አብዮታዊ ዴሞክራሲ ሲታወስ – ሁኔ አቢሲኒያ
አብዮታዊ ዴሞክራሲ ሲታወስ
ሁኔ አቢሲኒያ
አጼ ቴዎድሮስ የአማራ ብሄርተኝነትን ለማስፋፋት የታገለ መሪ ነበር (የወረዳው አስተዳዳሪ የተናገሩት)
በትላንትናው እለት ለገዢው ፓርቲ ካድሬዎች እስኪ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ምንድን ነው? አብዮታዊ ዴሞክራሲስ የሚባል ነገር አለ ወይ? አብዮታዊ ዴሞክራሲ እውን ካለስ ጽንሰ ሀሳቡ ከየት መነጨ? መድረሻውስ ምንድን ነው? ልማታዊ ዴሞክራሲስ ምንድን ነው? ለመሆኑ ልማታዊ ዴሞክራሲስ የሚባል ቲዮሪ አለ ወይ? የሚል ጥያቄ አቅርቤ ነበር ይህንን ጥያቄ ያቀረብኩት መልስ ፈልጌ ሳይሆን ካድሬዎቹ እናውቀዋለን የሚሉትን ፓርቲያቸውን እና ረእዮተ አለም እንደማያውቁት ማስገንዘብ ፈልጌ ሲሆን ይህንን የተገነዘብኩት ከአመታት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ በመምህርነት ሙያ ሳገለግል እታዘባቸው የነበሩ እውቀታቸው ሳይሆን ካድሬነታቸው ታይቶ አብረውኝ ያስተምሩ የነበሩ ካድሬ መምህራንን ማንሳት ፈልጌ ነው።
ኢህአዴግ አባላት ለማፍራት ከሚሯሯጥባቸው የሙያ ማህበራት መካከል አንዱ የመምህርነት ሙያ ነው። ህወሀት ኢህአዴግ በየትምህርት ቤቱ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል በርካታ አባል መምህራን አሉት አስገራሚው ነገር ግን እነዚህ አባል መምህራን የኢህአዴግ አባል የሆኑት እውን የኢህአዴግ አባል መሆን ፈልገው አልያም የድርጅቱ ርእዮተ አለም ገብቷቸው አልነበረም የኢህአዴግ አባል መምህራን አስተያየት ለመስጠት እጃቸውን ሲያወጡ አባል ያልሆንን መምህራን በሚያወሩት ወሬ እንስቅ እና እንሸማቀቅ ነበር። እኔን የኢህአዴግ አባል ለማድረግ ተልከው ከነበሩት የኢህአዴግ አባላት መካከል ዛሬ የአዲስ አበባ ከተማ አሰተዳደር ትምህርት ቢሮ የስርአተ ትምህርት ክፍል ዋና ሀላፊ አቶ ንጉሴ አንዱ ነበር። ንጉሴ እንደማንኛውም የኢህአዴግ አባላት አብዮታዊ ዴሞክራሲ ምን እንደሆነ የማያውቅ ግን ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር የቆመ ራእዩ የሆነ ክፍለ ከተማ አስተዳዳሪ መሆን የነበረ አንድ ካድሬ ነበር። ዘወትር እየመጣ ”ይሄውልህ አንተ ወጣት ነህ በዛ ላይ የከተማ ልጅ ተምረሃልም ኢህአዴግ ደግሞ አዲስ አበባን ለማስተዳደር እንዳንተ አይነት የተማረ የአዲስ አበባ ልጅ ያስፈልገዋል” የሚሉ አረፍተ ነገሮችን በተደጋጋሚ ይነግረኝ እና አባል ለማድረግ ሲሞክር ”የተማረ አባል ከፈለጋቹህ ከእኔ ይልቅ ለምን ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን አትሰብኳቸውም እለው ነበር። ሌላ ጊዜ ይመጣና ደግሞ ሲያናገርኝ አጓጉተሀኝ ሳይሆን አሳምነሀኝ አባል አድረገኝ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ምንድን ነው? አንተ እውን ታውቀዋለህ ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ሳቀርብበት ከትምህርት ቤቱ በዝውውር ወደ ሌላ ትምህርት ቤት እንድሄድ አስደረገ እርሱም በርካታ አባላት አፍርተሃል ተብሎ አዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ገባ።
በአንድ ወቅት ደግሞ አንድ የታሪክ መምህር ጓደኛዬ ያጋጠመው ታሪክ እስከዛሬ የሚያስቀኝ የሚያስገርመኝም ነው። ጉዳዩን በሌላ የብእር ስም ይሄው ጓደኛዬ ሌላ አካባቢ የተፈጠረ አድርጎ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ አውጥቶት ነበር። እንዲህ ነው ጉዳዩ እኔ እሰራበት በነበረው ትምህርት ቤት የመምህራን ስብሰባ አለ ይባልና መምህራኖች የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ እንገባለን አስገራሚው ነገር ስብሰባው የትምህርት ጉዳይ ሳይሆን አልማ የሚባል የአማራ ልማት ማህበር ያዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ ነበር እኔና ጓደኞቼ ስብሰባው እንደማይመለከተን ገልጸን እኛ እዚህ ትምህርት ቤት የተገኘነው ለማስተማር እንጂ ለፖለቲካዊ አላማ ለሚውል የልማት ማህበር ያውም በአማራው ስም እየተለመነ የህወሀት እና የብአዴን ሰዎች ኪስ ውስጥ ለሚገባ ገንዘብ አንሰበሰብም ስንል ተቃውሞ አሰማን ይህንን ጊዜ የእለቱ ሰብሳቢ የነበረው የወረዳው ተወካይ በግድ እንድንቀመጥ ካደረገ በኋላ ዲስኩሩን መደስኮር ጀመረ።
”የአማራ ክልል በርካታ ጀግኖችን ያፈራ ክልል ነው በዚህ ክልል ውስጥ በርካቶችን የአማራ ብሄርተኝነት ይስፋፋ ዘንድ ታግለዋል የድርግ ስርአት ተገርስሶ የአማራ ብሄርተኝነት ያብብ ዘንድ የተሰዉ ጀግኖች ብዙ ናቸው አጼ ቴዎድሮስም ቢሆን የአማራ ብሄርተኝነት ያብብ ዘንድ የታገለ የአማራ መሪ ነበረ” ሲል የስብሰባ አዳራሹ በተቃውሞ ቀውጢ ሆነ አብዛኛው መምህር ለመናገር እድል ይሰጠው ዘንድ ጥያቄ አቀረበ ከተረጋጋ በኋላ መምህራኑ ተራ በተራ ንግግራቸውን እና ተቃውሟቸውን አሰሙ አስገራሚው ንግግር ግን ያ ጓደኛዬ የታሪክ መምህሩ የተናገረው ነበር ”እኔ ታሪክ መምህር ነኝ አንድም ቀን ግን አጼ ቴዎድሮስ የአማራ ብሄርተኝነት ያብብ ዘንድ የታገለ ነው ብዬ አስተምሬ አላውቅም” ሲል አዳራሹ በጭብጨባ ተናጋ አለገባኝም ነበር ለካስ ያ የወረዳ አስተዳዳሪ የዚህ የጓደኛዬ የማታ 10ኛ ክፍል ተማሪ ነው።
ለዚህ ነው እኔ ካድሬ የምንቀው ለዚህ ነው የህወሀት አመራሮች የምግብ እንጂ የማንበብ ፍላጎት የላቸውም የምለው።