በጠላት እጅ ወድቄአለሁና መታገል አልችልም:: ያለኝ አማራጭ የሚሉኝን ተገድጄ በመናገር ስቃዬን መቀነስ ነው:: አሁን እናነተ ደግሞ ወደ መሬት በመውረድ ተረከቡኝ ብሏል::
 
እንግዲህ የሚሰማ ካለ ይስማ:: ካልሆነም እንደተለመደው ሰምቶ እንዳልሰሙ ሆነው በባዶ መንጫጫት ነው አማራጩ:: ወያኔም እኛን ማዋረዱን ይቀጥላል:: እኛም በባዶ መንጫጫታችን ይቀጥላል::
 
ይህንን ውርደት እስከመቼ ነው ዝም ብሎ መመልከት የሚቻለው ጎበዝ? ያን ያህል የምናከብረውን ጅግናችንን ወያኔ አፍኖ አሥሮ ደግሞ ደጋግሞ የሥነ-ልቡናና ርካሽ የፕሮፓጋንዳ መጫወጫ ሲያደርገው ምንም ሳያደርጉ ቁጭ ብሎ ብቻ መመልከት ያስቻለን ምን ዓይነት ልብና አእምሮ ቢኖረን ነው? 
አሁን ይበልጥ ለቡዙ ሰውና ለምእራብ አገር ተራማጅ ሃይሎች እየተገረሙ የመጡበት ነገር የወያኔ ርካሽ ተግባር መደጋገም ሳይሆን የኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ሃይሎች ዝም ብሎ መመልከት ነው:: በወያኔ ላይ ቆራጥ ርምጃ ያለመውሰድ ምክንያት የሆነው የተቃማዊው የሃሞት መፍሰስ ቡዙዎችን አስገርሟል:: ወያኔ በሽለላና በስድብ ጋጋታ አይወርድም::
 
አለበለዚያ ዝም በሉ! በጫጫታ የፈረሰች አገር ኢያሪኮ ብቻ ነች ብሎ ያ ደደብ ደርግ ሲፎክር ትዝ ይለኛል:: ደርግ አምላክን ከሃዲ ሆኖ ነው እንጂ የኢያሪኮ ግንብ የፈረሰው አምላክን በእውነት ባመኑና በእርሱ በተመኩ ሰዎች ጸሎት ነው:: ግንቡን ያፈረሰው የሰዎቹ ጫጫታ ሳይሆን አሁን በቅርቡ ወያኔን በሚደመሥሰው በአምላክ ሃይል ነው::እኛ ግን ወይ ከጸሎቱ አይደለን ወይ ጅግንነቱ የለን እንዴት አርገን ነው ወያኔን የምናፈርሰው? ሰላማዊ ሰልፍ ማብዛትና የጽሁፍ ብዛት መቆለል የትም የማያደርስ ጫጫታ ነው:: በጫጫታ ወያኔ አይፈርስም:: በቆራጥ እርምጃ እንጂ!
 
ይህን በአውሬው ወያኔ እየተፈጸመ ያለውን አንዳርጋቸውን አስግድዶ የማናዘዝን ወንጀል ዝም ብሎ በቃል መልስ መስጠትና ማውገዝ ብቻ በቂ አይደለም:: ይህ ወንጀል ትልቅ ሕዝባዊ አመጽ ማስነሳት ያለበት በነበረከት እየተፈጸመ ያለ አረመኔያዊና ፀረ-ህዝብ ወንጀል ነው::
 
ማንም ሰው ተገድዶ የሚናገረውን ነገር እውነት ነው ብሎ የሚያምን ጂል ሰው ያለ አይመስለኝም:: የሚናገረው ነገር ሁሉ እንኳን እውነት ቢሆን በግዳጅ የተናገረው ነገር ተቀባይነት አይኖረውም:: አሁን አንዳርጋቸው የተናገረውን ለመቀብል መጀመሪያ በነጻነት የሚናገርበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል:: ሰብኣዊ መብቱ ተጠብቆና ተከራካሪ ጠበቃ ከጎኑ ቆሞ ከቶርቸር ነጻ ወጥቶ መሆን አለበት::
 
ስለሆነም አንዳርጋቸውን በቶርቸር እያስገደዱና ሰብአዊ መብቱን ሳይጠብቁ የሚያንገላቱትን ኢሰብኣዊ ወንጀል በአስቸኳይ የሚያቆሙበትን ግፊት መፍጠር ያስፈልጋል:: ለምሳሌ 1) በመላው ዓለም የሚገኙ የወያኔ ኤምባሲዎችን መውረር ልክ ዋሺንግተን ዲሲ ውስጥ እንደተካሄደው ማለት ነው:: የወያኔ ኤምባሲውችን የመውረር አስቸኳይ እርምጃ አሁን በመላው ዓለም መካሄድ አለበት:: አለበለዚያ ወያኔ ከዚህ የባሰ ወንጀል መፈጸሙን ይቀጥላል::
 
ይህን ፀረ ሕዝብ ወራዳና ዘረኛ የወንጀለኛ ቡድን በቃላት ብቻ ማስቆም አይቻልም:: ዲሲ ውስጥ እነ ሽመልስ በወያኔ ኤምባሲ ላይ የወሰዱትን ዓይነት ቆራጥ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል:: ወያኔ በተግባር ባዋረደን ቁጥር እየለፈለፍን ራሳችንን አናቅልል:: አጸፋውን ባገኘነው መንገድ መመለስ አለብን:: የተቃውሞ ሰልፍ ብቻ መውጣት በቂ አይደለም:: የዋሺንግተን ዲሲው ጅግንነት በቡዙ ቦታዎች ላይ መደገም አለበት::
 
ወያኔ በጽሁፍ ብዛት በሽለላና በስድብ ጋጋታ አይወርድም!
 
በባዶ ሜዳ መፎከሩንና ሽለላውን ተወት አርገን  ዝም ማለቱ ይበጃል:: እየፎከሩ መቅለል በዛ::አቅምን ማወቅ አንዳንድ ጊዜ ጥሩ ነው:: ማኝክ የማይችሉትን መግመጥ ለመታነቅ ነው:ይላሉ ፈረንጆች::
 
በሰላማዊ ሰልፍና በቃላት መልስ ብቻ ሳይሆን በወያኔ ላይ ቆራጥ ርምጃ ወስዶ አጸፋውን ለመመለስ  አሁኑኑ ተነሱ! 
 
ስለ ስሜታዊነቴ ይቅርታ! ሃዘንና የብቀላ ስሜት የፈጠሩት የመንፈስ ምሬት ነው::
 
አመሰግናለሁ!
ኪሩቤል በቀለ